ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ላይ በቀጣዮቹ ሳምንታት ድርድር እንዲጀምሩ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ጠየቁ

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡

ሁለቱ አካላት በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት ሊወሰዱ በሚችሉ እርምጃዎች ላይ መክረዋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የአውሮፓ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር ጆሴፍ ቦሬል በብራሰልስ ተገናኝተው በተለያዩ ዓለም አቅፍ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ አስነብቧል።

ሁለቱ አካላት ከተወያዩባቸው በርካታ አጀንዳዎች መካከል የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶሰትዮሽ ድርድር እና የትግራይ ክልል ጉዳይ ዋነኞቹ ናቸው።

ብሊንከን እና ቦሬል በውይይታቸው፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በሕዳሴው ግደብ ላይ የሀሳብ መቀራረብ እንዲያሳዩ እና በቀጣዮቹ ሳምንታት ገንቢ ውይይት እንዲጀምሩ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ እየተካረረ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው የገለጹት ሁለቱ ባለስልጣናት ሀገራቱ የድንበር ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአውሮፓ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር የተወያዩበት ሶስተኛው ጉዳይ ደግሞ በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በግጭቱ ለተጎዱ ዜጎች ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦት እንዲኖር ፣ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ እና የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጣ ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች መክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ስለሚወስዷቸው እርምጃዎች በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት አንጻር ፣ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግስት 4.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ማድረሱን ገልጸው በትግራይ ያለው “የሰብዓዊ ሁኔታ ያሳስበናል” የሚሉ አካላት ግን ከወሬ ባለፈ እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አለማድረጋቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

 

 

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe