ኢትዮጵያ በክብር ጉዳይ የግብጽን ጥያቄ ውድቅ አደረገች፤

“ግብጾች ወጪ ችለን ካይሮ ተጫወቱ ቢሉንም የክብር ጉዳይ በመሆኑ ውድቅ አድርገነዋል” – ብሏል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤

የቡድ አሰልጣኝ ግብፅን “በሜዳችን የመግጠም ዕድልን ማጣታችን ሌላ ፈተና ነው” ብለዋል ከግብጽ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ እስከ 50 ሺ ዶላር ወጪ ሊያደርግ እንደሚችል ፌዴሬሽኑ አስታውቋል

በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ጋር የጨዋታ መርሃ ግብር ያላት ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በካይሮ ለመጫወት ጥያቄ አቅርባ እንደነበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፤ ከወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በሰጡት መግለጫ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ለመጫወት ሙሉ ወጪ ለመሸፈን ሃሳብ አቅርባ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው “የግብፅ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሙሉ ወጪያችሁን እንቻልና ካይሮ ላይ ኑና እንጫወት ብለውናል” ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህ የክብር ጉዳይ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉንም ነው አቶ ባሕሩ ያስታወቁት፡፡

ዋና ጸሐፊው በስም ያልገለጿቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አንድ አመራር “መሐመድ ሳላህን የመሰለ ዓለም አቀፍ ተጫዋች በኢትዮጵያ ስታዲየም እንዲጫወት አንፈቅድም” ሲሉ መናገራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ባሕሩ “አንድ የካፍ አመራር መሃመድ ሳላህን የመሰለ ወርልድ ክላስ ተጨዋች በዚያ ስታዲየም ሄዶ እንዲጫወት የምንፈቅድልህ ይመስልሃል ? ብሎናል” ሲሉም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ገንዘብ እስካለ ድረስ በውድድሩ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ባሕሩ፤ በቀጣይ ግን ውድድሮችን እስከ መሰረዝ የሚደርስ ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር በማላዊ ለምታደርገው ጨዋታ የአውሮፕላን ቲኬት የቡድኑ አቅርቦትና አበልን ሳይጨምርእስከ 50ሺህ ዶላር ወጪ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

ካፍ ያስቀመጠው መመዘኛ በዲፕሎማሲና በንግግር ሊፈታ እንዳልቻለም ነው ዋና ጸሐፊው የተናገሩት፡፡

“ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ ባለመገኘቱ ዋጋ እየከፈለ ያለው ብቸኛ ተቋም ፌዴሬሽኑና ተመልካቹ” እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በኮቪድ ያለ ደጋፊ አሁን ደግሞ ከሀገር ውጪ ጨዋታው መካሄዱ ለቡድኑ ከባድ እንደሆነና “ግብፅን በሜዳችን የመግጠም ዕድልን ማጣታችን ሌላ ፈተና ነው” ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe