ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወደ ጉለሌ አካባቢ የሜቴክ ህንጻ ሊዛወር መሆኑ ተሰማ

የተቋቋመበትን 57ኛ ዓመት በያዝነው ዓመት የሚያከብረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ አሁን ከሚገኝበት ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤት ወደ ጉለሌ ሊዛወር መሆኑን ተሰማ፡፡

በቅርቡ የተመሰረተውን አዲስ መንግስት ተከትሎ አዲስ ዋናና ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾመለት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ላለፉት 23 ዓመታት ሲጠቀምበት ከነበረው ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ከሚገኝበት ዋና ማሰራጫ ወደ ጉለሌ መድሃኒያለም አጠቃላይ ትምህርት ቤት አካባቢ ወደ ሚገኝ  አዲስ ህንጻ ለማዛወር ዝግጅት እየተደፈረገ መሆኑ ቁም ነገር መፅሔት ሰምታለች፡፡

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አዲስ የተሾሙት የኢቢሲ የስራ ሀላፊዎች በኢትየጵያ ሆቴል በተዘጋጀው የትውውቅ ስነ ስርዓት ላይ በድንገት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢቢሲ ጥሩ የስራ ሀላፊ ያልወጣለት መስሪያ ቤት መሆኑን ገልፀው ምናልባት  አሰራሩን በአዲስ መልክ ለመቀየር አዳዲስ የስራ ሀላፊዎች ብቻ ሳይሆን ህንፃውንም ራሱን መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ኢቢሲ የሚዛወርበት አዲሱ ህንጻ ጉለሌ አካባቢ የሚገኝ አዲስ የተገነባ የሜቴክ  ህንጻ ሲሆን  በአንድ ዓመት  ጊዜ ውስጥ የራዲዮና የቴሌቪዥን ስቱዲዮ በማስገንባት እንደሚዛወር ተሰምቷል፡፡በቀጣዮቹ ሶስት ወራትም የአስተዳደር ሰራተኞቹን ወደ አዲሱ ህንጻ እንደሚያዛወር በድርጅቱ የ100 ቀናት እቅድ ላይ ተመልክቷል፡፡

የመስሪያ ቤቱን ከከተማ ወደራቀ ስፍራ ማዛወሩን የተቃወሙ የኢቢሲ ሰራተኞች የሚዲያ  ስራ ከከተማ በራቀ ስፍራ ላይ በሆነ ቁጥር መረጃዎችን በፍጥነት ደርሶ ለመዘገብና እንደግዶችንም በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስቸግር በመግለጽ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ራዲዮንና ኤፍኤም 97.1ን  አየር ጤና አካባቢ ወደሚገኝው የዘነበወርቅ አካባቢ የኢትዮጵያ ራዲዮ ግቢ በመዛወሩ የተነሳ ከህዝብ ጆሮ እንዲርቁና በቅርብ በተቋቋሙ አዳዲስ ራዲዮ ጣቢያዎች ለመዋጥ እንደዳረጋቸው በመግለጽ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ንብረት የነበረው አሁን ኢቢሲ የሚገኝበት ህንጻ ምንም እንኳ ለራዲዮና ቴሌቪዥን ተብሎ የተሰራ ባይሆንም በ1990 ዓ.ም በኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ድንገተኛ ውሳኔ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተሰጥቶ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ህንጻው እንዲመለስለት ለዓመታት ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ኢቢሲ ከወራት በኋላ ህንጻውን ለባለቤቱ እንዲመልስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ መቀመጡ ታውቋል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe