ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት አመት በስድስት ወራት ውስጥ 61 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም በሚመለከት ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በቴሌ ብር አማካኝነት አንድ ትሪሊዮን ብር ዝውውር መፈፀሙን ገልጸዋል።
ወጪ ቆጣቢ የዲጂታል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉንም አብራርተዋል።
እንደ ሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሒደት ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ትልቁን ድርሻ ወስዶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ለሦስት ዓመት የሚተገበር አምስት ግቦች ያሉት ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የአገልግሎት ጥራት፣ የገቢ ምንጭ ማስፋት፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት መስጠትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን መፍጠር የስትራቴጂክ ዕቅዱ አካል መሆናቸውን አብራርተዋል።
ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት 202 በሚሆኑ አካባቢዎች አዳዲስ የገመድ አልባ አገልግሎቶችን ማስፋት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በስምንት ከተሞች ላይ የ5ኛ ትውልድ ወይም 5ጂ ኔትወርክ አንዲሁም 67 ከተሞችን የ4ኛ ትውልድ ወይም 4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎችን ዳግም ወደ አገልግሎት ለማስገባት በተሰራው ሥራ 216 አካባቢዎች ሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አብራርተዋል።
ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ተቋሙ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት 61 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ43 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 61 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘ

