ኢትዮ ቴሌኮም እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተከታታይ ውድድሮችን በአጋርነት ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት አደረጉ

ኢትዮ ቴሌኮም እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ2018 የ”ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ” (Discover Ethiopia Classics) ተከታታይ ውድድሮችን በአጋርነት ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት አድርገዋል። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም በአምስት ዋና ዋና ክልላዊ ውድድሮች ላይ የስያሜ ስፖንሰር (Title Sponsor) በመሆን የሚሳተፍ ሲሆን፤ ይህም ኩባንያው ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ለቱሪዝም እድገት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት እና ጽኑ ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የ2018 የሩጫ ተከታታይ ውድድሮችን በአምስት ከተሞች ማለትም በደብረ ብርሃን፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ በቆጂ እና ሐረር
የሚደረጉት ውድድሮች የስያሜ አጋር ሲሆን፣ የመጀመሪያው ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በደብረ ብርሃን ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀምር
ይሆናል፡፡ ይህም ጤናማ እና አምራች ዜጋን ከመገንባት ባሻገር የኢትዮጵያን ውብ መልክዓ ምድሮች፣ ታሪካዊ ቦታዎችና ባህሎች ለማስተዋወቅ
እና መልካም ማህበራዊ ትስስሮችን ለማጠናከር የላቀ ሚና ይኖረዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የታላቁ ሩጫ የቴክኖሎጂ አጋር በመሆን ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ተሞክሮ እንዲኖራቸው የሚያስችል ልዩ
የሩጫ መተግበሪያ (Running App) በማበልፀግ በስራ ላይ ያዋለ ሲሆን፣ ይህም መተግበሪያ በየትኛውም የሀገራችን አካባቢዎች ለሚከናወኑ
ውድድሮች በውድድር ወቅት ያሉ መረጃዎችንና መገኛ ቦታን በቀጥታ ለመከታተል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል። ይህ የቴክኖሎጂ ትስስር
ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የአኗኗር ዘይቤን ለማስተዋወቅ ከሚያከናውናቸው ስትራቴጂዎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር መሳይ ውብሸት እንደገለፁት ኩባንያው ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ዘመኑ
የደረሰባቸውን አዳዲስ የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በሀገራችን ተግባራዊ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮዽያን ራዕይ እውን
ለማድረግ እያከናወነ ከሚገኘው መጠነ ሰፊ ስራዎች በተጨማሪ ከሌሎች ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ለሀገራችን
ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡
አክለውም “ይህ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ“ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ” ተከታታይ ውድድሮች አጋርነት ስምምነትም የዚህ ኢንሸቲቭ አንዱ
አካል ሲሆን፣ ኩባንያው በአካልና በስነ-ልቦና የተገነባ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት፣ የሩጫ ውድድሮቹ የሚካሄድባቸው ከተሞችን ይበልጥ
ለማስተዋወቅና የቱሪዝም መዳረሻ ፍሰትን ለመጨመር እየተከናወኑ የሚገኙ ጥረቶችን ለማጠናከር እንዲሁም በሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ
እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመግለጽ በቀጣይም ለሀገራችን እድገት ቁልፍ ሚና ያላቸውን ተግባራት በመለየትና በቴክኖሎጂ
እንዲታገዙ በማድረግ አጋርነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ በበኩላቸው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሁልጊዜም ከሩጫ በላይ መሆኑን
በመግለፅ ባህላችንን እና ህዝባችንን የምናውቅበት እና የምናስተዋውቅበት መድረክ ነው” ብለዋል። ዋና ስራ አስኪያጇ አክለውም “ኢትዮ
ቴሌኮምን እንደ ዋና አጋር ማግኘታችን ውድድሮቹን ወደ ላቀ ደረጃ እንድናሸጋግር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው” ብለዋል፡፡
ይህ አጋርነት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪዝምን ለማሳደግ ያለውን የጋራ ራዕይ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ የደብረ ብርሃንን ታሪካዊነት፣
የሐዋሳ ሃይቅን ውብ ገፅታ፣ የጅማን የቡና መገኛነት፣ የአትሌቶች መፍለቂያ የሆነችውን በቆጂን በማጉላት እና የሐረርን የቱሪስት መስህብነት
አጉልቶ በማሳየት ኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ ያለመ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe