እናት ባንክ እናቶችን የሚወክል «እማዬ» የተሰኘ ቅርንጫፍ ከፈተ። ባንኩ “እማዬ” የሚል ስያሜ የሰጠው ይኸው ቅርንጫፍ “በእናትነታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ነገር ግን የልፋታቸውን ያህል ያልተፃፈላቸውና ያልተነገረላቸው እናቶች ውክልና እንዲኖራቸው ታስቦ የተከፈተ እንደሆነ ነው የተገለጸው።
ቅርንጫፉ በእናቶች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የሚሰሩበት ቦታ የተዘጋጀለት፤ ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነፃ ማከናወን የሚችሉበት፤ ዲዛይነም ሆነ በውስጡ ያሉት ግብአቶች ብዙሃኑን የሃገራችንን እናቶች እንዲወከል ታስቦ የተሰናዳ እንደሆነ ተነግሯል።
«እማዬ» ትርንጫፍ ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ መታስቢያ ሃውልት ጋር የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት አዲስ ህንፃ ላይ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው “ለእናቴና የአመቱ ድንቅ እናት” የፅሁፍ ውድድር ቢጠናቀቅም “የእማዬ” የቅርንጫፍ መከፈትን ምክንያት በማድረግ በልዩ ሁኔታ መወዳደሪያ ስራዎቻቸውን ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ተወዳዳሪዎች ወደ ቅርንጫፉ በመምጣት ማስገባት ይችላሉ ተብሏል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ እና በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ በአዲሱ “እማዬ” ቅርንጫፍ እንዲሁም በክልሎች ያሉ ተወዳዳሪዎች ስራዎቻቸውን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ ማስገባት ይችላሉ፡፡
የዘንድሮ ዓመት የጽሑፍ ውድድሩ የመዝጊያ መርሃግብር የእናቶች ቀን በሆነው የግንቦት ወር መጀመሪያ በሚካሄድ ደማቅ ስነ ስርዓት ይፋ እንደሚሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
ከእስራ አንድ አመታት በፊት በአስራ አንድ እንስት ባለራዕዮች ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው እናት ባንክ በመላ ሃገሪቱ “እማዬ” ቅርንጫፍ ሳይጨምር 206 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ለሃገርና ለወገን በጎ የዋሉ ብሎም አሻራቸውን ያሳረፉና ዝናን ባተረፉ እንስቶች ስም ሲሰይም ቆይቷል፡፡
«እማዬ» የተሰኘ የእናት ባንክ ትርንጫፍ ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ መታስቢያ ሃውልት አጠገብ ተከፈተ

