ክሳቸውን በፕላዝማ እንዲከታተሉ ጠየቁ
ከጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች በተለይ ከዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ ክሱን የመሠረተው የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡
ከአንድ ሺሕ በላይ በሆነ ገጽ ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸው አቶ በከረትና አቶ ታደሰ፣ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሲጣራና በባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ የከረመ ቢሆንም፣ አቶ በረከት የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣን የነበሩ በመሆናቸው ምክንያት ክስ የተመሠረተባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በመሆኑም ክሱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውክልና ያለውና ክሱን ሊያይ የሚችለው፣ የክልሉ አቻ ፍርድ ቤት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሆኑ ክሱ ሊቀርብ ችሏል፡፡
የክሱ ዝርዝር የደረሳቸው አቶ በረከትና አቶ ታደሰ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ፣ ክሱ ብዙ ገጽ ያለው መሆኑን ተናግረው በአግባቡ አንብበውና ተገንዝበው ምላሽ እንዲሰጡ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ክሳቸውን ጠበቃ አቁመው መከራከር ስላልቻሉ በውጭ ጠበቃ አቁመው እንዲከራከርላቸውና እነሱም ክርክሩን በፕላዝማ እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ የማይፈቀድላቸው ከሆነም የሕግ አማካሪ ባለሙያ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠበቃ እንዲቆምላቸው የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብርና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ትዕዛዝ በመስጠት፣ ክሱን አንብበው መቃወሚያ ሐሳብ ካላቸው ለመስማት ለሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡