‹ እኔ ዘፋኝ ነኝ፤ የተከበረ ሞያዬ ነው፤ ማንም አቁሚ ብሎኝ የማቆመው ሙያ አይደለም፤› የዓመቱ ምርጥ አርቲስት ቬሮኒካ አዳነ

ታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት ዘፋኝ እና ሙዚቀኛ አርቲስት ቬሮኒካ አዳነ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ስኬታማ ስራዎችን የሰራችበትና ከፍተኛ እውቅና ያገኘችበት ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን እያሳየች በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ ካሉ ወጣት አርቲስቶች መሀከል አንዷ የሆነችው ቬሮኒካ ላለፉት ሶስት ዓመታት የለፋችበትን የመጀመሪያዋን ‹መጠሪያዬ› ስትል የሰየመችውን አልበሟ ካወጣች በኋላ በአፍሪካ መድረክ ላይ እንደ ኮከብ ስታበራ ታይታለች፡፡

ቬሮኒካ አዳነ በሙዚቃው ዘርፍ ከተሰማራች አመታትን ያስቆጠረች ብትሆንም  ከአድማጮች ጋር ስትገናኝ የነበረው በተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ሆኖ ቆይቷል፡፡ የራሷንና የሌሎች ተወዳጅ ድምፃውያን ዘፈኖች በማቀንቀን  ለኢትዮጵያንና  ከሀገር ውጪ ባሉ አድናቂዎቿ ዘንድ አድናቆትን አትርፋለች፡፡

እንደ ‹ካንተ ሌላ፣ እናነይ፣ ተናገር እና አበባዬ› ባሉ ታዋቂ ዜማዎቿ ከፍተኛ እውቅና አግኝታለች። የቬሮኒካ  ሙዚቃዎች ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያ ሙዚቃ  አጫዋች ዲጄዎች ዝርዝሮች እና ገበታዎች ላይ  በሰፊው የሚጋበዝ ስራ ነው፡፡ ‹ይህም ሰፊ ተወዳጅነትን ያሳያል።› ሲል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ቬሮኒካ ክህሎቷንና ጥበባዊ እድገቷን የሚያሳይ ሙሉ አልበሟን ካወጣች በኋላ በመላው ዓለም የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ለማሳየት ጉዞ አድርጋለች፡፡ የሙዚቃ ኮንሰርቶቿ ትኬቶች ከትርኢቱ ቀን በፊት በአብዛኛውን ተሸጠው ያለቁ ሲሆን የውጭ ሀገር ሙዚቃ አፍቃሪያን ሳይቀሩ የኮንሰርቶቿ ታዳሚያን መሆናቸው ታይቷል፡፡

ቅድመ ህይወት እና ዳራ

ቬሮኒካ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ከሙዚቃ ቤተሰብ የተገኘችው ቬሮኒካ  አባቷ አርቲስት አዳነ ተካ ታዋቂ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቀኛ ነው፣ ይህም ከሙዚቃ እና አፈጻጸም ጋር በነበራት ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ቬሮኒካ ወደ ሙዚቃ የመሳብ ዕድል ያገኘችው በአባቷ ብቻ አይደለም፡፡ ቤተዘመዶቿ ጭምር ለሙዚቃ  ጥበብ ቅርብ ናቸው ሊባል ይችላል፡፡ የአባቷ ታናሽ እህት ማለፊያ ተካ እንደ ወንድሟ የተዋጣላት ድምፃዊ ስትሆን በአርቲስት የሺእመቤት ዱባለ የሚመራው የእርጎዬዎች ቤተሰብ ለእነ አዳነ የቅርብ ዘመድ ነው፡፡

የጥበብ ቤተሰብ

ቬሮኒካ ወትሮም የጥበብ ቤተሰብ ልጅ ስለሆነች ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባትና ስሜቷን ለመግልፅ አልተቸገረችም፡፡ አባቷ አርቲስት አዳነ ተካ ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በማሲንቆ ጨዋታውና በአዝማሪነቱ እውቅናን በአጭር ጊዜ የተቀዳጀ አርቲስት ነው፡፡ በተለይም እዛው መድረክ ላይ ቆሞ ከሚያየውና ከሚታዘበው ነገር ተነስቶ የሚገጥማቸው የአዝማሪ ግጥሞች ብዙዎችን የሚያዝናኑን የሚያስፈግጉ ናቸው፡፡

ታናሽ እህቱ ማለፊያ ተካም እንደ አዳነ ሁሉ በአዝማሪነትና በባህል ሙዚቃ ተጫዋችነት በርካታ ዘፈኖችን የተጫወተች አርቲስት ናት፡፡ ሁለቱ አርቲስቶች በሙዚቃ ጥበብ ተስበው ትምህርታቸውን አቋርጠው  ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ የመጡት  ገና የአስራዎቹ ቤት ታዳጊ እያሉ ነው ፡፡ ገና ጉልበታቸው ሳይፀና ለበለጋነት እድሜያቸው  ለቤት ወጪና ለአንዳንድ ነገሮች መግዢያ የተሰጣቸውን ገንዘብ ይዘው ወደ አዲስ አበባ መሳፈሪያ አድርገው የመጡት አዳነና ማለፊያ እሱ ድምፅንና ማሲንቆ መጫወቱን እሷ ደግሞ የአዳነ ተቀባይ ሆና ድምፃቸውን ተማምነው ነበር ፡፡ አዲስ አበባ እንዳሰቡት እጇን ዘርግታ ባትቀበላቸውም ኑሮን ለመጋፈጥ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው በመስራት በፅናት ታግለዋል፡፡ እርግጥ ከእነርሱ በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የሙዚቃ ስራ የጀመሩት የአክስቶቻቸው ልጆች እርጎዬዎችን አግኝተው የተሻለ ስራ ለመስራት ተስፋ ቢያደርጉም ነገሮች እንዳሰቡት አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም፡፡ ያም ሆኖ አዳነና ማለፊያ እየተቀባበሉ በሚሰሩባቸው ቦታዎች ደሞዝ ባያገኙም ሽልማቱ ግን ‹ኑሯችንን ይደጉም ነበር› ይላሉ የዛሬ ሃያ ዓመት በጋራ ለቁም ነገር መፅሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ፡፡

በልጅነታቸው ከሀገራቸው ወጥተው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ ስለሚያሳልፉ እንደ እድሜ እኩዮቻቸው በትምህርታቸው ለመግፋት አልቻሉም፡፡ ያም ሆኖ ግን አዳነ በራሱ ጥረት አማርኛን ብቻ ሳይሆን እንግሊዝኛንም ቆጥሮ በማንበብ መግባባት የሚችልበትን ችሎታ አዳብሯል፡፡ በስራ አጋጣሚም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሲሄድ ለመግባባትና ፈረንጆችን ጭምር ለማሳቅ እንደማይቸግረው ይናገራል፡፡

አዳነና ማለፊያ ‹ይወዳል› የተባለ ተወዳጅ የባህል ምሽት ቤት ካሳንቺስ ከፍተው ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል፡፡ የካሴት ስራዎቻቸውን በግልና በጋራ ለህዝብ ማድረስ እስኪጀምሩም ድረስ በጋራ ብዙ መድረኮች ላይ ሰርተዋል፡፡  አዳነና ማለፊያ ለረጅም ጊዜያት አብረው በሙዚቃ ስራ ላይ ሲሰሩ  ሁለቱም የስፖርት ወዳጆች መሆናቸውን ሳይሸሽጉ ነው፡፡ ነገር ግን  በሚደግፏቸው ክለቦች ይለያያሉ፡፡ አዳነ ከሀገር ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ሲሆን ማለፊያ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ናት፡፡ አዳነ በማንችስተር ዩናይትድ ቀልድ እንደማያውቅ ሲናገር  ማለፊያ ደግሞ የአርሰናል ነገር አይሆንላትም፡፡ በቤተሰባዊ አቋማቸው አዳነ የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆን ማለፊያ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናት፡፡ አዳነ ሙሉ እድሜውን በሙዚቃ ስራ ላይ ያሳለፈ ቢሆንም የመጀመሪያ ልጁ ቬሮኒካ አዳነ ወደ ሙዚቃ ሙያ ስታዘነብል ‹ተይ› ሊላት አልፈለገም፡፡ እንደውም ከትምህርቷ ጎን ለጎን የሙዚቃ ስራዎችን እንድትሰራ በማበረታታ አሁን ለደረሰችብት ደረጃ የአንደበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ቬሮነካ በተለያ መድርኮች ላይ የምትናገረው እውነት ነው፡፡ ቬሮኒካ በጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለት ሲሆን በተማረችው ትምህርት የመስራት ፍላጎት እንዳለት በተደጋጋሚ ተናግራለች፡፡

ቬሮኒካ ገና በለጋ እድሜዋ ነው  መዘመር የጀመረችው፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዋም  ትርኢት በማቅረብ እና የእጅ ሥራዋን በማሳየት ወደ ሙያዊ የሙዚቃ ትዕይንት መግባቷ እንደ አባቷ የስኬትን መንገድ እንድትከተል በር ከፍቶላታል፡፡ የቬሮኒካ ዝነኛ መሆን የጀመረችው በዘፈኖቿ  ብቻ ሳይሆን አይን ገብ በሆነው የፋሽን ተከታይነቷና ደም ግባቷ ነው፡፡ ቀደም ሲል በለቀቀቻቸው ነጠላ ዜማዎች ላይ በምታሳየው የመድረክ ውዝዋዜና ስታይል የብዙዎች መነጋገሪያነቷን አሳይታለች፡፡ ይህም ድምጿን እና ስሜታዊ አቀራረቧን በማሳየት ታማኝ ተከታዮችን በፍጥነት ለመገንባት አስችሏታል።

ባለፉት አመታት፣ አበባዬ፣ ካንተ ሌላ፣ ተው፣ ኩርፊያ እና ሌሎችም በመላ ኢትዮጵያ እና በዲያስፖራዎች ዘንድ በስፋት የተሰሙ ዘፈኖቿ ናቸው። የቬሮኒካ  ዘፈኖች በተለምዶ የኢትዮጵያን ቅንቶች  ከባህላዊ ዜማዎች እና ዘመናዊ ፕሮዳክሽን ጋር ተዋህደው የሚደመጡ መሆናቸውን የሙዚቃ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡ ይህም የተለያዩ ድምፆችን ማጣጣም ለሚፈልጉ የሙዚቃ አድማጮችን ቀልብ የሚስብ ነው፡፡ የቬሮኒካ ሙዚቃ በስሜት የሚነዝሩ በመሆናቸው  በትውልዶች ውስጥ የማስተጋባት ችሎታ ፈጥሯል።

የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ

የቬሮኒካ ተጽእኖ በሙዚቃው ኣለም ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ተዘርግቷል፡፡ እሷን የሚመለከቱ መረጃዎችን በፍጥነትና በትጋት በማጋራት ጠንካራ ተሳትፎዋን ታሳያለች፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን ራሷንና ስራዋን ለማስተዋወቅ ከመጠቀሟም በላይ ሰዎችን ለመርዳትና ችግራቸውን ለመጋራት እንደ አንድ የግንኙነት መድረክ ስትጠቀምበት ይታያል፡፡  ከ800 ሺህ በላይ ተከታይ ያላት ቬሮኒካ  ለሽልማት የሚያበቃትን ቅስቀሳም በተደጋጋሚ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመቅረብ ተጠቅማበታለች፡፡እናም በኢትዮጵያ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሙዚቀኛ እና የባህል ሰው ተደርጋ ትጠቀሳለች፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሙዚቃ ስረሳዎቿንም ሆነ የማስታወቂያ ስራዎችን ፖስት ባደረገች በሰዓታት ውስስ በርካታ ምላሽ የምታገኘው ቬሮኒካ አብአዛኛዎቹ አድናቂዎች በሆኑበት ምላሻቸው መሀከል ቀላል የማይባሉ ትችቶችና ጎነጥ የሚያደርጉ አስተያየቶችን ታስተናግዳለች፡፡ በአንድ ወቅት በእጇላይ የቅድስት ድንግል ማርያምን ምስል መነቀሷን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የነበረው ውዝግብ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ቬሮኒካ ግን በአቋሟ በመፅናት የልጅነት ህልሟን ያሳካችበት አጋጣሚ መሆኑን በመግለፅ የምታደርገውን የምታውቅ ጠንካራ ሴት መሆኗን እንዲህ ስትል ነበር የተከላከለችው፡፡

‹ እኔ ዘፋኝ ነኝ፤ አምኜ ተቀብየው ብዙ ቤተሰብ የማስተዳድርበት የተከበረ ሞያዬ ነው፤ ማንም አቁሚ ብሎኝ የማቆመው ሳይሆን እሱ በቸርነቱ በቃሽ ሲለኝ የማቆመው ጉዳይ ነው የዛኔ እንኳን ሙያዬን፤ ዓለምን ክጄም ልመንን እችላለሁ፤ እኔ እና ፈጣሪ ያለንን ንግግር ሰምታችሁ አታውቁም፤ እኔ እምነቴ ላይ ያለኝን ጥንካሬም አታውቁም፤ ሁሌ ፈጣሪዬን ተንበርክኬ የምጠይቀውን ጥያቄም አታውቁም፤ ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ እያለ እኮ ውሎው ከፃድቃን ጋር አልነበረም፤ ልክ እንደ አንዳንዶቹ ምን ሁኖ ነው ከሀፅያን ጋር የሚውለው ጥያቄያቸውም ነበር፤ የእመቤቴን የቅድስት ድንግል ማርያም ንቅሳት መነቀስ የዘመናት ህልሜ ነበር ማለት፤ መነቀስ አቅቶኝ ነበር ማለት ሳይሆን ልነቀሳት ወይስ አልነቀሳት የሚለው ጥያቄ ውስጥ ለዘመናት ነበርኩ ማለት ነው፤ መነቀሴ ልክ ነበር በጣም ደስተኛም ነኝ፤ የትም ብሆን ድሮም አብራኝ ነች አሁን ደግም በይበልጥ ይሰማኛል፤ (አንዳንዶቻችሁ) ልታደርግ ትችላለች ብላችሁ ያሰባችዋቸው አፀያፊ ተግባሮች፤ ትላንት ከእናንተ ገና ሰማሁት፤ እንምታስቡትም በዚ ልክ የወረድኩ ሴት አይደለሁም፤ ልኬን የማውቅ ነኝ፡፡ አሁን ደግሞ በይበልጥ ራሴን እንዳከብር እና ከብዙ ነገር እንድቆጠብ ትረዳኛለች፤ ለሰው እማ ቢሆን አልነቀሳትም ነበር፤ ማንም ምንም ቢል፤ እሷን በመነቀሴ ደስተኛ ነኝ፡፡›

ይህም ቬሮኒካ አዳነን በድምፅ ተሰጥኦዋ ብቻ ሳይሆን በመድረክ  ተፅእኖዋ የተከበረች ግንባር ቀደም የሙዚቃ አርቲስት አድርጓታል፡፡ ከመጀመሪያዋ አዲስ አልበም ጀምሮ እስከ አለም አቀፍ እውቅና እና ሽልማቶች ድረስ ስራዋ  ጥበባዊ እድገት አሳይቷል፡፡ እናም በኢትዮጵያውያን አርቲስቶች በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ የመታየት ዕድልን ያሰፋች መሆኑን ያሳያል። ቬሮኒካ አዳነ የመጀመሪያዋ አልበሟን ‘’መጠሪያዬ’’ የተሰኘውን አልበሟን ባጋራችበት በዩቲዩብ  ላይ ከ32 ሚሊዮን በላይ ጉልህ ተመልካች ማግኘት እላለች፡፡ ለዚህም አድናቂዎቿን አመስግና አትጠግብም፡፡

ተወዳጇ  ድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ፣ “ካንተ ሌላ” በተሰኘው ስራዋ  ደግሞ በአህጉሪቱ ከሚገኙ ታላላቅ የሙዚቃ ሽልማቶች አንዱ በሆነው የአፍሪማ የሙዚቃ አዋርድ መድረክ ላይ መሸለሟ ለመላው የሙዚቃ አፍቃሪ ኩራት ነው፡፡ የዘንድሮው የሽልማት መሪ ቃል “ወደ ስራችን እንመለስ!” (ወደ መሰረታችን እንመለስ!) (Back to the roots!) የሚል ሲሆን፣ የንጹህ ባህላዊ ቅኝቶችን በማቅረብ ባህላቸውን በህይወት እንዲቆይ የሚያደርጉ አርቲስቶችን እውቅና መስጠትን አላማው አድርጓል። የቬሮኒካ ተፎካካሪዎች፦ በዚህ ምድብ ውስጥ ከቬሮኒካ አዳነ ጋር ታጭተው የነበሩት ታዋቂ የአፍሪካ አርቲስቶች የሚከተሉት ናቸው፦

  • ቢግ ዙሉ – ን’ሳለ ኖባኒ (ደቡብ አፍሪካ)
  • ሺሪን ላጅሚ – ኤሼህ ኤሼህ (ቱኒዚያ)
  • ሌዲ ፖንስ – ዤ ቮ ዳንሰ (ካሜሩን)
  • ላማ ሽሬፍ – ጃየክ ላህሴብ (ቱኒዚያ)
  • ላሪ ጋጋ, ፍሌቨር እና ንግስት ቴሬዛ ኦኑራ – ኦቦዶ (ናይጄሪያ)
  • ሶና ታታ – ናይናይ ባና (ጊኒ)
  • ስቶንቦይ – ጄጄሬጄ (ጋና)
  • ቲናሪዌን – አሞስ ኢድጅራው (ማሊ)
  • ቶንቶን ፓል እና ቢንጊኒ ባካጋ – ኩሮን (ማሊ) ናቸው፡፡ የቬሮኒካ አዳነ በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ መሸለም የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በአህጉሪቱ ያለውን ተጽዕኖ በድጋሚ ያሳየ ሲሆን፣ በብዙ አድናቂዎቿ ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል።

የቬሮኒካ አዳነ አዲስ የድል ጉዞ በታንዛኒያ!

ቬሮኒካ  በቅርቡ በታንዛኒያ በተካሄደው “2025 Zikomo Africa Awards” በ2025 በዚኮሞ አፍሪካ ሽልማት ላይ በተለያዩ ዘርፎች የተሸለመች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አርቲስት በመሆን ታሪክ ሰርታለች፤ ከዚህም ሌላ  በ‹ካንተ ሌላ› ዜማ የዓመቱ ምርጥ ሴት አርቲስት እና የአመቱ ምርጥ ዘፈን ሽልማትን ተቀዳጅታለች፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ትልቅ አህጉራዊ ስኬት ነው። በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ንግግር ያደረገችው ቬሮኒካ ‹በጣም ደስ ብሎኛል፤ ለአድናቂዎቼና ድምፅ ለሰጣችሁኝ በሙሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አባቴን በጣም እወድሃለሁ› ስትል ተናግራለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ያለ እናት ያሳደጋትን አባቷን አዳነ ተካን በየመድረኩ አመስግና የማትረካው ቬሮኒካ ይህ አህጉራዊ ስኬት የአባቷም እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ለዚኮሞ ሽልማት ስነስርዓቱ ዳሬሰላም የገባችው ቬሮኒካ  በሽልማት መድረኩ ላይ ድንቅ ስራዎቿን በማቅረብ ዓለም አቀፋዊ ሙዚቃ በመጫወት ኢትዮጵያውያንን አስተዋውቃበታለች፡፡ ይህ  የቬሮኒካን የጥበብ ትጋት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በምስራቅ አፍሪካ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

የበጎ አድራጎት ስራዎች

ቬሮኒካ በሙዚቃ ስራዎቿ ብቻ ሳይሆን በተለያ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ አገልግሎቷን ስትወጣ ትታያለች፡፡ነቢች የተባለ የፊስ ቡክ ፀሐፊ የቬሮኒካ አዳነን የበጎአድራጎት ስራዎች በዝርዝር ተመልክቶታል፡፡ እንደ አብነትም ጎንደር ላይ በደረሰዉ አደጋም የ 500 ሺ ብር ድጋፍ ስታደርግ በመቄዶንያ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይም በመገኘት 8,000,000 ብር ገቢ አድርጋለች፡፡  በተለያዩ ት/ቤቶች እና ቦታዎች ለወጣቶች ምክር የምትለግሰው ቬሮኒካ  ወይ ጁቴ የተሰኘው የወጣቶች ሙዚቃ ሲዘጋጅና አብራቸው እንድትዘፍን ስትጠየቅ  ታዋቂ ነኝ ብላ ፊቷን ሳታዞር አብራቸው ተጫውታለች፡፡   በ Zojak Worldwide OFFICIAL Youtube Channel ዘፈኑ ሲለቀቅም ቪድዮ ላይ በመገኘት ብቻ ሳይሆን ከZojak ጋር በማገናኘት የሚገርም ክፍያ ተከፍሏቸው እንዲሸጡት ማድረጓ የልብ ቅንነቷን ያሳያል፡፡  ከዚህ ሌላም በማህበራዊ ሚዲያ ፕላት ፎርሟ ላይ ለተለያዩ ሰዎች እርዳታ አድርጋለች፡፡ ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ነጻ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ተሳትፋለች፡፡ ማዕዶተ ኢትዮጵያ የዝማሬ መርሐግብር ላይ 800 ሺ ብር ገቢ አድርጋለች፡፡

ቬሮኒካ ከአልበሟ መውጣት በኋላ  በአውሮፓ ጉብኝቷ ወቅት በዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ፤ ፍራንክፈርት፤ስቶኮሆልምና በአሜሪካ የተለያዩ ስቴቶች አስደማሚ  ትዕይንቶችን በማሳየት ከኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ማህበረሰቦች እና ሰፊ ታዳሚዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖዋን አሳይታለች።

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe