ኦማር ሀሰን አልበሽር ፈንቅለው ወጥተው፣ ተፈንቅለው የወረዱ መሪ

 

ኦማር ሀሰን አልበሽር ፈንቅለው ወጥተው፣ ተፈንቅለው የወረዱ መሪ

በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው አለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ይፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ከአህጉረ አፍሪካ ለመውጣት ሲቸገሩ ነበር፡፡ ሱዳንን ለ30 ዓመታት ያክል መርተዋል፡፡ ኦማር ሀሰን አልበሽር ከዛሬ 30 ዓመታ በፊት ወደስልጣን በመጡበት መንገድ ከስልጣናቸው ወርደዋል፡፡ የስልጣናቸው መጀመሪያ እና መጨረሻ ተመሳሳይ እና ድራማዊ ሆኗል። በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የወጡበትን ዙፋን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተነጥቀዋል።

ለረጅም ጊዜያት የቆየውና በዳቦ እጥረት ምክንያት የተነሳው የሱዳናውያን አመጽ ፕሬዚዳንት አልበሽርን ከስልጣን እስከማውረድ ደርሷል፡፡ ከሳምንታት በፊት ምሳ ሰዓት ገደማ ነበር የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር አዋድ አብን በሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው፤ የኦማር አልበሽር አገዛዝ አክትሟል፤ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ወታደራዊ መንግሥትም ተመሥርቷል፤ ሲሉ አዋጅ ያሰሙት። ሱዳን ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንደምትተዳደርም ነው ሚኒስትሩ ቆፍጠን ባለ ንግግራቸው ያሳወቁት። አክለውም፤ አል-ባሽር በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ «ደህንነቱ በተጠበቀ ሥፍራም ይቆያሉ» ሲሉ ዜናውን አሰሙ። አሁን አልበሽር በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

የሰውዬው መኖሪያ ከሰሞኑ ሲፈተሽ ብዙ ጥሬ ገንዘብ ተገኝቷል፡፡ ስድስት ሚሊዮን ዩሮ፣ አምስት ሚሊየን የሱዳን ፓውንድ እና ከ351 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ በሻንጣ ታጭቆ ተገኝቷል፡፡ ይህም አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡

‹ወንጀለኛው›

አልበሽር የመሯት ሱዳን የተረጋጋ ፖለቲካ ኖሯት አያውቅም፡፡ ጦርነት ሁሌም ነበር። በአውሮፓውያኑ 1989፡፡ ኦማር ሀሰን አልበሽር በጊዜው በቆዳ ስፋቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ የነበረችውን ሱዳን ለማስተዳደር መንበሩን በመፈንቅለ መንግስት ተቆጣጠሩት። በጊዜው ኮሎኔል የነበሩት አልበሽር ጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አልማሃዲን ከዙፋኑ አውርደው ነበር በቦታው የተተኩት፡፡ ሰውዬው ወደ ሥልጣን ሲወጡ በደቡባዊ እና ሰሜናዊ ሱዳናውያን መካከል በተከሰተ የእርስ በርስ ጦርነት ሃገሪቱ ትታመስ ነበር።

ሱዳን በአልበሽር አገዛዝ መባቻ ግድም የተረጋጋች ብትመስልም ግጭቱ እንደ አዲስ አገረሸ፤ አልበሽርም ዳርፉር አካባቢ ከባድ የጦር ኃይል ተጠቅመዋል ተብለው ተወቀሱ። ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አልበሽር የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅመዋልና እፈልጋቸዋለሁ ሲል ለፈፈ።

እንዲያም ሆኖ ግን ጫና የበረታባቸው አልበሽር በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2015 የተደረጉ ምርጫዎችን አሸንፈው መንበራቸው ላይ ተደላደሉ። በአይሲሲ የእሥር ማዘዣ የወጣባቸው አልበሽር ከሃገራቸው ውጭ በተገኙበት የካቴና ሲሳይ እንዲሆኑ ተወሰነባቸው፡፡ በዚህ ሳቢያ ወደአውሮፓ ሃገራት ከመጓዝ ተቆጠቡ፡፡ ወደ ግብፅ፣ ሳዑዲ አራቢያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪቃ ከመሄድ ግን ያገዳቸው አልተገኘም።

ወርሃ ሰኔ 2015 ላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሳሉ ሊያዙ መሆናቸውን የሰሙት አልበሽር ሹልክ ብለው ወጡ፡፡ በጊዜው የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ነበር፡፡

አልበሽር የዳርፉር፣ ማሳሊት እና ዛጋዋ ብሔር ተወላጆችን አስገድለዋል፤ በቡድኖቹ አባላት ላይ አካላዊና አእምሯዊ ቀውስ አድርሰዋል፤ የተጠቀሱት ብሔር ተወላጆች የተጎሳቆለ ኑሮ እንዲኖሩ ሆን ብለው አስደርገዋል፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል፤ ከሃገር ማባረር፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል፣ ማሰቃዬትና የጦር ወንጀል ፈጽመዋል፤ እንዲፈጸምም አድርገዋል ተብለው ይከሰሳሉ፡፡ የዳርፉር ነዋሪዎች ላይ በከተሞች እና በመንደሮች ውድመትና ዝርፊያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውም ይነሳል፡፡ አልበሽር ባያምኑም ዳርፉር ላይ ብቻ ከ200 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚደርሱ ሱዳናውያን ሞተዋል፡፡ 2.5 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ተሰደዋል፡፡ አብዛኞቹ ወደኢትዮጵያ የገቡ ናቸው፡፡

‹ጦረኛው ገንጣይ›

አልበሽር ሥልጣን ከመቆናጠጣቸው በፊት ወታደራዊ አዛዥ ነበሩ፤ ኅላፊነታቸው ደግሞ በጆን ጋራንግ የሚመራውን በደቡብ በኩል የሚንቀሳሰቀሰውን አማፂ ቡድን መዋጋት። ባሽር ፕሬዝደንት ከሆኑ በኋላ ከጋራንግ ጋር እርቅ ቢያወርዱም ሙሉ ሰላም ሊሰፍን ግን አልቻለም። አልፎም ደቡብ ሱዳናውያን ‘የእንገንጠል’ ጥያቄ አቀረቡ።

2011 ላይ በተካሄደ ሕዝበ-ውሳኔ 99 በመቶ ያክል ደቡብ ሱዳናውያን ‘የእንገንጠል’ ጥያቄውን ደግፈው ድምፅ ሰጡ። ከስድስት ወራት በኋላ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን በይፋ ተለያዩ።

ምንም እንኳ ደቡብ ሱዳን ተገንጥላ ራሷን ብትችልም አልበሽር በዳርፉር ጉዳይ አሁንም ጣልቃ እየገቡ ነው ተብለው መወቀሳቸው አልቀረም፤ ምንም እንኳ እርሳቸው ክሱን ቢክዱም።

ስልጣን ቻው

በ1944 የተወለዱት ባሽር በለጋነታቸው ነበር ወደ ውትድርናው ዓለም የገቡት። ምንም ልጅ እንደሌላቸው የሚነገርላቸው ባሽር በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ ሳሉ ሁለተኛ ሚስታቸውን አገቡ። ከዚህ ውጭ ስለ አል-ባሽር የግል ሕይወት ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም።

ባሽር በ30 ዓመት የሥልጣን ዕድሜያቸው የዘንድሮውን አይነት ተቃውሞ ገጥሟቸው አያውቅም። በታህሳስ ወር ላይ በዳቦ እና ነዳጅ ዋጋ መናር ሳቢያ የተጀመረው ተቃውሞ እነሆ ባሽርን ጠልፎ ጥሏቸዋል። ከደቡብ ሱዳን መገንጠል በኋላ የሱዳን ምጣኔ ሃብት ቀጥ ብሎ ሊቆም አልቻለም፤ ምክንያቱ ደግሞ የካርቱም ነዳጅ ሦስት አራተኛው ከጁባ ጋር በመሄዱ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኑሮ መናርና ድህነት መስፋፋት ያዘ። የባሽር አገዛዝ ግን ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ ራሱን በሙስና ተጠልፎ አገኘው። ፍየል ወዲህ የሆነባቸው ባሽር ወርሃ የካቲት ላይ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳወጁ፤ ካቢኒያቸውንም እንደ አዲስ ለማዋቀር ተገደዱ፡፡ በምርጫ ያወጣኝ ሕዝብ በምርጫ ያውርደኝ ያሉት ባሽር የሽግግር ጊዜ መንግሥት አላቋቁምም፤ የ2020 ምርጫ ላይ እንገናኝ ሲሉ ተደመጡ። ተቃውሞ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ 28 ሰዎች እንደተገደሉ ዘገባዎች ያረጋግጣሉ፤ ምንም እንኳ ‘ሂውማን ራይትስ ዎች’ ቁጥሩ ከዚያ በላይ ነው ቢልም።

አልበሽር ለሰላሳ ዓመታት ከተቆናጠጡት መንበር በግዴታ ወርደዋል፤ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥትም ተመሥርቷል። የአልበሽር ሥልጣን ግብዓተ-መሬት ሱዳናውያንን ቢያስፈነድቅም ነገ ላይ ስለሚሆነው ነገር ግን ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe