‹ኦኤም ኤን እስከዛሬ ድረስ ውሸት አስተላልፎ አያውቅም፤› የኦኤምኤን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ጉተማ

አቶ ግርማ ጉተማ
‹ለተመልካቾቻችንም ክብር መስጠት ስላለብን በኢሳት ላይ ስለሚባሉ ጉዳዮች ሁሉ መልስ አንሰጥም›
‹እኛ የግለሰቦችን ሀሳብ ለምን አላፈናችሁም በሚል የሚከሰን ካለ ራሳችንን በዚህ ረገድ ለመከላከል ዝግጁ ነን›
ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሀከል አንዱ የሆነው ኦኤም ኤን ራሱን ከትግል ሚዲያነት ወደ መደበኛ መገናኛ ብዙሃንንት ለመቀየር እየሰራ መሆኑ ይናገራል፤ የኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ዳይሬክተር የሆነው አቶ ለግርማ ጉተማ የትኛውም ሚዲያ ደፍሮ የማያነሳቸውን ሀሳቦች በግልጽ ለህዝብ በማቅረብ በኩል የተሳካ ስራ እየሰሩ ስለመሆናቸው ይናገራል፤ በአቶ ጃዋር መሐመድ ተመስርቶ ሲንቀሳቀስ የቆየው ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ምንም እንኳ ጃዋር ‹ባርኔጣውን ቀይሮ› ወደ ፖለቲከኝነቱ ቢገባም በቀጣዩ ምርጫ ጣቢያው የማንም ልሳን ሆኖ እንደማይሰለፍ አቶ ግርማ ያስረዳል፤ በዚህና ተያያዥ በሆኑ ወቅታዊ የሀገራችን ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ግርማ ጉተማ ጋር ቁም ነገር መፅሔት ቆይታ አድርጋለች፤
ቁም ነገር፡- ግርማ ማነው ከሚለው እንጀምር?
ግርማ ፡- ተወልጄ ያደኩት ነገሌ ቦረና ነው፤ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማርኩት እዛው ነው፤የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የተማርኩት፤
ቁም ነገር፡-በምን የትምህርት ዘርፍ?
ግርማ ፡-ፋርማ ቴክኖሎጂ ከመድሃኒት ምርምር ጋር የተያያዘ ነው፤ ሶስተኛ ዲግሪዬን በዩኒቨርሰቲ ኦፍ ኖርዌይ ገና አልጨረስኩም አሁን የመመረቂያ ፅሑፍ እየጻፍኩ ነው፤ የጥናቴ ትኩረት ከመድሃኒት ኢኮኖሚክስ ጋር የተያያዘ ነው፤ የመድሃኒቶች የዋጋ ተመጣጣኝነት እንዲሁም ተደራሽነታቸው ላይ ያተኮረ ነው፤ ከዚህ በፊት የሰራኋቸው ሶስት ፕሮጀክቶች ነበሩ ፤ ሁለቱ ታትመዋል፤ ሶስተኛውን ነው ሰፋ አድርጌ እየሰራሁ ያለሁት፤
ቁም ነገር፡- ወደ ፖለቲካው ዓለም እንዴት ገባህ፤ከትምህርት ጋር ራቅ ያለ ነው ?
ግርማ ፡-ልክ ነህ፤ ትምህርቱ የተፈጥሮ ሳይንስ ነው፤ከልጅነቴ ጀምሮ የተወለድኩበትና ያደኩበት አካባቢ የትግል አካባቢ ነበር፤ የኦሮሞ መብት ታጋዮችን በቅርብ አይ ነበር፤ በጣም ጠንካራ ትግል የነበረበት ጊዜ ነበር፤ትምህርት ቤት እያለን የትምህርተ ቤቱ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ አንዳንድ ነገሮችን እንሰራ ነበር፤በዚህ የተነሳ ወደ ፖለቲካው ተስቤያለሁ፤ እርግጥ ሰፋ ያለ ንባብም አድርጌያለሁ፤ከመደበኛው ትምህርቴ ውጭ ስለ ፖለቲካው ሰፋ ያለ ንባብ አድርጌያለሁ፤
ቁም ነገር፡- ወደ ኦኤም ኤን ሀላፊነት ከመምጣትህ በፊት የት ሰርተሃል?
ግርማ ፡-ውጭ ሀገር ነበር የነበርኩት፤ እዛ ደግሞ በትምህርት ላይ ነበርኩ፤
ቁም ነገር፡-ከጃዋር ጋር እንደት ተገናኛችሁና ወደ ኦኤም ኤን ዳይሬክተርነት መጣህ?
ግርማ ፡-ኢኤም ኤን የአክቲቪስት ሚዲያ ማላት የትግል ሚዲያ ነበር፤አክቲቪስትነቱ ውስጥ ስላለሁበት ውጭ ሀገር እያለሁ በኦኤምኤን ላይ እሳተፍ ነበር፤ራባዶሪ የሚባል ፕሮግራም ነበር ፤ አሁንም አለ በእርግጥ የምሁራን ውይይት የሚደረግበት ፕሮግራም ላይ በስካይፕ እንወያይ ነበር፤ያንን ፕሮግራም ካቋቋሙ ስድስት ሰዎች መሀከል አንዱ ነኝ፤በእዛ ፕሮግራም ላይ ዓላማችን ምን ነበር? የቄሮ እንቅስቃሴ የዛን ጊዜ ከፍተኛ ነበር፤ቄሮ የሚባሉት ከእኛ እድሜ በታች ያሉ ያላገቡ ወጣቶች ናቸው፤ እኛ ከፍ ያልነው ከ32 እስከ 40 ኣመት ዕድሜ ያለው ራባዶሪ ነው የሚባለው በኦሮሞ ባህል፤ስለዚህ ቄሮዎችን እንደ እኛ ታናናሾች ነው የምናያቸውና ምክር የምንለግሳቸው፤ታላላቆቻቸው ስለነበርን ይሰሙናል፤ ምሁራዊ አስተያየት እየሰጠን በውይይታችን ጋይድ እናደርጋቸው ነበር፡፡
ቁም ነገር፡-ማን ነበር ፕሮግራሙን የሚያዘጋጀው?
ግርማ ፡-የእኛ የምሁራኑ ነው እንጂ የኦኤምኤን አይደለም፡፡ የተለያዩ ሀገራት ውስጥ ያለውን ስድስት ሰዎችን ነበርን ብዙ ጊዜ የምንወያይበት፤በአካል ባንገናኝም ባለንበት ሆነን እንወያይ ነበር፡፡ ኢኤምኤን መድረኩን ነበር የሰጠን፡፡ በዚህ ሳቢያ ነው ከኦኤም ኤን ጋር የተገናኘሁትና መስራት የጀመርኩት፡፡በፕሮግራሙ ላይ ከፍ ከፍ ያሉ ሀሳቦች ይቀርቡ ስለነበር የተሳካ ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡
ቁም ነገር፡-ኦኤም ኤን የትግል ሚዲያ እንደሆነ ተናግረሃል፤ ትግሉን አሳክቷል ብለህ ታምናለህ?
ግርማ ፡-ትግሉን አሳክቷል አላሳካም ወደሚለው ክርክር መግባት አልፈልግም፤ ግን ትግሉን አንድ እርምጃ ወደ ፊት ወስዶታል ለማለት እችላላሁ፡፡የኦሮሞ ትግል የኦሮሞ ፖርቲዎች ትግል ሆኖ ለነበር ለረዥም ዓመታት የቆየው ፤ አሁን ግን ትግሉን ከፖርቲ አውጥቶ የህዝቡ ትግል አድርጎታል ኦኤምኤን፤ወደ ህዝቡ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ ትግሉ ተሳክቷል አልተሳካም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝቡ ትግሉን የእኔ ብሎ እንዲይዘው አድርጎታል፤
ቁም ነገር፡-አሁንስ ኦኤምኤን ምን አይነት ሚዲያ ነው?
ግርማ ፡-አሁን የአክቲቪስት ሚዲያ ሳይሆን በጋዜጠኝነት መርህ መሰረት ለመስራት የሚመራ ሚዲያ ለማድረግ ነው እየሰራን ያለነው፤አቅጣጫችን አሁን ተቀይሯል፤ አቅጣጫ ስልህ የትግል አቅጣጫችን የፖለቲካ ትግል ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ፤ ሁሉንም እያወጣን የህዝቡ ኑሮ እንዲሻሻልና ልማቱ እንዲፋጠን የራሳችንን በጎ አስተዋፅኦ እናደርጋላን ብለን እናምናለን፤
ቁም ነገር፡-ኦኤምኤን ከምስረታው ጀምሮ ጥያቄ የሚሰነሳበት ሚዲያ ነው፤ ቀድም ሲል የተቋቋማችሁት እንዴት ና በማነው? አሁንስ ባለቤቱ ማነው?
ግርማ ፡-ኦኤም ኤን የህዝብ ሚዲያ ነው፤ በፊት ውጭ ሀገር ያሉ የኦሮሞ ዲያስፖራዎች ገንዘባቸውን አዋጥተው ያቋቋሙት ሚዲያ ነው፡፡አሁንም የህዝብ ሚዲያ ሆኖ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፤ ግን ቅርፁ እንዲቀየር እንፈልጋለን፤
ቁም ነገር፡-እንዴት?
ግርማ ፡-ለምሳሌ ኦኤምኤን ውጭ ሀገር አሜሪካ ሀገር በነበረበት ወቅት በሜኖሶታ ህግ መሠረት የበጎ አድራጎት ማህበር ሆኖ ነበር የተመዘገበው፡፡ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሆኖ ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ከህዝብ የምናገኘውን ማንኛውንም ገንዘብ ኦዲት እናስደርግ ነበር፡፡አሁን እዚህ ሀገር ስንገባ በተመሳሳይ መልክ ለመቀጠል ስለሚከብድ ወደ ንግድ ድርጅትነት ተቀይረን ነው ፈቃድ ያወጣነው፤ ይህ ማለት ህዝባዊነቱን እንዲያጣ ስለማንፈልግ በቀጣይነት ህዝብ ባለቤት እንዲሆን ወደ አክሲዮን ማህበርነት ለመቀየር እያጠናን ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ኦኤምኤን ከትግል ሚዲያነት ወደ ፕሮፌሽናል ሚዲያነት ራሱን ለመቀየር ምን ያህል እየሰራ ነው?
ግርማ ፡-አንድ ነገር ግልጽ መሆን አለበት፤ እንደማንኛውም ሚዲያ ኦኤምኤንም የራሱ ዓላማ አለው፡፡ ዓላማ የሌለው ሚዲያ የለም፤ያንን አላማውን ለማሳካት ምን ይህል ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ እየሰራ ነው የሚለው ጥያቄ ነው መጠየቅ ያለበት፤እኛ ዓላማችን ግልጽ ነው፤ኦሮሚያና ኦሮሞ ህዝብ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ምንም የምደብቀው ነገር የለም፤ ኦሮሚያ ትልቅ ክልል ነው፤አርባ፤ አርባ አምስት ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት ክልል ነው፡፡እዛ ላይ ትኩረት አድርገን ብንሰራም በእዛ ብቻ አንወሰንም፤ ሌሎች አካባቢዎችንም ለመሸፈን እንሞክራለን፤ አሁን ባለንበት ወቅት በስድስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የተለያዩ ፕሮግራችን እናሰራጫለን፤የመንግስት ሚዲያ ብቻ ይመስለኛል በዚህ ደረጃ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰራው፤ በግል የእኛን ያህል የቋንቋዎች ብዛኀነትን የሚጠቀም ሚዲያ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ ክሬዲት ሊያሰጠን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዓላማችን ግልፅ ነው ብያለሁ፤ ህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን እንደግፋለን፤
ቁም ነገር፡-ግን ፕሮፌሽናል የሆነ ስራ እንሰራለን ካልከኝ ይሄ ራሱ የፖለቲካ አቋም መያዝ ወይም መደገፍ አይሆንም?ምን ያህል ያስኬዳል?
ግርማ ፡-ህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምን እንደግፋለን ስንል ብዛሃነትን እንደግፋለን ማለቴ ነው፡፡ይሄ ህብረ ብሔራዊነት ነባራዊው የኢትዮጵያ ሁኔታን የሚያሳይ ይመስለኛል፤ መሬት ላይ ያለ እውነት ነው ማለቴ ነው፡፡ ይህንን እንደ አንድ ትልቅ እሴት ወስደን እንሰራበታልን ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡-ይህን ህብረ ብሔራዊነት የሚደግፉ የፖለቲካ ሀይሎች የመኖራቸውን ያህል ከዚህ የተለየ ስርኣተ መንግስት ነው የሚያስፈልገን ለምሳሌ አሀዳዊነት ነው የሚል በህገ መንግስቱ መሠረት የተከለከለ ሀሳብ አይደለም፤ የዚህ አይነት አቋም ያለው ፖርቲ ቢመጣ በእናንተ ሚዲያ ሀሳቡን የሚያስተላልፍበት መድረክ የማግኘት እድሉ ምን ያህል ነው?
ግርማ ፡-ለምን እድል አያገኝም? እኛ የማንቀበለው ስለሆነ ህዝብ ጋር መድረስ የለበትም ልንል አንችልም፤ ዋናው ነገር ሀሳቡን የሚገዛው ህዝብ አለ ወይ ነው ጥያቄው፤ ህብረህብሄራዊነት እኮ አሁን ህዝቡ የተቀበለው ነባራዊ እውነታ ነው፡፡ የተለየ የፖለቲካ ከአቋም የያዘ ሰው ዕድል መስጠት እኮ የመናገር ነፃነትን ማበረታታት ጭምር ስለሆነ የምንከለክልበት መንገድ የለም፤በነገራችን ላይ ለእንደዚህ አይነት አመለካካት ላላቸው ሰዎች እድሉን ስናመቻች የመናገር ነፃነታቸውን ለማክበር ያህል ብለን ነው እንጂ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል በሚል አይደለም፡፡
ቁም ነገር፡-አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የፖለቲካ ፖርቲዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች አሉ፤ ይህ ባለበት ሁኔታ መጪው ምርጫ ምን ያህል ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል ትላለህ?
ግርማ ፡-ሚዲያ ገለልተኛ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ ከጅምሩ ሀሳባዊ ወይም አይዲያሊስቲክ ይመስለኛል፤ሚዲያ ነፃ ነው መሆን ያለበት እንጂ ገለልተኛ አይደለም፡፡
ቁም ነገር፡-ምን ማለት ነው?
ግርማ ፡-አንተ እንደ ሚዲያ አቋም ሊኖርህ ይችላልላ፤በአሜሪካ ለምሳሌ ወይ ዲሞክራትን ትደግፋለህ ወይ ሪፐብሊካንን፤ያንን አቋምህን ይዘህ ስራህ ላይ ሳትጨምር በነጻነት መስራት መቻልህ ይመስለኛል ዋናው ነገር፤ሚዲያ ገለልተኛ ሊሆን አይችልም፤ ቢያንስ ለእውነት ትወግላናለህ፤
ቁም ነገር፡ እውነት ራሱ ምንድነው?
ግርማ ፡-እሱም ያከራክራል፤ ቢያንስ ግን እኛ እውነት ነው ብለን ለያዝነው አቋም ልንወግን እንችላለን፤መደባበቅ አያስፈልግም፡፡ለምሳሌ ህብረ ብሔራዊነት ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል ስንል ብዛሃነት ያለበት ሀገር ስለሆነ ነው እውነታው፡፡ አይደለም አሃዳዊነት ነው የሚሻለው የሚል ቢመጣ ሀሳቡን እናከብርለታልን እንጂ ልንወግነው አንችልም ማለት ነው፤
ቁም ነገር፡-በንደፈ ሀሳብ ሳይሆን በተግባር ኦኤም ኤን ከሚያቀነቅነው ሀሳብ ውጭ ሀሳብ ላላቸው አካላት ምን ያህል እድል እየሰጠ ነው?
ግርማ ፡-እንግዲህ ከእኛ የተለየ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች መጥተው ቢናገሩና የሀሳብ ብዛህነት ቢታይ እኮ የምንጠቀመው እኛው ነን፤ በየጊዜው አንድ አይነት ሀሳብ ስንወቅጥ ከምንውል ህዝቡም ሌላ አማራጭ ሀሳብ ያያል፡፡ፍላጎታችን ይሄ ሆኖ ሳለ በተግባር ላልከው ግን በጣም ብዙ ችግሮች አሉብን እንደዛ እንዳይሆን፤
ቁም ነገር፡-ለምሳሌ?
ግርማ ፡-ለምሳሌ የመንግስት ባለስልጣናትን ስንጠራ አይመጡም፤ የአንዳንድ የተቃዋሚ ፖርቲ አመራሮችም አይመጡም፤የማሳተፍ ፍላጎቱ ቢረኖርህም እንደዚህ አይነት ነገሮች ያጋጥሙሃል፤
ቁም ነገር፡-ግን ችግሩ ምንድነው የሚለውን አይታችኋል፤ ለምሳሌ የመንግስት ባለስልጣናት የማይመጡበት ምክንያት?
ግርማ ፡-ያው ቀደም ሲል ኦኤምኤን የነበረው የቀድሞ ስም አለ፤ ከእዛ ሀንጎቨር ገና አልወጣንም፤ ፅንፈኛ ሀሳብ ያነሳል ብለው የሚቀሩ አሉ፤ ሀሳብ ይፈራሉ ማለት ነው፡፡ እኛ ጋዜጠኞች በኩል ለሁሉም እድል ለመስጠት ነው የሚሰሩት፤ እንደውም በጋዜጠኞቻችን ከምንኮራበት ነገር ውስጥ አንዱ ሀሳብ ሳይፈሩ በነፃነት መዘገባቸው ነው ፡፡ ማንም ሳንሱር ሳያደርጋቸው ነው የሚያቀርቡት፡፡
ቁም ነገር፡-ጣቢያችሁ ከሚወቀስበት ነገር ውስጥ አንዱም ማንም ሰው ተነስቶ የሚናገረውን ነገር እንዳለ ማስተላለፋችሁ ነው፤ የቅርብ ጊዜውን ክስ መጥቀስ ይቻላል፤ ገብረጉራቻ ላይ በነበረ ስብሰባ ላይ አንድ ‹የሀይማኖት ›ግለሰብ የተናገሩትን ቀስቃሽ ሀይማኖታዊ ንግግር እንዳለ አሰራጭታችሁታል፤ ይህ ጉዳይ ከህግና ከሙያው አንፃር እንዴት ይታያል?
ግርማ ፡- እንግዲህ ያ ጉዳዩ እንዴት ከህግና ከሙያው ጋር እንደሚጋጭ አላውቅም፤ እርግጥ ክሱን አይቼዋለሁ፤ ግን ፕሮግራሙ ከፍተኛ ህዝብ የተገኘበት ስብሰባ ነው፤ እንደ አንድ ሚዲያ ሊያውን የኦሮሚያ ክልልን ጉዳይ በስፋት እንደሚዘግብ ሚዲያ ክስተቱን ዝም ብለን ልናልፈው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፤ ያንን ጉዳይ እዛው ቦታ ድረስ ሄደን ስንዘግብ ለምን አስተላለፋችሁ ነው ክሱ፤ እርግጥ ግለሰቡ በወቅቱ ያደረጉት ንግግር የፖለቲካም የሀይማኖትም ይዘት ያለው ንግግር ነው፤ የህግ ተጠያቂነትም ካለ የእሳቸው ነው መሆን ያለበት እንጂ ጣቢያው የግለሰብ ሀሳብ ለምን እንዲያፍን ይጠበቃል ነው ያልነው፤ እንዳልኩህ የዚህ አይነት ጉዳዮችን የኦኤምኤን ጋዜጠኞች በነፃነት ለህዝብ በማድረግ የሚቀድማቸው የለም፤ በዚህ ኮራ ብዬ ነው የምናገረው፤
ቁም ነገር፡-እና ግለሰቡ እንጂ ጣቢያው ሊጠየቅ አይገባም እያልከኝ ነው?
ግርማ ፡-ትክክል ፤ ሰውየው እዛው አለላቸው፤
ቁም ነገር፡-ሰውየው እኮ ያንን ንግግር የተናገረው እዛው ላለው ሰው ብቻ ነበር፤ በየቤቱ ላለው በሚሊዮን ለሚቆጠረው ህዝብ ያሰራጨው እኮ የእናንተ ጣቢያ ነው፤ ታዲያ እንዴት ነው እኛን አይመለከትም የምትለኝ?

ግርማ ፡-እኛ የግለሰቦችን ሀሳብ ለምን አላፈናችሁም በሚል የሚከሰን ካለ ራሳችንን በዚህ ረገድ ለመከላከል ዝግጁ ነን፤
ቁም ነገር፡-ወደ ሌላ ጥያቄ ልውሰድህ፤ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ እንዴት ነው የምትረዳው፤ ማናቸውም ነገሮች ቢነገሩት አመዛዝኖ መቀበል የሚችል ነው ወይስ በትንሽ ነገር ወደ ግጭት ለመግባት ያሰፈሰፈ ሃይል ያለበት ህብረተሰብ ነው?
ግርማ ፡-እኔ የመጀመሪያው አይነት ህብረተሰብ እንዲኖረን ነው የምፈልገው፤
ቁም ነገር፡- አንተ የምትፈልገው ሳይሆን አሁን መሬት ላይ ያለው እውነታ የቱ ነው?
ግርማ ፡-ሰዎች ማሰብ ይችላሉ፤ ማመዛዘን ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው፤ ምን አይነት ነገር ቢነገራቸው ያስባሉ፤ ለምሳሌ እኔ የሆነ ነገር ብናገር ሰዎች ተነስተው ይጨቃጨቃሉ ወይም ይጋደላሉ ብዬ ማሰብ አልፈልግም፤ከዚህ የተለየ መንገድ መከተል የሚፈልጉ ሰዎች አይኖሩም ማለት አይደለም፤ ግን ለእንደዛ አይነት ሰዎች ደግሞ ህግ የሚባል ነገር አለ፤በነገራችን ላይ ግልጽ ነገር በመናገር ከሚመጣው አደጋ ይልቅ ግልጹን ነገር እንዳይነገር በማድረግ የሚመጣው አደጋ ይበልጣል ብዬ ነው የማስበው፤
ቁም ነገር፡-ግን በግለሰቦች ንግግር ብቻ ግጭቶች እዚህ ሀገር ላይ አልተነሱም ወይ? መንገዶች አልተዘጉም ወይ?
ግርማ ፡-መንገድ መዝጋት ሰላማዊ የትግል ስልት ነው ችግር ያለው አይመስለኝም፤
ቁም ነገር፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ አደባባይ የወጣ ሰው መኪናና ፋብሪካ ማቃጠሉስ?
ግርማ ፡-መኪና ወይም ፋብሪካ አቃጥሉ ያለ ሰው ካለ ያ ወንጀለኛ ነው፤ እኛ የዚህ አይነት ነገር አናስተላልፍንም፤ ልናስተላልፍም አንችልም፤ ኦኤም ኤን እስከዛሬ ድረስ ውሸት አስተላልፎ አያውቅም፤ ውሽት አስተላልፈን ይቅርታ የጠየቅንብት ጉዳይ የለም፤ሌላው ሚዲያ ስንት ጊዜ ነው ተሳስቻለሁ ብሎ ይቅርታ የሚጠይቀው፤ አንድ ሪከርድ የለብንም በዚህ ረገድ፤የሚነሳ ጥያቄ የለም ማለት ግን አይደለም፤
ቁም ነገር፡- ከዜና ውጭ በፕሮግራሞች ላይ ግለሰቦች ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ስማቸው ለምን ይነሳል?
ግርማ ፡-ለምሳሌ?
ቁም ነገር፡-ለምሳሌ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ባሉትም ባላሉትም ጉዳይ ላይ ስማቸው እየተነሳ ይብጠለጠላሉ፤
ግርማ ፡-እሳቸውማ መብጠልጠል ብቻ አይደለም፤ ሃሳባቸው እየተነሳ በደንብ ይተቻል፤ እሳቸው እኮ የሀገር መሪ ናቸው፤ የፖለቲካ ሰው ናቸው ፤ ፐብሊክ ፊገር የሚባሉ ናቸው፡፡ቢቢሲም ሲኤንኤንም ብታይ የየሀገራቸውን መሪዎች ይተቻሉ፤
ቁም ነገር፡-ግን ክብርን በሚነካ መንገድ ነው?
ግርማ ፡-ክብራቸውን በሚነካ መልኩ መደረጉን አላስታውስም፤
ቁም ነገር፡-የብሮድካስት ባለስልጣን ሚዲያችሁን በተመለከተ ተደጋጋሚ ደብዳቤ መፃፉ ይነገራል፤ ያ ምን ያሳያችኋል?
ግርማ ፡-ብሮድካስት ባለስልጣን የህዝብ ቅሬታ ሲመጣለት በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሀሳብ አላችሁ በማለት ደብዳቤ ይፅፋል፤ለደብዳቤው ህጋዊ ምላሽ እንሰጣለን፤ ከሌላው በተሻለ ሁኔታ ደፈር ብለን በነፃነት ስለምንዘግብ ቅሬታዎች መምጣታቸው የሚጠበቅ ነው፤
ቁም ነገር፡- በጣቢያችሁ ላይ ለተለያዩ ብሔር ተኮር ፖርቲዎች የአየር ሰዓት ሰጥታችሁ ፕሮግራሞቻቸውን ያስተላልፋሉ፤ ለምን ለእነርሱ ብቻ መርጣችሁ ሰጣችሁ?
ግርማ ፡-እኛ አልመረጥንም፤ ራሳቸው ናቸው የአየር ሰዓት ይሰጠን፤ ሀሳብ አለን ለህዝባችን የምናስተላልፈው ብለው የመጡት፤
ቁም ነገር፡-በነጻ ነው በክፍያ?
ግርማ ፡-አምስት ሳንቲም አናስከፍላቸውም፤ ሌሎችም ሀሳብ አለን የምናስተላልፈው ካሉ መምጣት ይችላሉ፤ በነገራችን ላይ እነዚህ አካላት ከሚያስተላልፏቸው የፖለቲካ አቋሞች ይበልጥ ከአሁን በፊት በሚዲያ ተሰምተው የማያውቁ ቋንቋዎችን ለህዝባቸው እንዲያደርሱ ዕድል መስጠቱ ነው ለእኛ የበለጠ ትኩረት የምንሰጠው፤ኢትዮጵያውያን ሲተዋወቁ ነው የኢትዮጵያ አንድነት የበለጠ እየጠነከረ የሚሄደው ብለን ነው የምናምነው፡፡
ቁም ነገር፡-ከፖለቲካ አቋማቸው ይልቅ በቋንቋቸው መጠቀማቸው ነው የእኛ ትኩረት ብለሃል፤ ለምሳሌ ለቅማንት የሰጣችሁት የአየር ሰዓት በቅማንትኛ የሚቀርብ አይደለም፤
ግርማ ፡-ከቻሉ የከለከላቸው የለም፤ ግን በዚህ የተነሳ የፖለቲካ ሀሳባቸውን ማፈን አይገባንም፤ ምርጫው የእነርሱ ነው፤
ቁም ነገር፡-ኦኤም ኤን የንግድ ሚዲያ ሆኖ ተመዝግቧል፤ የገቢ ምንጫችሁ አሁን ምንድነው?
ግርማ ፡-እንደማንኛውም ሚዲያ ማስታወቂያ ነው፤ በትብብር አብረውን ለመስራት የሚፈልጉ ተቋማት ስፖንሰር የሚያደርጉ አሉ፤ለወደፊቱ አክሲዮን ሸጠን ካፒታላችንን ለማሳደግ ነው ሀሳባችን፡፡
ቁም ነገር፡-ከዚህ ከስፖንሰር ሽፕ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ፋብሪካ ያላቸው የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች ኦኤምኤንን እንዲደግፉ ግፊት ይደረግባቸዋል ይባላል፤ ይህን ያህል እውነት ነው?
ግርማ ፡- ማነው ግፊት የሚያደርገው?እኛ መንግስት አይደለንም ግፊት የምናደርገው፤
ቁም ነገር፡-ያው ከአሁን በፊት ጃዋር ሁለት መንግስት ነው በዚህ ሀገር ያለው ብሏል እኮ፤
ግርማ ፡- እኔ አንድ መንግስት እንዳለ ነው የማውቀው፤ ሁለት መንግስት የለም፤ ማንኛውም ሚዲያ በህዝቡ ውስጥ የራሱ የሆነ ተቀባይነት አለው፤ ደረጃው ሊለያይ ይችላል እንጂ፤ባለሀብቶችን እኛ አገልግሎት ሸጠንላቸው ነው ገንዘብ ልንቀበላቸው የምንፈልገው፤ድርጅታቸውን አስተዋውቀን ማለት ነው፡፡ እኛን ማንም እንዲያስገድደን እንደማንፈልገው ሁሉ እኛም ማንንም አናስገድድም፤
ቁም ነገር፡-ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ከተከለከሉ ሚዲያዎች መሀከል የእናንተና ኢሳት ይጠቀሳል፤ አሁን ሁለታችሁም ሀገር ቤት ገብታችኋል፤ ኢሳትን እንዴት ነው የምታዩት? እንደ አጋር ነው እንደ ተቀናቃኝ ሚዲያ?
ግርማ ፡- ኢሳት ልክ እንደኛ ውጭ ሀገር የነበረ ሚዲያ እንደሆነ ይታወቃል፤ ሁለታችንም የተለያ ኣላማ አለን ብዬ ነው የማስበው፤ከዚያ በተረፈ እንደ አንደ ተወዳዳሪ ሚዲያ ነው የምናያቸው፤ ገበያውን እንካፈላለን፤ ተመልካችም እንካፈላለን፤በውድድር ላይ ያለን ሚያዎችን ነን፡፤
ቁም ነገር፡-ውድድራችሁ ግን ጤናማ ነው ለማለት ይቻላል፤ እናንተ ጣቢያ ላይ ስለ ኢሳት የሚባል ነገር አለ፤ እነርሱም ላይ ስለ እናንተ የሚባል ነገር አለ፤
ግርማ ፡-እነርሱ ናቸው ስለእኛ ብዙ የሚናገሩት እንጂ እኛ አይደለንም፤እነርሱ በየጊዜው ጃዋርን ሳያነሱ አያልፉም፤ ጃዋር በአንድ ወቅት የዚህ ሚዲያ ዳይሬክተር ነበር፤
ቁም ነገር፡-አሁንስ?
ግርማ ፡-አሁን ባርኔጣ ቀይሮ ፖለቲካኛ ሆኗል፤ ግን አሁንም ድረስ የዚህ ሚዲያ ባለቤት አድርገው ነው የሚያቀርቡት፤ አንድ ሰው እንዴት በየዕለቱ የአንድ ሚዲያ የውይይት አጀንዳ ሊሆን ይችላል? ግለሰቡ እያሉ ሲያወሩ ነው የሚውሉት፤ የዛን ጊዜ እኛም መልስ ሰጥተናል፤ ከእዛ ውጭ መነታረክ አንፈልግም፤ ለተመልካቾቻችንም ክብር መስጠት ስላለብን በኢሳት ላይ ስለሚባሉ ጉዳዮች ሁሉ መልስ አንሰጥም፤ጃዋር ግለሰብ ነው፤ ገና መንግስት አልሆነም፤ እንዴት በየእለቱ ስለ እሱ ብቻ ይወራል?
ቁም ነገር፡- ከሌሎች በኦሮሞ ስም ከሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነትስ?
ግርማ ፡-ጥሩ ነው፤ በብዙ ነገሮች እንገናኛለን፤ እንደውም የኦሮሞ ሚዲያ ፎረም ለመመስረት ጥረት እያደረግን ነው፡እኛ ጋር ያለ ጥሩ ነገር አለ፤ እነሱም ጋር ያለ ጥሩ ነገር አለ፤ ያንን ልናቀናጀው እንችላለን፤ አብረን መስራት እንፈልጋለን፤
ቁም ነገር፡- ምዕራብ ወለጋ ላይ ከዶምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ ጋር ተያይዞ ትልቅ ችግር አለ፤ ይህንን ሁኔታ ኦኤምኤን እንዴት ነው እየዘገበው ያለው?
ግርማ ፡-ትክክል ነው፤ አካባቢው ላይ ሰፊ ችግር አለ፤ ለቀምት ላይ የእኛ ሪፖርተር ነበር፤ ነገር ግን ከቦታ ቦታ ተቀሳቅሶ ለመዘገብ ስላልቻለ ምንም መረጃ ማግኘት አልቻልንም፤ለምሳሌ ባላፈው ሳምንት ከወለጋ ተፈናቅለው ጋምቤላ የሰፈሩ ሰዎችን ለማገነጋገር ጋምቤላ ድረስ ሄደው ነበር፤ በተወሰነ ደረጃ መረጃ ስለአካባቢው ለማግኘት ሞክረዋል፤ ብዙም የተሟላ አይደለም፤ፕሮግራም ተሰርቶበታል፤ይህንን ያህል ስለሁኔታው መረጃ የሰጠ ሚዲያ መኖሩን አላውቅም፤
ቁም ነገር፡-ምርጫ 2012 በመጪው ነሐሴ ይደረጋል ተብሏል፤ ኦኤምኤን እንዴት ነው ይህንን ምርጫ ለመዘገብ እየተዘጋጀ ያለው?
ግርማ ፡-እንደማንኛውም ሚዲያ መረጃ ስለምርጫው ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው፤ ፕሮግራሞቻችን 90 ከመቶ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚሰራጭ በመሆኑ በተለይ ኦሮሚያ ላይ የሚኖረውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት፤ተጨባጭ ዳታዎች ላይ የተመሰረቱ ዘገባዎችን እንሰራለን፤ አንድ ነገር እርግጠኛ ሆኜ ልንግርህ የምችለው ግን ከህዝብ ኪስ በተዋጣ ገንዘብ የሚንቀሳሰቀስ ሚዲያ ስለሆነ ለማንኛውም የፖለቲካ ፖርቲ ማስተጋቢያ ሊሆን አይችልም፤በዚህ ረገድ መንግስትም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንድንችል የራሱን አስተዋፅኦ ቢያደርግልን ጥሩ ነው እላለሁ፤
ቁም ነገር፡- ጣቢያችሁ ወቅታዊ ጉዳዮችና ፖለቲካው ላይ አተኩሮ የሚሰራ ሚዲያ እንደሆነ ይታወቃል፤ ግን ህይወት ፖለቲካ ብቻ አይደለም፤ በመሆኑም ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን የመስራት እቅዳችሁ ምን ያህል ነው?
ግርማ ፡-ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስንነጋገር ይህንን ያነሳሉ፤ በየወሩም ግምገማቸውን ይልኩልናል፤ 90 ከመቶ ፖለቲካ ላይ ነው የምትሰሩት የሚል አስተያየት አላቸው፤ እኛም የተለያዩ ይዘቶችን ለመጀመር ፍላጎት አለን፤ የሴቶች፤ የወጣቶች፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ በአማርኛም በኦሮምኛም የመስራት ፍላጎት አለን፤ አንዳንዶቹ ተቋርጠው ነው፤ስፖርትም ተቋርጦ ነው፤ባህል ላይም የምንሰራቸው ፕሮግራሞች አሉ፤ ለማስፋት ሳይነስና ቴክኖሎጂ፤ የህጻናት ወዘተ ለመጀመር ፍላጎቱ አለን፤
ቁም ነገር፡-ህጋዊ ሆናችሁ በሀገር ቤት ገብታችሁ እየሰራችሁ በመሆኑ የሚዲያ ካውንስል አባል ለመሆን ምን ታስባላችሁ?
ግርማ ፡-ጥሩ ነው መሳተፍ አለብን ብለን እናስባለን፡፡በእንደዚህ አይነት ማህበራት ውስጥ ገብተን የበኩላችንን ሚና መጫወት እንፈልጋለን፤ የህግ አማካሪ አለን፤ ከእርሱ ጋር እየተነጋገርንበት ነው፤ ብቻችንን ተለይተን መቅረት አንፈልግም፤ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራትም ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፤
ቁም ነገር፡-አመሰግናለሁ፤
ከአዘጋጁ፡- ከኢሳት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ሀሳብ የኢሳት አዲስ አበባ ስራ አስኪያጅን ጠይቀን ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe