የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባወጣው የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ መመሪያ መሠረት አዲሱ የተሸከርካሪ ሰሌዳ የመቀየር ሥራ ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚጀመር በሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎት እና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስ ተናግረዋል፡፡
አማካሪው ከአሐዱ ሬዲዬ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 ሆኖ መጽደቁን አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 መሠረት፤ አሁኑ በሥራ ላይ ያሉ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ላይ የሚቀመጠው የተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች መለያዎች ተመሳሳይ መለያ እንዲኖራቸው ያስገድዳል።
በዚህም መሠረት በሀገሪቱ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሸከርካሪዎች የሚለጥፉት የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ላይ፤ የኢትዮጵያ ካርታ እንዲሁም ኢትዮጵያ ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የተሰጣትን ሀገራዊ ልዩ ምልክት “ETH” እና ” ኢት” የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው ይደረጋል ተብሏል፡፡

