ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የተለያዩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመለሱ

በ1868 በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች በይፋ ለኤምባሲው መመለሳቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
ከተመለሱት ቅርሶች መካከል በ1868 ከመቅደላ የተዘረፈ የመድሃኒያለም ታቦት፣ የልኡል አለማየሁ የጸጉር ዘለላ፣ ከብር የተሰሩና በነሃስ የተለበጡ ሦስት ዋንጫዎች እንዲሁም በዘመኑ ጦርነት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ እንደሚገኙበት ገልጿል፡፡
ለንደን በሚገኘው የአቴናየም ክለብ በተካሄደው የቅርሶቹ ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ፤ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልኡካን ቡድን፣ የብሄራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተወካይ፣ የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት፣ ቅርሶቹን ለማሰመለስ የተባበሩ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይም አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፤ የተመለሱት የተለያዩ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት፣ ታሪክና ባህላዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሀብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አሳዛኝ በሆነው የመቅደላ ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች እሰከአሁን አለመመለሳቸው በመላው ኢትዮጵያዊ ልብና አእምሮ ውስጥ ጥያቄ ፈጥሮ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
“እነዚህ ቅርሶች እንደ ቀላል ቁስ የሚታዩ ሳይሆኑ የአንድ ጥንታዊት አገር የታሪክ፣ የባህልና የማንነት መገለጫዎች ናቸው።” ብለዋል፡፡
አምባሳደር ተፈሪ አክለውም፤ ኤምባሲው ከመቅደላና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘርፈው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተጋዙ ቅርሶች እንዲመለሱ፤ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ለኹሉም የብሪታኒያ ሙዚየም የሥራ ሃላፊዎች፣ ለጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ለቅርስ አስመላሽ እና ተሟጋቾች እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው፤ “አሁንም ይህ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።” ማለታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe