መስክ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የግብር እና የወጪ ህግ አሳፋሪ እና አስጸያፊ ሲል ኮንኗል፡፡ የባለብዙ ትሪሊዮን ዶላር የታክስ እፎይታ እና ተጨማሪ የመከላከያ ወጪዎችን ጨምሮ የአሜሪካን መንግስት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲበደር የሚፈቅደው ይህ ህግ በግንቦት ወር ጸድቋል፡፡
ኤለን መስክ ማክሰኞ እለት በኤክስ ገጹ ላይ በለጠፈው መልዕክት ይህንን ህግ ለማጽደቅ ድምጻቸውን የሰጡ ያሳፍራሉ ብሏል፡፡ ቢሊየነሩ መስክ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ዶጅ ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለ129 ቀናት ወጪን ለመቀነስ ከሰራ በኋላ በድንገት አስተዳደሩን መልቀቁ ይታወሳል፡፡
ኤለን መስክ ቀደም ሲል እቅዱን አሳዛኝ በማለት የጠራው ቢሆንም አሁን የሰጠው አስተያየት ግን የመንግስት ሃላፊነቱን ከለቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያለውን አለመግባባቱን የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡
ትራምፕ ግዙፍ ቆንጆ ህግ ብለው የሚጠሩት ይህ አዋጅ መንግስታቸው ያለበትን የበጀት ጉድለት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚያደርገው ተገምቷል፡፡
ኤለን መስክ ማክሰኞ እለት ባጋራው ጹሑፍ አስፈሪ፡ከፍተኛ የመንግስት ወጪን ለመሸፈን ወጣ ህግ ቀደም ሲል ያለውን ግዙፍ የበጀት ጉድለት ወደ 2.5ትሪሊየን ዶላር በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል እንዲሁም የአሜሪካ ዜጎችን በሚያስደነግጥ አስተማማኝ ባልሆነ እዳ ይጭናቸዋል ሲል ተችቶታል፡፡
ህጉ በ2017 በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር ጊዜ የጸደቀውን እና በቅርቡ የሚጠናቀቀውን የግብር ቅነሳ እና ለመከላከያ ወጪ የሚመደበውን የገንዘብ መጠን ለማራዘም ያስችላል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አስተዳደሩ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞችን በጅምላ ለማባረር የገንዘብ ድጋፍ ለ ማድረግ ያስችላል፡፡/

