ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ምርቶችን የሚያመጡ ነጋዴዎችን የሚቆጣጠር አዲስ መመርያ ማዘጋጀቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ

በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሳቢያ እንደ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ስንዴ፣ፓስታና ማካሮኒ የመሳሰሉ መሠረታዊ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ባለፈው ዓመት መፈቀዱ ይታወሳል።

ነገር ግን ነጋዴዎች የተሰጠውን ዕድል በሕገወጥ መንገድ እየተጠቀሙበት በመሆኑ አዲስ መመርያ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳውቋል።

ሚስቴሩ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱ የፍጆታ ምርቶች ታሪፍ የማይከፈልባቸው በመሆናቸው ኅብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ እንዲገዛ ለማድረግና የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ቢሆንም አስመጪዎች ግን በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል ብሏል።

ከቀረጥ ነፃ ዕድልን የሚጠቀሙ አስመጪዎች በተጠበቀው መሠረት እየሠሩ እንዳልሆነ የገለፀው ሚኒስቴሩ ምርቶቹን ያለ ደረሰኝና በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ እንደሆነ ገልጿል።

ይህን መሠረት በማድረግ አስመጪዎችን የሚቆጣጠር መመርያ ተዘጋጅቷል።

አዲሱ መመርያ አስመጪዎች ያስመጡትን የምርት መጠን፣ ዓይነትና ያስመጡበትን ጊዜ ጉምሩክ ኮሚሽን መዝግቦ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ለክልል ንግድ ቢሮዎች የሚያስተላልፍበትን አሠራር ይዟል።

ጉምሩክ ኮሚሽን በሚሰጠው መረጃ መሠረት የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ንግድ ቢሮዎች ምርቱ ለማን እንደተከፋፈለ፣ በምን ያህል ዋጋ እንደተሸጠና በሕጋዊ መንገድ መሸጡን ያረጋግጣሉ።

ይህ አዲስ መመሪያ ከ2 ሳምንት በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል። አስመጪዎቹ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ምርቶችን ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና ለሸማቾች ማኅበራት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያቀርቡ ያዛል።

ምንጭ፦ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe