ከአምባገነኑ መሪ ጀርባ ያሉ አምባገነን እጆች

ፍፁም የአምባገነኖች ምድር፤ፍፁም የተጨቋኞች ሀገር። ዓለም አንድ በሆነበት ዘመን 26 ሚሊየን ዜጎቿን ይዛ የመነነች። የወንድ አምባገነን መሪዎች አልበቃት ብሎ ተጨማሪ ሴት አምባገነኖችን ለማዋለድ መንገድም የጀመረች። የአንድ ቤተሰብ ርስት፤የአንድ ቤተሰብ ንብረት። ሰሜን ኮሪያ። ከአምባገነኑ መሪ ጀርባ ያሉ አምባገነን እጆች።

በፒዮንግያንግ ፖለቲካ ውስጥ እለት እለት የምናየውና የምናውቀው ፊት አንድ የኪም ጆንግ ኡንን ብቻ ነው።ግን ከእስክሪኖቹ ኋላ፤ከውሳኔዎች ሁሉ ጀርባ ኪም ብቻቸውን ሳይሆኑ አንድ ሴት አብራቸው አለች ነው የሚባለው። እርሷን ሴት አብረን እንፈልጋታለን።

ሁሉም ነገር በሚስጥር በሚያዝባት ሰሜን ኮሪያ መረጃዎችን ማገኘት ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል። ነገር ግን ጎረቤት ከሆነችው ደቡብ ኮሪያ ጥብቅና ሚስጥራዊ መረጃዎች በየጊዜው ሲወጡ እናያለን።

እንደአብነትም። የሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ አቅም እንደምታሳየን ሳይሆን ከዚህ የደከመ ነው። መሪያቸውም ሲበዛ ጠጭ ፤በዚህም ታማሚ ነው አይነት ሚስጥሮችን ደቡብ ኮሪያ ለውጩ ዓለም ሚዲያ ታሾልካለች።

እናም ከዚች ሴት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በብዛት የደቡብ ኮሪያ ሚዲያዎችን ምንጮቻችን አድርገን የሀገሪቱ ሁለተኛዋ ሁሉን አድራጊ ሴት ስለሆነችው ጥቂት መረጃዎችን እናያለን።

ሰሜን ኮሪያ የሶስት ትውልዶች ሀገር። የኪም ዳይናስቲ ንብረት መሆኗ ይታወቃል። ኪም ጆንግ ኡን ሦስተኛው የኪም ዳይናስቲ ሰው ናቸው። የአባትየውን መሞት ተከትሎ ከ2011 ጀምሮ ሁሉን እንዳሻቸው እያደረጉ በስልጣኑ አሉ።

በሰሜን ኮሪያ ፖለቲካ ውስጥ ከኪም ቀጥሎ የሦስት ሴቶች ስሞች ተደጋግመሙ ይታወቃሉ። ቀዳሚዋ የሁሉን አድራጊው ኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህት ኪም ዮ ጆንግ ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ቀዳማዊት እመቤቷ ሪሶል ጁ ናቸው።
ሦስተኛዋ ደግሞ ገና የ11 ዓመት እድሜ ያላት የኪም ልጅ ኪም ጁ ኤ ነች። በርግጥ ኪም ጁንግ ኡን ሌላ ሁለት ልጆች እንዳሏቸው ይነገራል።

ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ኪም ጁኤ ከ2022 ጀምሮ ካባቷ ጎን በመሆን የሀገሪቱ የሚሳኤል ጣቢያ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎችን ሲያስወነጭፍና ሲጎበኙ የሚያሳይ ፎቶ በመልቀቅ ነበር ከተቀረው ዓለም ጋር የተዋወቀችው።

በወቅቱ ኪም ለምን ገና ከዋና:ከፈረስ ግልቢያ እና ከትምህርት ቤት ያልወጣች በጣምም ታዳጊ የሆነች ልጃቸውን ባላስቲክ ሚሳኤልን እንድትጎበኛና ዓለምም ልጃቸውን በዚህ ሁኔታ እንዲያውቁላቸው ወደዱ እያሉ ብዙዎች እየጠየቁ ነበር።

ከዚህ ጥያቄያቸው አያይዘውም ምንአልባት የወደፊቷ የሰሜን ኮሪያ መሪ ልትሆን ትችላለች እያሉ መልስም ሰጥተው ነበር። በርግጥ ብዙዎች በዚህ እርግጠኞች ናቸው። በቀጣይ የሰሜን ኮሪያ ተተኪ አምባገነን መሪ ሴት እንደምትሆን ። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ኪም ጆንግ ኡን በህይወት እስከሌሉ ብቻ ነው።

በወቅቱ የሰሜን ኮሪያዊያን ሚዲያዎች ልጅቱን ሲጠሩና ሲያስተዋውቁ ተወዳጇ ልጅ እያሉ ነበር የጠሯት።

ቆየት ብለው እርሷም በተደጋጋሚ ከአባቷ ጎን በወታደራዊ ቦታዎች:በትልልቅ እራት ግብዥዎች መታየት ስታበዛ ግን ተወዳጇ ልጅ የሚለውን መጠሪያ በመተው የተከበረች ልጅ ወደሚል ለውጠውታል።

የሰሜን ኮሪያ ሚዲያዎች ያለምክኒያት ይህንን መጠሪያ አይጠቀሙትም እናም ተተኪ መሆኗን እየነገሩን ነው ይሉነበር የእስያ ሀገር ሚዲያዎች።

ኪም ጆንግ ኡንም ቢሆኑ ከአባትየው ተተኪ መሪ ተብለው የተሾሙት የ8 ህጻን እያሉ ነበር።

ኪም አሁን ገና የ40 ዓመት ጎልማሳ ናቸው። ምንም እንኳን ይሄ ነው ተብሎ የተነገረ በሽታ እንዳለባቸው ባናውቅም ከውፍረታቸው ጋር የተገናኘ የጤና ችግር ሳይኖርባቸው እንደማይቀር ነው የሚነገረው።

አሁን ኪም 140 ኪሎ ግራም ይመዝናሉ ነው የሚባለው። እናም ይህ ውፍረት መዘዝ ሳያመጣባቸው እንዳልቀረም ይነገራል።

በሰሜን ኮሪያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ የምግብ እጥረት አለበት፤ የተመጣጠነ ምግብ የማያገኝ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

እናም በዚች ሀገር ውፍረት የሀብት መገለጫ ነው። የወፈረ ሁሉ ሀብታም፤ቀጠን ያለው ደግሞ ያጣ የቸገረው እንደማለት ነው።

ታዲያ የኪም ውፍረትም የሀብት መጠንን ለማሳየትም ሊሆን ይችላል።

ኪም በጣም ጠጭ በጣምም አጫሽ እና ጭንቀታም ሰው መሆናቸው ደግሞ ሌላው ለውፍረታቸው መንስኤ ነው ተብሎ ይነሳል። ኪም አባታቸውንም ይሁን አያታቸውን ያጡት በልብ ህመም ነበር ። እናም የኪም ቤተሰብ የልብ በሽታ ስጋት ያለበት እንደሆነ ነው የሚታወቀው።

እናም እነዚህና ተያያዥ ስጋቶች ያሉባቸው በመሆኑ ነው ኪም ልጃቸውን ወደፊት ማምጣት የፈለጉት የሚሉም አሉ።

በርግጥ ኪም ጆንግ ኡን ገና 40 ዓመት ላይ ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ ሀገሪቱን ብዙ የመምራት እድል አላቸው ግን የጤናቸው ሁኔታ ስጋትን ፈጥሮባቸዋል ነው የሚባለው። ከወራቶች በፊት በጭምትምታም ቢሆን የኪም መታመምን የሰሙ ሰሜን ኮሪያዊያን በየቤታቸው በለቅሶ እንዳሳለፉም ሲነገር ነበር በወቅቱ።

ምንም እንኳን ኪም አንድ ወንድ እና ሌላ አንድ ሴት ልጅ ቢኖራቸውም በይፋ ማስተዋወቅ የፈለጉት ግን በጣም የሚወዳዷትን ኪም ጆንግ ኤን እንደሆነ ነው የሚነገረው።

እናም ሰውየው የ11 ዓመት ሴት ልጃቸውን ሚሳኤሎች ባህር አቋርጠው ሲወነጨፉ በማሳየት አስቸጋሪውን የአለም የፖለቲካ ስልጣን እንድትማረው እያደረጉ ስለመሆናቸው የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም።

እናም ሰሜን ኮሪያዊያን ጁኤን በይፋ ከተዋወቋት በኋላ ቀጣይ መሪያቸው ልትሆን እንደምትችል መገመት የጀመሩት ከ2022 ወዲህ ባለው ጊዜ ነው።

ሚዲያውም ጁኤ አሁን ወደ መድረኩ ብቅ ያለችው ያለመክኒያት አይደለም። በፖዲየም ፊት ቆሞ ንግግር ማድረግን ልትለማመድ:የሀገራት መሪዎችን አባትየው ተቀብለው ሲያነጋግሩ ከእጅ መጨበጥ ጀምሮ ሌሎች የፕሮቶኮል ጉዳዮችን በተግባር ለመማር ነው ወደፊት የመጣችው ነበር የሚሉት።

ምን አልባት ይሄኛው ግምት ካልሆነ ግን ትልቅ ስምና ስልጣን ያላት የጁኤ አክስት የኪም ደግሞ ታናሽ እህት ኪም ዮ ጁንግም አለች።

ይች ሴት ከ2011 ጀምሮ ኪም በተገኘበት ቦታ ሁሉ ከኋላም ይሁን ከጎን የማትጠፋ ነች።

ኪም ጆንግ ኡን በ2011 የሰሜን ኮሪያዊያን የረጅም ጊዜ መሪ የነበሩት ኪም ጆንግ ኢል ሲሞቱ እና ኪምም መንበሩን ተረክበው የአባታቸውን የቀብር ስነ ስርዓት ሲያስፈፅሙ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እህትየው ኪም ዮ ጁንግ በፒዮንግያንግ ፖለቲካ ውስጥ አለች። ደሞም እጀረጅምም ነች ይባላል። እርሷን ተረዳናት የሚሉ ሰዎች ስልጣን ወደእርሷ እንደሚሄድ ያምናሉ።

በ2017 የኪም ጆንግ ኡን በአባት ይሁን በእናት የሚወለደው ወንድሙ በማሌዢያ ኤርፖርት ውስጥ ሁለት ሴቶች አቀናበሩት በተባለ ጥቃት እንዲገደል ተደርጎ ነበር።
እናም የብዙዎች ጥርጣሬ አስገዳይዋ ኪም ዮ ጁንግ ነች ነው። ስልጣን እንዳይሻማኝ እና የቤተሰብ ስርዎ መንግስት ሳይበረዝ እንዲቀጥል በሚል ይህን አድርጋለች የሚሉ ነበሩ ምንም እንኳን ባይረጋገጥም።

በ2018 የኮሪያ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጉብኝት ካመሩት የኪም ቤተሰቦች ውስጥ የመጀሪያዋም እንደሆነች ይታወቃል።

በዚያን የጉብኝት ወቅትም ደቡብ ኮሪያዊያን ፈገግታ የማይለያት መሆኗን ከተመለከቱ በኋላ ቀጣይዋ የሰሜን ኮሪያ ንግስት እዚህ አለች ደግሞም እርሷ ነች ይሏት እንደነበርም መረጃዎች ያሳያሉ። በሌላ በኩል ደግሞ

ኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህቱን በጣም ይወዷታል ደግሞም በጣም ያምኗታል ነው የሚባለው። በሁለታቻው መሃል ያለው ግንኙነትም ፍፁም ሰላማዊ ስለመሆኑ ይመሰከራል።

ከ2021 ጀምሮ የሀገሪቱ ሁለተኛ አድራጊ ፈጣሪ የሚያደርጋትን ስልጣን ከወንድሟ ተቀብላለች።

ከዚያ በፊት የሀገሪቱ የሰራተኛ ፓርቲ የመረጃ ዲፓርትመንት ውስጥ የፕሮፓጋንዳ ስራዎችን ትሰራ ነበር።

በሰሜን ኮሪያ ሁሉም ዜጎች ያለመንግስታቸው ፈቃድ እና ትዕዛዝ ውጭ አንዳች ነገር ማድረግ እንደማይችሉ ይታወቃል።

መሳቅም፤ማልቀስም በትዕዛዝ እንደማለት ነው። እዚህ በሮች ሁሉ ዝግ ናቸው። መንግስታዊ ስልጣንም ከአባት ወደልጅ ከላይ ወደታች ነው የሚወርደው።

ኪም በድንገት የሉም ብለን ብናሳብ ልጃቸው ወይንስ እህታቸው እሳቸውን ይቸኳቸዋል ወይ የሚለው ቀላል እንደማይሆን ማሳያዎች አሉ።  (በአብርሃም መካንንት)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe