‹ከአሰልጣኝነት ለመልቀቅ የወሰንኩት ለጨዋታ ከመሄዴ በፊት ነው›

ላለፉት ሁለት ዓመት ከሰባት ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን የሰራው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በራሱ ፈቃድ መልቀቂያ ማስገባቱ የሰሞኑ አነጋጋሪ አጀንዳ ነበር፡፡ በወር 250 ሺ የተጣራ ደሞዝ ያገኝ የነበረው ውበቱ 24 ጨዋታዎችን አድርጎ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ቢሸነፍም የዓመታት ባላንጣችን የሆነችውን ግብፅን በጨዋታ ብልጫ 2ለ0 ማሸነፉ የምንግዜም ታሪኩ ሆኖ ተመዝግቧል፤ በቻን የአፍሪካ ዋንጫና በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳትፎ ያልዘለለ ውጤት ያስመዘገበው ውበቱ በመገናኛ ብዘሃን ባለሙያዎች የተቀናጀና የተናበበ ዘመቻ እንደተከፈተበትና ሀላፊነቱን ለመልቀቅ ምክንያት እንደሆነው ከሁሉ ስፖርት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ላይ ተናግሯል፤ ‹የብሔራዊ ቡድን ያህል አስልጣኝ ሆነህ በሚዲያ ላይ ስብዕናን የሚነካ ስድብና ቤተሰብን የሚያሸማቅቅ ጸያፍ ንግግር ሲደረግ ከለላ የሚያደርግ ተቋም የለም› ይላል፡፡

 • ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በቅርቡ ለቀሃልና አሁን ያለህበት ስሜት ምን ይመስላል?

ውበቱ፡- አሁን እረፍት ላይ ነኝ ያለሁት፤ ከብሔራዊ ቡድኑ ሃላፊነት ከተለያየሁ አሁን አንድ ሁለት ሳምንት ሆኖኛል፤ ወደ ኖርማል ህይወት ተመልሻለሁ፤ ከቤተሰቦቼ ጋር እየተዝናናሁ ነው፤

 • ከብሔራዊ ቡድኑ በመልቀቅህ የተለየ ስሜት ፈጥሮብሃል?

ውበቱ፡- ከብሔራዊ ቡድኑ ለመልቀቅ ስወስን ነበር ከባዱ ነገር፤ ለረጅም ዓመታት እግር ኳስ ተጫውተህ ልታቆም ስትወስን፤ ወይም አንድ ቤት ላይ ረጅም ዓመታት ኖረህ ለመልቀቅ ስታስብ ነው ከባዱ ስሜት፤ እኔ አስቤበት አውጥቼ አውርጄ የወሰንኩት ውሳኔ ስለሆነ አሁን ያ ስሜት የለም፤ በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት ቦታ ስትገባ አንድ ቀን ልትወጣ እንደምትችል ታውቀዋለህ፤ አንድ ቦታ ላይ ረጅም ዓመት የሚቆዩ አሰልጣኞች ቢኖሩም ብዙ አይደሉም፤ አብዛኛዎቹ አንድ ክለብ ይይዛሉ ከእዛ ይለቃሉ፤ ይሄ ያለ ነበር ነው፡፡

 • እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስከው ምናልባት የኢትዮያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደማያልፍ አውቀህ ተስፋ ስለቆረጥክ ነው ለማለት ይቻላል?

ውበቱ፡-  በህይወቴ ተስፋ ቆርጩ አላውቅም፤ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በእግር ኳስ ሙያዬ ብቻ ሳይሆን በህይወቴም ተስፋ ቆርጩ አላውቅም፤ በስራና በህይወት ከፍና ዝቅ እንዳለ ይታወቃል፤በስራህ የምትፈተንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፤ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር በእኔ ውስጥ የለም፤ የእግር ኳሱ ሂደት እንደዚህ አይነት ውሳኔ ለመወሰን ያበቃሃል፤

 • ምናልባት ቀጣዩ የቡድኑ ጨዋታ ከግብጽ ጋር ስለሆነ ፈርቶ ነው፤ ታሪኬን ጠብቄ እንዳሸንፍኩት ላቁም ብሎ ነው መባሉስ?

ውበቱ፡- እንደዛ ሲባልም ሰምቻለሁ፤ እንደዛ አይነት ሰው አይደለሁም፤ ከአሁን በፊትም ተናግሬያለሁ፤ በምሰራው ስራ እኔ የመጀመሪያው፤ እከሌን ያሸነፍኩ፤ ብቸኛው ምናምን ማለት አልወድም አላውቅበትም፤የእዛ አይነት ፍቅር ያለኝ ሰው አይደለሁም፤ እኔ ዝም ብዬ ስራዬን እየሰራሁ መሄድ ነው የምፈልገው፤ውድቀቴንም ስኬቴንም የእኔነው ብዬ ስራዬ ብዬ ነው የምቀበለው፤ የስራ አካል ነው፤መሸነፍም ማሸነፍም ያለ ነገር ነው፤ እንደዛ አይነት ሰው ብሆን ኖሮ ግብፅን እንዳሸነፍን በነጋታው መልቀቅ ነበረብኝ፤ እንደውም ከግብፅ በኋላ አራት ጨዋታ ከሜዳችን ውጭ ተጫውተን አሸንፈን አልፈናል፤ እንደውም አስቀጥሉኝ ብዬ የጠየቅሁት እኔ ነኝ፤ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈናል፤ለቻን አፍሪካ ዋንጫ አልፈናል፤ ያ ግን ብቻውን በቂ አይደለም፤  በውስጤ የሌለኝ ነገር ቢኖር ፍራቻ ነው፤ የማይፈራ ሰው አለ ወይ ሊባል ይችላል፤ ትክክል ነው፤ ላይኖር ይችላል፤  በእግር ኳስ ግን ፈርተህ የትም አትደርስም፤ ያ ከሆነ ሀላፊነት መቀበል አትችልም ማለት ነው፤ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ብቻ ለመጫዋወት አሰልጣኝ ልትሆን አትችልም፤ ምዕራብ ፍሪካዎቹ እንደነ ናይጄሪና ሰሜን አፍሪካዎቹ ጋር ልትገጥም ትችላለህ፤ ከጋና ከቡርኪና ፋሶ ጋር ተጋጥመናል፤

 • የጊኒው ጨዋታ የተገኘው ውጤት ሽንፈት ባይሆን መልቀቂያውን ታስገባ ነበር?

ውበቱ፡- የምታውቃቸው ተጫዋቾች ካሉ መጠየቅ ትችላለህ፤ ከእዛ ጨዋታ በኋላ ተሸክሜ የቆየሁትን ነገር ይዤ ለመቀጠል እንደማልፈልግ ወስኛለሁ፤ በህይወትህም ብዙ ነገሮችን ችለህ ኖረህ በመጨረሻ ከዚህ  በላይማ የምትለው ነገር አለ፤ በህይወቴም በጣም ታጋሽ ነኝ፤ ብዙ ነሮችን ላልፍህ እችላለሁ፤ ያ ሰዓት ሲመጣ ግን እቆርጣለሁ፤ ከመሄዴ በፊትም ለቅርብ ልጆች ተናግሬያለሁ እንደማቆም፤ ፈጣሪ ውጤቱን ያሳምረው እንጂ ከዚህ በኋላ ብሔራዊ ብድኑን ይዤ አልቀጥልም ብዬ ተናግሬያለሁ፤

 • ግን በእዛ ሰዓት ተገቢ ነው እንደዛ ማለት?

ውበቱ፡- አይደለም፤ ይሄን እኮ በጣም ለምቀርባቸውና አንዳንድ ነገሮችን ለማናወራቸው የቡድኑ የቅርብ ልጆች ነው እንጂ የተናገርኩት ለሁሉም አይደለም፤ በቃ ከዚህ በኋላ እስኪ ወጣ ብዬ ደግሞ ልመልከት ነው  ያልኩት፤ እና ስለተሸነፍኩ አይደለም ያንን ውሳኔ የወሰንኩት፤ መሸነፍ ቢሆን ከእዛ በፊትም እኮ ሌላ ጨዋታ ተሸንፈናል፤

 • ግን በግልጽ እንነጋገርና ውበቱ አባተን እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው ነገር ምንድነው?

ውበቱ፡-  ከዚህ በፊት ተናግሬያለሁ፤ እዛ ቦታ ሆኜ ድጋፍ አላገኝንም ነበር፤ ድጋፍ ስልህ ቡድኑን የሚደግፍ ደጋፊ የለም እያልኩህ አይደለም፤ ስፖርቱ በቀጥታ የሚመለከተው አካል እየደገፈኝ ነበር ብዬ ለመናገር አልችልም፤

 • ያ አካል ማነው? ፌዴሬሽኑ ነው?

ውበቱ፡- ፌዴሬሽኑ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከጎኔ ነበር፤   እዛ ቦታ ላይ ሆነህ ሀገርን የወከለ ቡድን ይዘህ ስለምትናገረውና ስለምታደርገው ነገር ጥበቃ ከለላ ሊደረግልህ ይገባል፤ ያ አልነበረም፤ ጥበቃ ስልህ ትችት ሰዎች ለምን ይተቹኛል እያልኩ አይደለም፤ ትችት ብተች ችግር የለብኝም፤ ግን ስክሪን ዘርግትህ፤ መረጃ ይዘህ የቡድኑን አጨዋወት አንድ ሁለት እያልክ ብታሳየኝ ደስ ነው የሚለኝ፤  ከእዛ ውስጥ መቀበል ያለብኝ ነገር ካለ መማር ያለብኝ ነገር ካለ እቀበላለሁ፤ ግን ከእዛ ውጪ የሆኑ ስድቦች ክብረ ነክ ንግግሮች ሲመጡ  ያበሽቅሃል፤የትኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሆነ ስሙን አልጠቅስም እንጂ የሆነ ቴሌቨዥን ፕሮግራም  የስፖርት ፕሮግራምን ለመክፈት ስፈልግ እኮ መጀመሪያ ልጆቼን ‹በሉ ወደመኝታ› ብዬ አስተኝቼ ነው የምከፍተው፤ይህን ያህል ያሳቅቅሃል ስድቡ፤ ልጆቼ ስድብ እንዲሰሙ አልፈልግም፤ አባታቸው ሲሰደብም መመልክከ የለባቸውም፤ማንጓጠጥና ማሸማቀቅ ነው የምትሰማው፤ ከዚህ ሁሉ አልፎ ደግሞ ራሳቸውን እንደ ስፖርት ኤክስፐርት በመቁጠር ‹እከሌን ስናሸንፍ እኛ ነን የአሰላለፍ ስታይሉን ያወጣነው› ምናምን  ሲሉ ትሰማለህ፤ እዚህ ደረጃ የደረሱ አካላት አሉ፤ አንዳንዴ እጅህን ጠምዝዘው በስራህ ጣልቃ ሊገቡ ይሞክራሉ፤ እምቢ ስትል ደግሞ በየዕለቱ ጣቢያ እየቀያየሩ ይዘምቱብሃል፤ እዚህ ጋር ስትቀመጥ እኮ ግለሰባዊ ሃላፊነት ቢሆንም ሀገርን የምታገለግልበት ቦታ ነው፤ ይሰለቻል በዚህ ደረጃ እየተዋረድክ በሚዲያ ችለክ ብለህ መቀመጥ ይሰለቻል፤አስፈላጊም ነው ብዬ አላምንም፡፡

 • ሃላፊነት ከወሰድክ ግን መጠየቅ የለብህም፤

ውብቱ፡- ከሃላፊነት አንጻር ካየኸው መጠየቅ የለብኝም ልልህ እችላለሁ፤ ምክንያቱም እኔ በቆታዬ 24 የነጥብ ጨዋታ ነው ያደረግሁት፤ ከዚህ ውስጥ ሃያውን ጨዋታ የተጫወትነው ከሜዳ ውጪ ነው፤ የግድ ውጪ መጫወት ያለብን ጨዋታዎች እንዳሉ ሆነው ማለቴ ነው፡፡ ይሄ የሆነው በምናውቀው የሜዳ ችግር ሳቢያ ነው፤ እና ይሄንን እያወቅህ በዚህ ደረጃ ሊዘመትብኝ ይገባል ወይ? ከዚህ በፊት የነበረውን የብሔራዊ ቡድናችን ታሪክ ይታወቃል፤ ጨዋታዎች እዚህም ውጪም ነበር የሚካሄዱት፤ይሄንን እያወቁ የሚያደርጉ ሰዎች ቁማሩን እየተጫወቱ ያሉት ሀገር ላይ መሆኑን አለማወቃቸው ነው ችግሩ፡፡ በእዛ ላይ ተጫዋቾቹን የማገኛቸው ቢበዛ ለአስር ቀን አለበለዚያም ለሰባት ቀን ነው፤ በዚህ አስር ቀን ውስጥ ልጆቹን አግኝተህ ምን ተአምር እንድትሰራ ይጠበቃል? የሚነፃጸር አይደለም ፍላጎቱ፤ ለምን ጋናን አላሸነፍንም፤ ለምን ካሜሮንን አላሸነፍንም ትባላለህ? ብናሸነፍ ጥሩ ነው፤ ግን እንዴት ሰርትን መቼ ተገናኝተት ነው የምሸንፈው፤ ከተጫዋቾች አንፃርም ሽመልስ በቀለ ብቻ ነው ከሀገር ውጪ ግብጽ የሚጫወተው፤ ሌሎቹ በሙሉ በሀገር ውስጥ ክለብ ላይ የሚጫወቱ ናቸው፤ ተጋጣሚዎቻችንን ስታይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ፕሮፌሽናል ናቸው፤ ከእናማን ጋር ነው የምንጫወተው የሚለውን ማወቅ ይጠይቃል፤ የሊቨርፑልና የቫሌኒሺያ አማካይ ተጫዋቾች አይደሉም እንዴ የጊኒ ብሔራዊ ቡድን አንቀሻቃሾች? ያም ቢሆን ያንን ጨዋታ ውጤት ለማጥበብ ብዙ ሰርተናል፤ጫናው በብዙ ቢሆንም ማላቴ ነው፤

 • ውል ከፌዴሬሽኑ ጋር ስትዋዋል ከሜዳ ውጭ እንደምትጫወት ታውቃለህ አይደለም እንዴ?

ውበቱ፡- በተፃፈው ህግ መሠረት ከሆነ ሀላፊነቱ የእኔ ነው፤ ግን ያልተፃፈውስ ጫና? ግን ከ24 ጨዋታ 20 ጨዋታ ከሀገር ውጭ መጫወት ከባድ አይደለም ወይ?በልጆቹ ስነልቦና ላይ ያለውስ ጫና ታይቷል ወይ ነው ጥያቄው፤

 • ጊኒም እኮ ከሜዳዋ ውጭ ነው የተጫወተችው አይደል?

ውበቱ፡- ትክክል ጊኒም ከሜዳዋ ውጭ ነው የተጫወተችው፤ ይህ እኮ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ ክርስቶስ የተናገረውን ነገር ያስታውሰኛል፤ ባለፀጎች ለቤተክርስቲያን ካላቸው ላይ ሲሰጡ አንዲት እመበለት ግን ያላትን አስር ሳንቲም ነበር የሰጠችው፤ ታዲያ ክርስቶስ ምን አለ? ከሁሉ አስበልጣ የሰጠችው እሷናት አለ፤ እኛና እነሱ በምን እንነፃፀራለን፤ ቅድም እኮ እንዳልኩት የእነርሱ ተጫዋቾች ውጪ ሀገር በመጫውት ልምድ የያላቸው ናቸው፤ ልዩነታች የትና የት ነው፤ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ መጫወትና ውጭ መጫወት እንዴት ነው ለልጆቹ ስነልቦና አንድ አይነት የሚሆነው፤እኔ እኮ አሁን ለቅቄያለሁ አይደል፤ ለቀጣዩ አሰልጣኝ ይሄ ሁሉ ነገር ከግምት ሊገባልት ይገባል ነው የምለው፤ ሜዳችን በአስቸኳይ ተጠናቆ ጨዋታዎች ወደ ሀገር ቤት ሊመለስ ይገባል፤ ትልቅ ጫና አለው፤

 • ከሚዲዎች ጋር ያለው ጫና ከፍተኛ ነው ብለህ ነበር፤ ውበቱ እንዲህ አይነት ጫናዎችን ተቋቁሞ የማለፍ አቅሙ ደካማ ነው ማለት ነው?

ውበቱ፡-ብዙ ጫና ተቋቋምኩ እኮ፤ ሁለት ዓመት ከሰባት ወር ነው የቆየሁት በአሰልጣኝነት፤ ከቅጥር እስከ ለቀቅሁበት ዕለት ድረስ በጫና ውስጥ ነበርኩ፤የቅጥር ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጠሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ለቀቅሁበት ዕለት ድረስ ስድብ አልቆመልኝም፤አሁን ከወጣሁን በኋላም ቀጥሏል፤አሁን ነፃ ነኝ፤ በፊት እንደዛ የሚናገሩኝን ሰዎች እዛ ቦታ ላይ ሆኜ መናገር አልችልም፤ የሀገር ክብር የሚባል ነገር አለ፤ አሁን ግን ነፃ ስለሆንኩ እንደፈለኩ መናገር እችላለሁ፤ ግን እንደእነሱ መውረድ ስለሆነ ነው አሁንም ዝምታ የመረጥኩት፤ እኔ ራሴን ፕሩፍ ያደረኩ ሰው ነኝ፤ አብርሃም ትልቅ አሰልጣኝ ነው፤ የአፍሪካ ኢንስትራክተር ነው፤ ፕሩፍ አድርጓል፤ አንተ ማን ሆነህ ነው አብርሃምን ወይም እኔን እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ የምትለው፤አትችልም፤ እኔ ከታች ከፖሊስ ጀምሮ ብዙ ክለቦችን ይዤ ልምድ ቀስሜ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስኩት፤ ከሀገር ውጭ ሁሉ ሰርቼ ነው የመጣሁት፤ አንተ ውጤት አመጣለሁ የምትል ከሆነ ሰርትህ አሳይ ነው የምለው፤ እንደማንኛውም ቀና ሰው እንዲህ ቢሆን እንዲህ ቢሆን ብለህ ሀሳብ ልትሰጠኝ ትችላለህ፤ ግን የጨዋታውን አካሄድ ትልመራ ተጫዋች ልትመርጥልኝ ግን አትችልም፤ ከእኔ አልፎ ቤተሰብ መሳደብ እኮ ጫና ብቻ አይደለም፤ ብልግናም ነው፤

 • የዚህ አይነት አስተያየት የሚሰጡት ሰዎች ግን ሆን ብለው አንተን ለመጎዳት ነው ወይስ ባለማወቅ ነው ብልህ ታምናልህ?

ውበቱ፡- አንዳንዶቹ  ሳያውቁ ሀገራቸውን የጠቀሙ እየመሰላቸው የሚናገሩ አሉ፤ ሲናገሩ ግን ሰውን የሚናገሩበት ቋንቋ ሰውን የሚጎዳ የማይመስላቸው አሉ፤  ለምሳሌ የቀጥታ ጨዋታ ሲያስተላልፉ የእነ ደምሴ ዳምጤን ጎርፍነህ ይመርን ድምፅ እኮ አሁንም ድረስ እናስታውሳለን፤ እኔ ጨዋታ እየመራሁ የሬዲዮ ዘገባውን ላልሰማ እችላለሁ፤ ግን በምንም መልኩ የሀገርህ ብሔራዊ ብድን ላይ ጎል ሲገባ ልትደሰት አይገባም፤ አንዳንዶአቹ እኮ እኛ ላይ ጎል ሲገባ ስሜታቸውን መቆጣጠር ይሳናቸዋል፤ ከደስታ ብዛት ማለት ነው፤ ከእዛ ከእኔ ጋር ችግር ስላላቸው የሚሰጡት አስተያየት እየተነገረው እከሌን አስወጥቶ እከሌን አስገብቶ ይሉሃል፤እነዚህ የመጀመረሪዎቹ ናቸው ከማያውቁት ጎራ እመድባቸዋለሁ፤ ሁለተኛዎቹ ግን እኛ ነን  የምናውቀው እግር ኳስ፤ እኛ ካልሰራነው እግር ካስ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም የሚሉ አሉ፤ እነሱ አሰልጣኝ የመሆን ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፤ ያ ችግር የለውም፤ ግን ያንን ቦታ የሚፈልጉት ከሆነ እንደማንኛውም ሰው ሰርተው ቦታውን ለማግኘት መጣር ነው፤ አንተ በያዝከው ሃላፊነት ላይ ግን የራሳቸውን ፍላጎት ሊጭኑብህ ይፈልጋሉ፤ በራስህ መንገድ ስታሸንፍ እንኳ በአጋጣሚ ነው ብለው የሚያጥሉ ናቸው፤ ሀገር የሚቅም እስከ ሆነ ጊዜ ድረስ ማንም ጥሩ ነገር ቢናገር ልቀበለው እችላለሁ፤ አይቬሪኮስትን እኮ ያሸነፍነው እኛ ነን፤ እኛ ዲዛይን ባደረግነው መልኩ ስለተጫወቱ ነው ብለው የተናገሩትን ሰምቻለሁ፤ በኋላ ላይ ደግሞ አብረን እንስራ የሚልጥያቄ ይዘው መጡ፤

 • ያንተ ምላሽ ምን ሆነ?

ውበቱ፡- እኔማ ያንን ሁሉ ሲሉ ቆይተው እንዴት ነው አብረን የምንሰራው፤ እኔ አብረውኝ የሚሰሩትን እነ አስራትን እነ ደሳለኝን እነ አንዋርን መርጫለሁ ብዬ ነው የመለስኩላቸው፤ ፍላጎቱ ካላቸው እኮ ጋዜጠኝነትን ትተው አሰልጣኝ ሆነው ሰርተው ማሳየት ይችላሉ፤ ዛሬ እኮ ዘመኑ የውድድር ነው፤ ያለህን ሰርተህ አሳይና ነው የምትመረጠው፤

 • ስለዚህ ልዩነታቹህ እየሰፋ የመጣው አብረን እንስራ ብለውህ አንተ አልፈልግም በማለትህ ነው?

ውበቱ፡- ትክክል እንደዛ ነው፤ አለበለዚያማ በየዕለቱ የሚዲያ አፍ ማሟሻ አልሆንም ነበር፤ በእኔ ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ ማድረስ ሲያቅታቸው ደግሞ አሁን ከተጠየቅን አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን የሚል መግለጫ ሲሰጡ ሰምቻለሁ፤ ጥሩ እኔ አያስፈልገኝም የእነርሱ እርዳታ፤ ግፋ ቢል ዘመቻቸው የሚያመጣው ነገር ከብሔራዊ ቡድኑ መልቀቅ ነው፤ የክለብ አሰልጣኝ ብሆን ማንም ዝም አይላቸውም፤ የክለቡ ደጋፊ አፋችሁን ዝጉ ከክልባችን ላይ እጃችሁን አንሱ ይላቸዋል፤ ብሔራዊ ቡድኑ ግን ባለቤት የለውም፤ ተቆርቋሪ የለውም፤ ለዚህ ነው ማንም እየተነሳ የሚፈነጨው፤ ቀጣዩ አስልጣኝም ይሄ ነው ዕጣ ፈንታው፤ እምቢ ካለ ዘመቻ ይከፍቱበታል፤ በአንድ በኩል ጋዜጠኛ ነኝ ብለው ሚዲያውን ይዘውታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተጫዋች ኤጀንት ነኝ ብለው ተጫዋች ያዛውራሉ፤ ያንን ተጫዋች አንተ እንድታሰልፍላቸው ይጠይቃሉ፤ እምቢ ስትል ዘመቻ ይከፍቱብሃል፤ ይሄ ነው እየሆነ ያለው፤ ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ነገር ሲሆን የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ማህበር የት ነው? የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማህበር የት ናቸው?

ውበቱ፡- ስለዚህ ለውጤቱ መጥፋት ሚዲያው ተጠያቂ ነው ማለት ነው?

ውበቱ፡- አንዱ ችግር ናቸው፤ ጠያቂዎችም፤ መላሾችም፤ አስተያየት ሰጪዎችም፤ አስልጣኝ እንሁን ባዮችም ናቸው፤ አሁን መንግስት ከስልጣንህ ልቀቅና እኛ እንምራ ወይም እኛ በምንሰጥህ መንገድ ብቻ ተጓዝ ቢሉት ይያደርገዋል እንዴ? እንዳዛ ካልሆነ ነው እየተባለ ነው፤

 • ከግብፅ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ ያስመዘገባቸውን ውጤት የተመለከቱ ሰዎች የግብጽ ውጤት በዕድል የተገኘ ነው ይላሉ ምን ትላቸዋለህ?

ውበቱ፡-ምንም አልላቸውም፤ከግብጽ በኃላና በፊት ያለውን ቪዲዮ ማየት ያስፈልጋል፤ ካለኝ እኔ  ልሰጥህ እችላለሁ፤ ከግብጽ በኋላ ከማላዊ ጋር ተጫውን 2 ለ1 ተሸንፈን ነበር፤ ነገር ግን ጨዋታችን ጥሩ ስለነበር እዛ ማላዊ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለቡድኑ አጨዋወት በጣም ተገርመው ነበር የሚያደንቁት፤ እንደውም ይህንን ጨዋታ ከግብጽ ጋር ደግማችሁት ብትሸነፉ ሊቆጫችሁ አይገባም  ነበር የሚሉት፤ ከእዛ በኋላ ደግሞ የተጫወትነው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ነው፤ አራት ተጫውተን ሁለት ተሸነፍን ሁለት አሸነፍን፤ ጨዋታችንን ቪዲዮ ስላላ መመልክት ይቻላል፤ አጋጣሚ ነው ልትለው የማትችለው ጨዋታ ነው፡፡

 • ጌታነህ ከበደ ጋር ያለህን ልዩነት ለማጥበብ ሽማግሌ ልከህ እንደነበር ይነገራል፤ እውነት ከሆነ የእርሱ ምላሽ ምን ነበር?

ውበቱ፡-ድሬዳዋ ላይ እያለን የቡድኑ ወጌሻ ይስሃው ጠርቶኝ በጌታነህ ጉዳይ እንነጋገር ብሎኝ ቁጭ ብለን አውርተናል፤ ሀሳቡን የመጣው በይስሃቅ ነበር፤ይስሃቅንም ጌታነህም አመሰግናለሁ፤ ይሄ የሆነው መቼ ነው? አንድ ጊዜ ትቼው ወደውጭ ሄጄ አኩርፎ ነበር፤ ለእዛ ጉዳይ ነው ቁጭ ብለን ያወራነው፤ እኔም ጠይቄ እንነጋገር ብል ምንም ችግር አልነበረውም፤አርፍዶ ከመጣ በኋላ ልምምድ ላይ ከቀነስኩት በኋላ ሽማግሌ የሚባል ነገር አልነበረም፤ እኔ ሌላ ጠብ ማንም ጋር የለኝም፤ ጌታነህንም በጣም የምወደው ተጫዋች ነው፤ ከደደቢት ጀምሮ ያሰለጠንኩት ልጅ ነው፤ በጣም ቡድኑን ያገለገለ ነው፤ አምበል ነው፤ ብዙ ጎል አግብቶልናል፤ ግን ዲስፕሊን ለማንኛውም ተጫዋች ያስፈልጋል የሚል እምነት ያለኝ ሰው ነኝ፤ ከእዛ ብሔራዊ ቡድን አልጫወትም ብሎ መግለጫ የሰጠውን አየሁ፤ ግን ለሀገር ያስፈልጋል ብዬ ስላመንኩ የመጨረሻ ጥሪ ከማድረጌ በፊት ላናግረው ስልክ ደወልኩለት፤ መቼም አንድ ሰው ብሔራዊ ቡድን አልጫወትም ብሎ መግለጫ ሰጥቶ አትጠራውም፤ እኔ ግን ሌላ ሰውም አማላጅ ብዬ አናግሩት አላልኩም ራሴ ነኝ ስልኬን አንስቼ የደወልኩለት፤ ስልኬን አልመለሰም፤  አጠገቤ ብቻዬንም አልነበርኩም አቶ ኢሳያስ ጂራ ፕሬዚዳንቱ ባለበት ነው የደወልኩለት፤ ምክንያቱም ሀገርም ህዝብም ከሁላችንም በላይ ናት የሚል እምነት ነው ያለኝ፤ አቶ ኢሳያስ ባለበትም ስልኬን አላነሳም፤ ከእዛ በኋላ ነው ለሌሎቹ ጥሪ ያስተላለፍኩት፤

– እንደ ውበቱ ነገሮች ቢመቻቹልን የተሻለ ውጤት እናስመዘግብ ነበር የሚሉ አሰልጣኞች እንደዳሉ ይነገራል፤ ምን ትላለህ?

ውበቱ፡-ያድርግላቸው ነው የምለው፤ ይቅናቸው ነው የምለው፤

 • ከብሔራዊ ቡድኑ ለመልቀቅ ወስነህ ነገር ግን ከሌሎች ክለቦች ጋር ትደራደር ነበር ይባላል፤ እውነት ነው?

ውበቱ፡-እውነት አይደለም፤እንደዚህ አይነት ነገር በህይወቴ አድርጌ አላውቅም፤ አንድ ቦታ ሆኜ ሌላ ክለብ ጋር ድርድር የሚባል ነገር አድርጌ አላውቅም፤ እርግጥ ክረምት ላይ የብሔራዊ ቡድኑ ኮንትራቴ ስላልታደሰ አንዳንድ ክለቦች አናግረውኝ ነበር፤ብሔራዊ ቡድኑ ያስቀጥለኝ አያስቀጥለኝ የማውቀው ነገር የለም፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አውቃለሁ፤ እስከዛ ድረስ ግን ታገሱኝ ያልኳቸው ክለቦች ነበሩ፤

 • በሚዲያ ላይ ያለብህ ጫና ትላልቅ ክለቦችን እንዳትይዝ ተፅእኖ ይፈጥርብኛል ብለህ ትሰጋለህ?

ውበቱ፡- እንደውም ትልልቅ ክለቦችን ነው የምይዘው፤ በክለቦች ላይማ ተፅእኖ መፍጠር አይችሉም፤ ሲጀመር ቅድም እንዳልኩህ ክለብ ባለቤት ደጋፊ አለው፤ ዝም አይልም፤ትልቅ ክለብ ትልቅ ደጋፊ ስላለው ድጋፍ ታገኛለህ፤ ከለላ አለህ፤ ብሔራዊ ቡድኑ እኮ የሁላችንም ነው በሚል ነው ማንም እየተነሳ የሚሳደበው፤

 • ከዚህ በኋላ ድጋሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንድትሆን ብትጠራ ትቀበላለህ?

ውበቱ፡-ቅድም ያልኩህ አይነት ጫናዎች ባሉበት ሁኔታ አልቀበልም፤ የወጣሁበት ሁኔታ ባልተቀየረበት ሁኔታ ምን ልሰራ ድጋሚ እመለሳለሁ፤ ሀገርን ማገልገል ጥሩ ነው፤ ግን በዚህ መልክ መሆን የለበትም፤

 • በቀጣይነት ለሚመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ምን ትመክረዋለህ?

ውበቱ፡- እንግዲህ ማን እንደሆነ በትክክል አላውቅም፤ ግን በሩመር ደረጃ ሲነገር ሰማሁት አለ፤የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆን ማለት ትልቅ ነገር ነው፤ ወደእዚህ ቦታ ሲመጣ ሁኔታውን ያጣዋል ብዬ አልገምትም፤ ግን ከባድ ቻሌንጅ ሊገጥመው ስለሚችል መዘጋጀት ይኖርበታል፤ ከዚህ ውጪ የሚመጣው አሰልጣኝ እድለኛ ነው አሁን፤ ምክያቱም ብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ሀገር ሄዶ ሲጫወት ሊሸነፍ ይችል ይሆናል፤ ግን የሚያሸማቅቅ አይነት ሽንፈት እንደማይሸነፍ ማሳየት ችሏል፤ ማሸነፍም እንደሚችል አሳይቷል፤ሌላው የተጫዋቾች ዝግጅት ሰፊ ጊዜ የለም ፤ አጭር ቀን ነው ለእዛ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤መልካም እድል ነው የምመኝለት፤

-በመጨረሻ ማለት የምትፈልግው ነገር ካለ?

ውበቱ፡- በቆይታዬ በርካታ ሰዎችን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ፕሬዚዳንቱን አቶ ኢሳያስ ጂራን፤ በጣም አጋዤ ነበር፤ የኮቺንግ ስታፍ በሙሉ አመሰግናለሁ እከሌ እከሌ ሳልል ፤ምክንያቱም ለስራው ሁሉም ቀናዎች ነበሩ፤ አንዳንድ ጊዜ እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ ስንወያይ እናመሻለን፤ቤተሰቦቼን ከእኔ ጋር ሲያዝኑና ሲደሰቱ ነበር፤ አብረውኝ ለነበሩ በሙሉ አመሰግናለሁ፤ክለቦችን ፤ ሊግ ካምፖኒውን አመሰግናለሁ፤አሰልጣኞችንም  የሚዲያ አባላትንም ቅድም የወቀስኳቸውን ጨምሮ አመሰግናለሁ ነው የምለው፡፡ አላግባብ ያስቀየምኳቸው ሰዎች ካሉም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

 • አመሰግናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe