ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ጋር የተወያዩ የለገጣፎ ተፈናቃዮች ጥያቄያችን መልስ አላገኘም አሉ

የለገጣፎ ተፈናቃዮች ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን ጋር ያደረጉት ውይይት ጥያቄያችንን የሚመልስ አይደለም አሉ፡፡ ‹‹እንወያይ ብለው ሲጠሩን መፍትሔ እናገኛለን ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ማፍረሱ ይቀጥላል ብለውናል፤›› ያሉት አንድ  ተፈናቀይ ‹‹ለምን እንደተጠራን አልገባንም፤›› ብለዋል፡፡

ከማስተር ፕላን ውጪ ናቸው ተብለው ይፈርሳሉ ከተባሉ 12,800 ቤቶች መካከል እስካሁን 3,800 ቤቶች መፍረሳቸውን የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ ቤቶቹ ከተገነቡ ከአሥር ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውን ያስረዳሉ፡፡ የቤት ቁጥር ተሰጥቷል የነዋሪዎች መታወቂያ ኖሯቸው እንደ ማንኛውም ሕጋዊ ነዋሪ የተለያዩ የመሠረት ልማት አውታሮች ተሟልተውላቸው ሳለ፣ ሕገወጥ ተብለው ቤቶቻቸው ፈርሰው መፈናቀላቸው አግባብነት እንደሌለው በተዘጋጀው መድረክ ቢገልጹም፣ አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ተፈናቃዮቹን የማይወክሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በውይይቱ እንዲሳተፉ ሲደረግ፣ ማኅበረሰቡ የወከላቸው ግን ፈቃድ የላችሁም ተብለው ወደ ስብሰባ አዳራሹ እንዳይገቡ በጥበቃ አካላት መከልከላቸውንም አስረድተዋል፡፡

በለገዳዲ 01 እና 02 ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ ተፈናቃዮችን እንደሚወክሉ የሚናገሩት አንድ ግለሰብ የሁለት ቀበሌዎችን 85 አባወራዎችን ወክለው በውይይቱ መድረኩ ለመሳተፍ ቢሄዱም፣ ከበር እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር የተወከሉ ሌሎች ተወካዮችም ፈቃድ የላችሁም ተብለው በጥበቃ እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ በተፈናቃዮቹ የተወከሉት በሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ ይሁንና ፈቃድ የላችሁም ተብለው እንዲመለሱ ሲደረጉ ኮሚቴውን የማይወክሉና ቤታቸው ያልፈረሰባቸው ሰዎች እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በለገጣፎ 03 ቀበሌ ሚሶማ ጉዲና በሚባለው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ 40 ተፈናቃይ አባወራዎችን ወክለው በውይይቱ ላይ መሳተፋቸውን የሚናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ ‹‹ጥያቄያችን አልተመለሰም፣ የማለባበስ ነገር ነው የተሠራው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሕጋዊ መረጃ እያለን ፈርሶብናል፣ በምንኖርበት ድንኳን ውስጥ እየገቡ ያስፈራሩናል፣ ምግብ የሚያቀርቡልንን ሰዎች ሳይቀር ያስፈራራሉ፣ አቤት ብንልም አጥጋቢ መልስ አላገኘንም፤›› ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡

‹‹አገራችን የሰው ልጅ ተነስቶ ዛፍ የሚቆምባት ምድር እየሆነች ነው፤›› የሚሉት የ01 እና 02 ቀበሌ ተወካይ፣ ተፈናቃዮች በአካባቢው በሚገኙ መጠለያዎች እንኳ ለመቆየት ችግር ገጥሟቸዋል ብለዋል፡፡

ሃምሳ ሁለት አባወራዎች በአካባቢው በሚገኝ መስጊድ ተጠልለው ይኖሩ እንደነበር፣ ከሳምንት በፊት ግን መስጊዱን ለቀው እንዲወጡ መደረጉን፣ በአሁኑ ወቅት በሜትር በ27 ብር ሒሳብ የገዙትን 50 ሜትር ሸራ ወጥረው ወንዶች እያደሩበት መሆኑን፣ ሴቶችና ሕፃናት በየሰው ቤት ለምነው እንደሚያድሩና 40 የሚጠቡ ሕፃናት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 120 የተፈናቃይ ቤተሰብ የሆኑ ተማሪዎች ከመፈናቀሉ በኋላ ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያቀርቡላቸውን ምግብ ይመገቡ እንደነበር፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ምግብ መቋረጡንና ተፈናቃዮች እየተራቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከቀይ መስቀል እንኳን ዕርዳታ አላገኘንም፤›› ሲሉ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ጠይባ በነዋሪዎቹ ላይ የመብት ጥሰት ባደረሱ የፀጥታ አካላት ላይ የማጣራት ሥራ ተከናውኖ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ሕገወጥ ግንባታዎች በመከናወናቸው በፊት ማስቆም ይሻል እንደነበር ገልጸው፣ በሕገወጥ ግንባታ ላይ በተሳተፉ የመንግሥት አካላት ላይም አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ለድርድር እንደማይቀርብ፣ የሕግ የበላይነትን የማስፈጸም ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በውይይቱ ወቅት ተደምጠዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ ያሉ ከተሞችን በፕላን እንዲመሩ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት የገጠር አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ በለገጣፎ የተወሰደው ዕርምጃ በሌሎች ከተሞች ከተወሰደው የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡ ነገር ግን አጋጣሚውን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የሚጣጣሩ አካላት እንቅስቃሴው ሌላ አጀንዳ ከበስተጀርባው እንዳለ አድርገው እያቀረቡ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚከናወነውን ሥራ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት ጉዳዩን የብሔርና የሃይማኖት መልክ እንዲይዝ እያደረጉ ነው ያሉት ወ/ሮ ጠይባ፣ ቤት ከፈረሰባቸው ዜጎች መካከል አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ የደሃ ደሃ ለሆኑት የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe