ከዘጠኝ መቶ በላይ በሚሆኑ ህገ-ወጥ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተደረገ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ በህገ ወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ 926 የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ቤቶች ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ጋር በመቀናጀት እርምጃ ተወስዷል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን እርምጃ በመውሰዱ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሲሆን በእነዚህ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ውስጥ ህገ ወጥ ተግባር እንደሚፈፀም እና በነዋሪዎች ላይ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሁከት እየፈጠሩ እንደሚገኙ በመግለፅ የህዝብ ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
ይህንን የህዝብ ቅሬታ መነሻ በማድረግ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በሰባት ክፍለ ከተሞች ላይ እርምጃ የመውሰድ ተግባር የተከናወነ ሲሆን በጉለሌ ክፍለ ከተማ 152፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 173፣ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ 167፣ በልደታ ክፍለ ከተማ 49፣ በየካ ክፍለ ከተማ 87፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 276 እንዲሁም በአቃቂ ክፍለ ከተማ 22 ህገ ወጥ የስፖርት ውርርድ ቤቶች እንዲታሸጉ ተደርጓል፡፡
ከሚመለከተው አካል የተሰጠ ህጋዊ ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ማጫወት፣ ዕድሜያቸው 21 አመት ያልሞላቸው ሰዎች እንዳይጫወቱ የሚከለከል ቢሆንም ይህንን ክልከላ ጥሶ መገኘት፣ ከትምህርት ቤቶችና ከእምነት ተቋማት አካባቢ እንዲርቁ የተቀመጠላቸውን የርቀት ወሰን ሳይጠብቁ ማጫወት እንዲሁም በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ጫት ማስቃም ከተፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ህጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው የስፖርት ውርርዱን የሚያካሂዱ ንግድ ቤቶች ቢኖሩም በህጋዊነት ሽፋን ህገ ወጥ ተግባር እየፈፀሙ በመሆኑ የህዝብን ሰላም የማስጠበቅ እና የወንጀል ስጋትን የማስወገድ ሃላፊነት የተጣለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ እርምጃው ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውሶ ህብረተሰቡ መረጃ እና ጥቆማ የመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ከቀናት በፊት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተመሳሳይ እርምጃ እንደተወሰደ መገለፁ ይታወሳል፡፡
ዘገባ፡- ሳጅን አምሳሉ መብራቴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe