ከደምቢድሎ የታገቱት ወጣት ሴቶች ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ገጽታና የማንቂያ ደወል

አክሊሉ ወንድአፈረው ethioandenet@bell.net
“እጅግ ተደናግጨ ራሴን መጠየቅ ጅመርኩ፣ በውነት ይህ ነገር በኔላይ ነው እየሆን ያለው? አዚህ ጫካ ውስጥ ምን አያደረግኩ ነው?እያልኩ ራሴ መጠይቅ ጅምርኩ። ድንገት ከፍተኛ ቅዝቃዜ ተሰማኝና ፣ ድንብርብር ባለ መንፈሰ ፣ ይሀን አላምንም በፍጹም ሊሆን አይችልም፣ ፈጣሪ ሆይ ይህ መቼም በኔላይ አይሆንም አያልኩ ማጉረምረም ጀመርኩ” አንድ ታጋች ሰለደረሰበት ከተናገረው የተወሰደ

በሀገራችን ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህግ የበላይነት ተጥሶ የህዝባችንም የህይወት ዋስትና አጅግ ተናግቶ ይገኛል። ዜጎች ከመኖሪያቸው በባለጉልበቶች ይፈናቀላሉ፣ ባንኮች በጠራራ ጸህይ ያላንዳች ከልካይ ይዘረፋሉ፣ ተማሪዎች በትምህርት ገበታችው ውስጥ በሌሎች ተማሪዎች ከፎቅ ተወርውረው ይገደላሉ፤ ዜጎች የዚህ ድርጅት ደጋፊ ነህ ተብለው ተዘቅዝቀው ተስቅልው በአሳት ይቃጠላሉ፣ ቤተ ክርስቲያኖች ያላንዳች ተው ባይ ይጋያሉ፣ አይነኬ የነበሩ ቀሳውስትን “አባሯቸው” አየተባለ በአድባባይ ይቀሰቀሳል፣ መስጊዶም እንዲጋዩ ይደረጋል፣ ይህን አሳፋሪ ተግባር የፈጸሙትም ጀብዱ አንደሠራ ሰው ሲጨፍሩና ሲፎክሩ ይታያል።

አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች የፈልጉት ነገር ካልተደረገ መንግሥትን ያስፈራራሉ፣ አስገድደውም የሚፈለጉትን ለማስፈጸም ይንቀሳቅሳሉ፡ የመንግሥትን አቅድ በጉልበት ያስቆማሉ፣ አንዳንድ ቦታ የአካባቢ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በሚዲያ በኩል ትዕዛዝ ሲሰጡ ይደመጣል፣ በየቦታውም ባለሥልጣኖችን ከሥራ አባርረው የፈልጉትን ይሾማሉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት በተለይም በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎችና ወንጀል ፈጻሚ ፖለቲከኞች ላይ ድምጹን አጥፍቶ አንዳልስማና እንዳላየ ሲሆን ይታያል፣ ወይም ድምጹን በለሆሳስ ከማስማት የዘለለ ጉዳይ ሲሠራ አይታይም፣ ወይም ያከናወነው ተግባር ለህዝብ በበቂ አይገልጽም።

ይህ ሁሉ ተጠራቅሞ ብዙዎችን በዚች ሀገር ውስጥ መንግሥት አለወይ?፣ መንግሥት ካለስ ስንት መንግሥት? ወደሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እንዲሄዱ አስገድዷል።

ከላይ የተጠቀሰውን የሀገራችን ሁኔታ በግንዛቤ ውስጥ አስግብቶ ለሚመለክት ነፃ አእምሮ፣ ታግተው አስካሁን (ከ 50 ቀን በላይ) መዳረሻቸው ያልታወቀው የደንቢዶሎ ዩኒቪርሲቲ ሴት ተማሪዎች ጉዳይ እጅግ አስጨናቂ፣ አሳፋሪና የሚረብሽም ነው። ይህ ሁኔታ ስለ ሀገራችን ሁኔታ ምን ያሳያል? የሚያስክትለው አደጋስ ምንድን ነው? የሚለውን ከተለያየ አቅጣጫ መመርመርና ተገቢ መፍትሄ መሻት እጅግ አጣዳፊ ተግባር ነው። ይህ አጭር ጽሁፍም በዚህ አኳያ ለሚደርገው ውይይት መንደርደሪያ ሀሳቦችን ያቀርባል።

እገታ አንደ ፖለቲካ ማሣሪያ
ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ የፖለቲካ ብሶትን ለማስማት፣ ዓላማን ለማሳወቅና የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ…ወዘተ ብዙ የፖለቲካ ኃይሎች አገታን አንደ አንድ ማሣሪያ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ይህ በአሜሪካም፣ በካናዳም፣ በአውሮፓም፣ በኤሽያና ደቡብ አሜሪካ አንዲሁም በአፍሪካችን የኛን ሀገር ጨምሮ የተከናወነ ተግባር ነበር።
እገታው አንዳንድ ጊዜ አይሮፕላንና ትሳፋሪዎችን መጥለፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አጋጣሚን በመጠቀም ትኩረት ሳቢ የሆኑ ዜጎችን ማፈንን ያካተተ ነበር። ከነዚህም ውስጥ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1968 የፓለስታይኑ ነፃ አውጪ ግንባር (Popular Front for the Liberation of Palestine ) የአስራኤልን አየር መንገድ ኢል አል (El Al ) እና ተሳፋሪዎቹ ላይ ያደረገው ጠለፋ፣ በ1972 ጥቁር መስከረም (ብላክ ሴፕተምበር) የተሰኘው የፓለስታይኑ ድርጅት በጀርመን ሚዩኒክ ኦሎምፒክ ዝግጅት ላይ የእስራኤል ስፖርተኞችን በማፈን ያደረስው ግድያ፣ በስሜን አየርላንድ፣ በአይ አር ኤ (IRA)፣ የጀርመኑ ሬድ ብርጌድ፣ በባስክ ስፔይን…ወዘተ የተካሄዱ ሁሉ አገታን አንደ ፖለቲካ መሣሪያ በመጠቀም ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከፖለቲካ ጋር ተዛምደው በተካሄዱ የግለሰብም ሆነ ስፋ ያለ የቡድን ጠለፋዎች ሲታስቡ የአፍጋኒስታኑ ታሊባን (Taliban,) የኢራቁና ሶርያው ኢስላሚክ እስቴት (ISIL) የዩጋንዳው ሎርድስ ሪዚስታንሰ አርሚ ( Lords Resistance Army)፣ የናይጀሪያው ቦኮ ሀራም፣ (Boko Haram) የጎረቤታችን ሶማሊያ አልሽባብና የመሳስሉት ያካሄዷቸው ሁሉ የሚጠቀሱ ናቸው።

እገታን አንደ ፖለቲካ መሣሪያነት የሚጠቀሙ ከፍሎች አንዱ ግባ የፖለቲካ ድርጅቶች በመንግሥት የታስሩ የድርጅቶቻቸውን አባላት ወይም ደጋፌዎች በልውውጥ ለማስፈታት፣ በድርጅቱ ላይ በመንግሥት የሚደረግን ጥቃት ለማስቆም፣ ወይም ቀዝቀዝ እንዲል ለማድረግ ታጋቾቹን በመደራደሪያነት ለማቅረብ የሚደርግ ሙከራ አንዱ ነው።

የደምቢደሎ ሴት ተማሪዎችን ጠለፋና እገታ ከላይ ከተጠቀሱት የተለያዩ ምክንያቶች አንፃር በመመርመር የሁኔታውን ምንነትና የተጋረጠውንም አደጋ ለመገንዘብ ዕድል ይሰጣል።ጠለፋው ተካሄደ የሚባልበትን አካባቢ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁኔታ ስንመርምር ደግሞ ጠለፋውን ሊያካሂዱ ከሚችሉ ክፍሎች ውስጥ የሚከተሉትን ማየት ይቻላል፡

በጃል መሮ የሚምራው አነግ ፡
ምንም አንኳ ብዙ ጊዜ ጠለፋን ለማካሄድ እጅግ ጠንካራ ድርጅትንና ጥልቀት ያለው እስትራትጂያዊ ጥናት ባያስፍልግም፣ በቁጥር ስፋ ያሉ ስዎችን ጠልፎ ከመንግስት ጥቃት እየተከላከሉ ከ 50 ቀን በላይ ለመቆየት አንጻራዊ ጥንካሬ ያለው ድርጅት ያስፈልጋል። ላልፉት 18 ወራት በጃል መሮ የሚምራው አነግ ውጭ በአካባቢው መሳሪያ ታጥቆ የሚንቅሳቅስ አንጻራዊ ጥንካሬ ያለው ድርጅታዊ ህይል እንደሌለ የሚታውቅ ነው።ከዚህ በተጨማሪም ፣ ይህ ድርጅት ባለፈው 18 ወራት ውስጥ በተለያዩ የባለስልጣኖች ግድያ፣ ጠለፋና በመሳስሉት ጉዳዮች ዋነኛው ተጠርጣሪ ሆኖ ቆይቷል። ከእነዚህን ሁሉ ጋር አያይዘን ሰንመለከትም ለጠለፋው በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ መንገድ ሽኔ በዋና ተጠርጣሪነት የሚታይ ይሆናል።

በርግጥም እነዚህ ሴት ወጣቶች የታገቱት በኦ ኤል ኤፍ (OLF ሽኔ ) ከሆን የዚህ ጠለፋ ያሁኑ ግብ ወጣቶች ከመታገታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ መንግስት በድርጅቱ ላይ የጀመረውን ወታደራዊ ጥቃት ለማስቆም ያስበ ነው ወደሚለው መደምደሚያ የሚያመላክት ይሆናል።

የሽኔ፣ የፖለቲካ አጀንዳ እጅግ ሰፊና ውስብስብ ሲሆን ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋውን በተመለከተም በአባ ገዳዎች፣ በሌሎች ፖለቲከኞችና ተጻእኖ ፈጣሪዎች ትብብር እስካሁን ግጭቱን የሚያስቆም አመርቂ መፍትሄን ማግኘት አልተቻለም። ሽኔ ደግሞ ደጋግሞ በሚያስማው ድምፅ የአለም አቀፉን ህብረተስብ (ሶስትኛ ወገን) ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ ነው። ይህም በመሆኑ ደርጅቱ ከሚሻው መፍትሄ ውስብስብነት አንጻር ሲታይ እገታው ረጅም ስላማዊ መፍትሄውም ሩቅ እንደሚሆን ይጠቁማል።

ሌሎች ተጸእኖ ፈጣሪዎች
በዚህ ጠለፋና እገታ ሌሎች ተጠርጣሪ ሊሆኑ የሚችሉ ክፍሎች ራሳችውን ልል በሆን መልክ በቡድን ያደራጁና በአካባቢው ሁኔታ ላይ የተለያየ ተጻእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለስቦችና ስብስቦች ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዛዋሪ ግንኙነት ሊኖራችው የሚችሉ አካባቢ በቀል ሀይሎች ናችው። የነዚህ ሀይሎች ዋና አላማ የፖለቲካ ውጥረትን በመፍጠር የተወሰን የፖለቲካ አጀንዳን ማራመድና የማይፈልጉትንም የመንግስት እርምጃ ማደናቅፍ ሊሆን ይችላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ውስጥ የመንግስትን ወይም የገዥውን ቡድን የተለያዩ አጀንዳዎች በጉልበትና የተለያዩ ቀወሶችን በመፍጠር ለማስቆም መሞከር (ማስቆም ) እየተለመደ አንደመጣ የሚታወቅ ሀቅ ነው። እገታው በተጠቀሱ ክፍሎች ቀጥተኛም ሆነ ቀጠተኛ ያልሆን ተእዛዝና ተጽእኖ የተፈጸም ከሆነ የአጋቾቹ ፍላጎት የፖለቲካ አጀንዳን ማስፈጸም ስለሆን ታጋቾቹን በድርድርና በስላም ብቻ ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት የማስግኘት አድል ቢኖረውም ቀላል አንደማይሆን ግን መገምት ይቻላል።

የአጠቃላይ አለመርጋጋትና ግጭት ተጠቃሚዎች
በሶስተኛ ደረጃ እገታው የአካባቢውንም ሆነ የመላ ሀገሪቱን መረጋጋት የማይሹ ፣ በተለያየ ምክንያትም ግጭት አንዲቀስቅስና እንዲስፋፋ የሚፈልጉ (የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ) ሀይሎች ረጅም አጅ ያለበት ሊሆን አንደሚችል መገመት ይችላል ። የነዚህ ሀይሎች እንቅስቃሴ ከመጀመሪያውም በበቂ ማቴርያል ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ሰለሚሆን ታጋዮችን ለማስለቀቅ በገንዝብ ሀይል ለማግባባት የሚችልበት ሁኔታ አጅግ ዝቅተኛ ነው።

ይህ ሁኔታ ከታጋቾች ማንነት አንጻር ሲመረመር በዋናነት ከአማራ ክልል በመጡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ምንም ግንኙንት በሌላቸው ሴት ወጣቶች ላይ ለምን አተኮረ ፣ የጠላፊዎች የፖለቲካ ችግር ከመንግስት ባሻገር ከአማራ ህዝብ ጋር ነውን? አላማቸው አካባቢውን አማራ ጠል አድርጎ ማሳየት ነውን ፣ በአማራውና ኦሮምኛ ተናጋሪው ህዝብ መህል ያለውን ግንኙነት ለማሻከር የተጠመደ ፈንጂ ይሆን ? ከዚህ ሁሉ ተጠቃሚውስ ማን ሊሆን ይችላል? የሚሉት ጥያቄዎች መነሳታችው የግድ ነው።

ጠለፋውም ሆነ እገታው ከተወስን የፖለቲካ አላማ ጋር ተያይዞ የተፈጸመ ሆነም አልሆነም ታጋቾች በመታገታችው ብቻ ከሚደርስባችው ስቃይ ባሻገር ለሌሎች ተጨማሪ አደጋዎችም ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ በተለያዮ ቦታዎች የተካሄዱ ተመሳሳይ እገታዎች አመላካች ናቸው።

አገታ አስግድዶ መድፈርና ሌሎች የስቃይ ተግባሮች (ቶርቸር)
ብዙውን ጊዜ እገታ የሚያካሂዱ ቡድኖች ወይም ግለስቦች አንዱና የመጀመሪያ አርምጃቸው ታጋቾችን በኃይለኛ ፍርሃት አንዲዋጡ፣ አጋቾቻቸው የሚሏቸውን ሙሉ በሙሉ አንዲፈጸሙ ይህን ካላደርጉም በራሳችውም ሆነ በሌሎች የሚያውቋችው ሰዎች ላይ የበለጠ አደጋ ይደርሳል ብለው አንዲያምኑ ማድረግ ነው። በሚወስዷችው አርምጃዎች ታጋቾች ሥነልቦናዊ ጥንካሬያቸው በአጠቃላይ ተሟጦ አንዲጠፋ የማምለጥም ሆነ ሌላ የአምቢታ ተግባርን ለመፍፀም የሚያስችል የፅናት ስሜታችው ሙሉ በሙሉ አንዲሰበር ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት በታጋቾቹ ላይ ሙሉ ቁጥጥርን ለማስፈን ነው።

ይህን ተግባራዊ ከሚያድርጉበት መንግዶች ውስጥ፣ አስቃቂ ድብደባና ሌሎች የግፍ ተግባሮች (ቶርቸር) መፈጸም ፤እንቅልፍ በመከልከል የአእምሮ ሁክትና በትክክል ማስብ አንዳይችሉ ማድረግ አልፎ ተርፎም አስግድዶ መድፈር፣ ዋነኛዎቹ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ከናይጀሪያው ቦኮ ሀራም አስክ ዩክሬይን፣ ከቦሊቪያ አስክ ህንድ፣ ኢራቅና ሶርያ የታየው የጠለፋና እገታ ታሪክ በአብዛኛው ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች አስቃቂ ተግባሮችን ያጠቃለለ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በሩዋንዳ፣ ቦዝንያና ሌሎችም ቦታዎች አንደታየው “የጠላትን ሴቶች” ከባለሥልጣናት አስከ ዘበኛ አስግድዶ መድፍር እጅግ የተዘወተረ ተግባር ነው፡፡ ተመሳሳይ መረጃ ለማየት የሚከትሉትን በመጫን ያንብቡ http://www.meredethturshen.com/www/pdf/WorldBankRapechapter.pdf
ከዚህ ለማስብ የሚከብድ ስቃይ በተጨማሪ አጅግ የሚዘገንነው ደግሞ አጋቾች በታጋቾች ላይ ከላይ የተጠቀስውን አሳፋሪ እርምጃ ከወስዱ በኋላ ታጋቾችን ለመልቅቀ የሚኖራቸው ፍላጎት እጅግ ዝቅተኛ አየሆነ የሚምጣ መሆኑ ነው። ይህ የሚሆነውም ታጋቾች ነፃ ቢሆኑ ስለደረስባቸው ግፍ ይናገራሉ፣ ይህም በወንጀል ተፈላጊነታችንን ከባድ ያደርግዋል፣ በኅብረተሰቡ ውስጥም ድጋፍ ያሳጣናል ብለው አጋቾች ሰለሚያስቡ ሲሆን ከዚህ አዘቅት ለመውጣት የሚከተሉት ጎዳና ብዙውን ጊዜ ታጋቶችን አንዳገቱ መቆየት ወይም ሚስጥራቸውን አንደያዙ በመግደል ወደተጨማሪ አዘቅት መግባት ነው፡፡

በታገቱት እህቶቻችን ላይ ከላይ የተገለጸው አንዱም አንዳይፈጸም ብመኝም፣ ይህ ኢ-ሰብዓዊ ጭካኔ እውን ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን ያለምንም መደባበቅ በግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው።ይህ አውነታ ታጋቾችን ነጻ የማውጣት ሃላፊነት አጥፍ ድርብ ያደርገዋል።

እገታ የረጅም ጊዜ የአእምሮ ቁስልና ያልተረጋጋ ኅብረተስብንም ይፈጥራል
እገታ በታጋቾች ላይ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ፣ ወዳጅና ዘመድ እንዲሁም ይህ ሁኔታ በሚካሆሄድብት አካባቢ ውስጥ በሚኖሩ ላይ ሁሉ የሚያደርሰው የአአምሮ ጤና መናጋትና በአርስ በርስ ግንኙነት ላይ የሚኖር አሉታዊ ተጽእኖ ወዘተ ከፍተኛ መሆኑን ብዙ ጥናት ያሳያል። ለምሳሌ ከፍተኛ መደበት፣ ከፍተኛ ጭንቀትና የምንፈስ አለመረጋጋትና፣ ከፍተኛ ድንጉጥነትን የመሳሰሉትን የአእምሮ ህመሞች አንደሚያስክትል፣ በቤተስብና በኅብረተስብ ደረጃ ደግሞ ከፍተኛ አለመተማመንንና ጭንቅን አንደሚያስፍን ብዙ ምርምሮች አረጋግጠዋል።

ከላይ የተጠቀስው ቀውስ የአንድ ሰሞንና በእገታው በቀጥታ የተጠቁ ሰዎች ችግር ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ረጅም ዋጋን የሚያስክፍል ሊሆንም ይችላል። ስለዚህ የታገቱት ወጣት ሴቶች ካሁን በኋላ ነፃ ቢሆኑ አንኳን ወዳጅና ዘመድ ትላንት የሚያውቃቸው ሰዎች አይሆኑም። በስቃዩ ምክንያት ህይወታቸው መሠረታዊ በሆነ መንገድ ተለውጧል።

ምን ይደረግ?1
አስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ እገታው በማን አንደተካሄደ፣ የአጋቾቹ ፍላጎትን የጠለፋው ዓላማ ምን አንደሆነ ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም። ይህ ሳይሆን ጊዜው እያለፈ በሄድ ቁጥርም የታጋቾቹ ደህንነት አጅግ አሳሳቢ፣ መኖራችውም አጠራጣሪ እየሆነ ይመጣል።
የተጠለፉትና የታገቱት ወጣት ሴቶች የሚገኙበት ሁኔታም ሆነ በትክክል በማን አንደታግቱ በመንግሥት በኩል አስካሁን የቀረበው መግለጫ አርስ በርስ የተምታታ ተጨባጨነትም ሆነ ግልጽነት የጎደለው ወይም ደግሞ በበቂ ደረጃ ያልተብራራ ነው።
ይህም በመሆኑ በአጋቾቹ ላይ ከሚታይው የቁጣ ሰሜት ያላነስ ወቀሳ በመንግሥት መሪዎች ላይ ተነጣጠሮ ይታያል። ብዙ ሰው መንግሥት ይህን ጉዳይ ለመፍታት ፍላጎትም ችሎታም አለው የሚለው አምነቱ በፍጥነት አየተቦረቦረ ነው።በጃንዋሪ 28,2020 በአማራ ክልል ብዙ ከተሞች የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የዚህ አንዱ መገለጫ ነው።
መንግሥት በዚህ ሁኔታ ላይ ወቅታዊ፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው መረጃ ባለመስጥቱም ህዝብ ለተለያዩ መላምቶችና ተባራሪ መረጃዎች ተጋልጧል።
ይህ ሁኔታ መፍትሄ ሳያገኝ እየተጓተተ በሄድ ቁጥር የኅበረተስቡም ቁጣ አጅግ እያደገና እየከረረ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ እጅግ በተካረረው የሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ግጭትና አለመርጋጋት የሚሄድበት ዕድል ሰፊ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ዜናው ዓለምአቀፍ ሽፋን አያገኘ በሄድ መጠን ቱሪዝምን ይገድላል፣ ኢንቪስትመንትን ያሸሻል፣ ዓለምአቀፍ ተጽእኖን ያጠናክራል፣ ኅብረተስብን ያልተረጋጋ ያደርጋል፣ መንግሥትን ክብር ያሳጣል፣ ህግ-አልባነትን ያበረታታል፤ ለጨለምተኞች ሁሉ ሰፊ በር ይከፍታል።
ከዚህ ለመውጣት ቢያንስ የሚከትሉት ተግባራት በአጣዳፊ ሊከናወኑ ይገባል፡
• መንግሥት ግልጽ ተዓማኒና ተጨባጭ ወቅታዊ መርጃ በተከታታይ ለህዝብ ማቅረብ ይኖርበታል
• መንግሥት በጠላፊዎቹ ላይ ስብአዊ መብትን የማይጥስ የማያዳግም ጠንካራ እርምጃ በመውስድ የታገቱትን ሁሉ ነፃ ማውጣትና ወደ ስላማዊ ኑሯቸው መመለስ ይኖርበታል፡
• ታጋቶች ነጻ ሲሆኑ ( ወዳጅ ዘምዶቻቸውን ጨምሮ ) የሚገጥማችው የስነ ልቦና የጤናና ሌሎችም ቀውሶች በመገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ዝግጅቱ ከአሁኑ መጀመር ይኖርበታል፡
• በአጋቾች ላይ የማያመነታ ስብአዊ መብትን የማይጥስ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ መንግሥት ለታጋቾችም ሆን ለሌላው ህዝብ ደህንነት ያለውን ሀላፊነት ለመውጣት ዝግጁ አንደሆነ፣ ለህግ የበላይነት አንደቆመና ለዚህ ዓይነት ወንጀል ምንም ትዕግሥት አንደሌለው ማሳየት ይኖርበታል
• ህግ የማስክብር ተግባር የገጠመው አደጋ አየስፋ ነው፣ መንግሥት ይህን ከቀን ወደ ቀን እየመነመነ የመጣውን በተቋማት ላይ እምነት ማጣትን በአስቸኳይ መልሶ መገንባት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ አደጋው ለራሱ ለመንግሥት ህልውና ብቻ ሳይሆን ለሀገር ተረጋግቶ መቀጠልም ጭምር ነው፡
• ከአማራ ክልል በመጡ ተማሪዎች ላይ የደረስው ጠለፋ ነገ በማንኛውም ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜጋ ላይ ሊደርስ አንደሚችል መጠራጠር የለብንም፡ የአሁኑ ጠለፋና እገታ የሚያስገኘው ጠቀሚታ (ሪዋርድ reward ) ከሚያስከትለው ኪሳራና ቅጣት (ፓኒሽምንት punishment) የሚበልጥ አስከሆን ድረስ ይህ ወንጀል ተጠናከሮ አንደሚቀጥል መገመት ይቻላል። ተግባሩን የፈጸሙት ብቻ ሳይሆኑ ይህን የሚመለከቱ ሊሎችም ተመሳሳይ ተግባር ውስጥ አንዲሰማሩ ሊያበረታታ ይችላል። ይህ ታላቅ ተግዳሮትን የሚፈጥር አደገኛ አዝማሚያ ነው፡፡ ለዚህም ሳይቃጠል በቅጠል አንደሚባለው ሁኔታው ይበልጥ ሳይሰፋፋ ከአሁኑ ከሥር መሠርቱ መፍታት የግድ ይላል።
• ይህን እያደገ የመጣ ታላቅ አደጋ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖትና ሌሎችም ተቋሞች፣ እንዲሁም መላው ህዝብ በጋራ ደግመው ደጋግመው ሊያወግዙት ይገባል።
• ሁኔታዎች ባስችኳይ ካልተቀየሩ የአካባቢው ፖለቲካዊ አለመርጋጋት አሁን ካስክተለው የባስ አደጋንም ሊደቅን ይችላል። ብዙ ጥፋትንም ይጋብዛል። ሰለዚህም ባካባቢው በመሳሪያ ሀይል ተደግፈው የሚንቅሳቅሱ ሀይሎችን ችግሮች በስላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረቱ ያለመታከት መቀጠል ይኖርበታል። ሀገራችን ከአመጽና ከመሳሪያ ፍልሚያ አዙሪት ልትውጣ በየትም ቦታ የሚገኝው ወገናችንም ስላማዊ አየር ለመተንፈስ እድል ሊያገኝ ይገባል።ይህ የስላም ፍለጋ ሂደት በአንድ አካባቢ ተወስኖ ሳይቀር ሁሉን አካታችና ሀገር አቀፍ ማድረግ ከዚህም በመነሳት ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ አሁንም ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው።
ማጠቃለያ
የተከስተው አሳዛኝ ሁኔታ ለመንግሥት አሁንም ሌላ የማንቂያ ደወል ሊሆነውና እስካሁን በተለያየ ምክንያት ያልወሰዳቸው ህጋዊ እርምጃዎች፤ ያላካሄዳችውን የአመለካከት ለውጦችን የፖሊሲ ውሳኔዎች…ወዘተ በስፊውና በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርግ ሌላ ማሳስቢያና ግፊት ሰጠቶታል። ይህን በማድረግም ህገርና ህዝብ ከቀን ወደ ቀን አየገቡበት ከሚገኘው አስክፊ ዝቅጠት ሊታደግ ይገባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe