ከ1300 በላይ ለሚሆኑት የቪኦኤ ጋዜጠኞች በተላከላቸው ኢሜይል የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ ተደረጉ

ጋዜጠኛ ሳሌም ሰለሞን በኤክስ ገጿ ላይ ‹‹እንደኤርትራዊ አሜሪካዊነቴ ያለ ነፃ ፕሬስ ህይወት ምን እንደሚመስል አብጠርጥሬ አውቀዋለሁ፡፡ በቪኦኤ ውስጥ እንደስራም ብቻ ሳይሆን ተልእኮ ጭምር እያገለገልኩ ያለሁትም ለዚህ ነው፡፡ በየቀኑ ታማኝ የሆኑ ዜናዎችን እያቀረብን ስንሰራ በመቆየታችንም ኩራት ይሰማኛል›› ብላለች፡፡
ይህች አንጋፋ ጋዜጠኛ ይህንን አስተያየት የፃፈችው የምትሰራበት ድርጅት የላከላትን ኢሜይል ካነበበች በኋላ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሰላም የምትሰራበት ድርጅት ቪኦኤ ይሁን እንጂ ዋናው ቀጣሪዋ የአሜሪካ ግሎባል ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩኤስ ኤጂኤም) ነው፡፡
ይህ ተቋም ቪኦኤን ጨምሮ፣ ሬዲዮ ፍሪ ኤስያን፣ ሬዲዩ ፍሪ ኢሮፕንና ሌሎችንም በአሜሪካ መንግስት በጀት የሚተዳደሩ ሚዲያዎችን የሚያስተዳደር ሲሆን ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ሰራተኞችን ያቀፈ ነው፡፡
ባለፈው አመት ብቻ 886 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ትልቅ ተቋምም ነው፡፡
ይሁንና ፕሬዝደንት ትራምፕ አርብ እለት ባወጡት ልዩ ትእዛዝ ይህንን ተቋም ‹‹አላስፈላጊ መንግስታዊ ቢሮክራሲ›› ብለው ከሰየሟቸው ውስጥ መድበውታል፡፡
ይህን ተከትሎ ለቪኦኤ ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ በላይ ለሚሆኑት ጋዜጠኞች በተላከላቸው ኢሜይል የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ ተነግሯቸዋል፡፡ በተጨማሪም በእጃቸው ላይ የሚገኘውን የፕሬስ መግቢያ ፈቃድና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲያስረክቡ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡
የቪኦኤ ዋና ዳይሬክተር ማይክል አብራሞዊትዝ ይህንን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ‹‹ከ83 አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የቪኦኤ ድምፅ እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡ እኛ የአሜሪካን ታሪክ በመናገር በመላው አለም ዲሞክራሲንና ነፃነትን ስናስተዋውቅ ቆይተናል፡፡ በተለይ በአምባገነን ስርአት ውስጥ ለሚገኙ ህዝቦች ተገቢና ሚዛናዊ መረጃዎችን ስናቀርብም ነበር›› ብለዋል፡፡
አንድ የድርጅቱ ጋዜጠኛ ስትናገር ‹‹ይህ እንደሚሆን እንገምት ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬ ይሆናል ብለን ግን አላሰብንም ነበር›› ያለች ሲሆን የተወሰደውን ይህንን እርምጃ መቀመጫውን በፈረንሳይ ያደረው ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ተቃውሞታል፡፡
ድርጅቱ በመግለጫው የአሜሪካ ኮንግረስ ይህንን ውሳኔ እንዲቀለብስም ጠይቋል፡፡ በፕሬዝደንቱ ውሳኔ መሰረት ቪኦኤ ለጊዜው እንዲቆም የተደረገ ቢሆንም በኮንግረስ ስብሰባ ላይ ይህ ውሳኔ ከፍተኛ ሙግት እንደሚገጥመው ይጠበቃል፡፡
ኋይት ሀውስ የፕሬዝደንት ትራምፕን ውሳኔ በማስመልከት ባቀረበው ፅሁፍ ላይ ግን በቪኦኤ ላይ በርካታ ክሶችን ዘርዝሯል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የቪኦኤ ማኔጅመንት ሀማስንና አባላቱን አሸባሪዎች ተብለው እንዳይጠሩ መወሰኑን ጠቅሷል፡፡#Zehabesha

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe