ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ሙስና የፈጽመ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊ ክስ ተመሰረተበት

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ከደንበኞች የማይንቀሳቀስ ሂሳብ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ስለመውሰዱ የሚያስረዳ ማስረጃ የተገኘበት ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንኪንግ ቢዝነስ መኮንን ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ሶስት የባንኩ ሰራተኞችም በዚሁ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
1ኛ ተከሳሽ አቶ እስጢፋኖስ ሙሉጌታ ገቢሳ (የባንኪንግ ቢዝነስ መኮንን) 2ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ አስኩዋል ወልደአብዝጊ ߹ 3ኛ በቀለ ሽፌ እና 4ኛ ተከሳሽ ይልቃል አዳነ ናቸው የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ሲል በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ክስ የመሰረተባቸው።
1ኛ ተከሳሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፒኮክ መናፈሻ ቅርንጫፍ ተቀዳሚ ባንኪንግ ቢዝነስ መኮንን የሥራ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ያልተገባ ጥቅም ለማስኘት በማሰብ በባንኩ ደንበኛ ከሆኑ ግለሰቦች ሳይንቀሳቀስ በመቆየታቸው ምክንያት የማይንቀሳቀሱ ሂሳብ (Inactive) የነበሩ የቁጠባ ሂሳቦችን ሃላፊነቱን በመጠቀም ወደ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ (Active) በመቀየር ደንበኞች ከሂሳባቸው ጋር ለሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ያስተሳሰሩትን የስልክ ቁጥር ሲስተም ላይ የተቀየረውን በማፅደቅ ከደንበኞች ሂሳብ ላይ በተለያዩ ጊዚያት በራሱ ሥም በተከፈቱ የሂሳብ ቁጥሮች በአጠቃላይ ብር 2,535,000 (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ አምስት ሺ) በሞባይል ባንኪንግ በማስተላለፍ የወሰደ በመሆኑ በፈፀመው ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል እና በወንጀል ድርጊት ያገኘውን ገንዘብ ህገ-ወጥ ምንጩን ለመደበቅና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ንብረቱን የለወጠ እና ለሌሎች ያስተላለፈ በመሆኑ በፈፀመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡
2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ ደንበኞች ባልቀረቡበት ፣ ማንነታቸው ባልተረጋገጠበት እና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት መጠየቂያ ቅፅ ባልሞሉበት ሁኔታ የደንበኛውን ሂሳብ የደንበኛው ባልሆነ ስልክ ቁጥር ለሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት በመመዝገባቸው በስራ ሃላፊነታቸው ሊጠብቁት እና ሊከላከሉት የሚገባውን የመንግስት ልማት ድርጅት ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በመፈፀማቸው የመንግስት የልማት ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች ዛሬ ግንቦት 11/2014 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት ቀርበው የክስ ቻርጁ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ክሱ በንባብ የተሰማ ሲሆን የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለግንቦት 24/2014 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል ።(ፍትህ ሚኒስቴር )

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe