በሀገራችን ባሉት ዝቅተኛ የሀይል ማመንጫ ግድቦች ምክንያት ከ64 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የመብራት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገልፀዋል።
ዶክተር አረጋዊ ይህንን ያሉት በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ በሚገኘው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ለህዳሴው ግድብ ያላቸው ተሳትፎ በሚለው ጉባኤ ላይ ነው።
የመብራት አገልግሎትን ከማጣት በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በጭስ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ተጋላጭ ሆነዋል ብለዋል።
ይህም ሆኖ በቂ የሆነ ለማገዶ ፍጆታ የሚሆኑ ነገሮችም ተሟልተው አያገኙም ነው ያሉት።
አሁን ከምንገኝበት ችግር ሊቀንስልን የሚችለውን የህዳሴው ግድብን በሀገራዊ ስሜት እየገነባን የምንገኘውም ለዚሁ ነው ብለዋል።
ስለሆነም ምሁራን በአባይ ወንዝ መነሻ ተፋሰስና ጣና አካባቢ የተፋሰሱን ጉልበት ሊጨምሩ የሚችሉ ጥናቶችንና ምርምሮችን ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ጥናቶቹም የብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ ብሎም የህዳሴው ግድባችን በደለል እንዳይሞላም የሚያስችሉ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አሳስብዋል።