‹ክስ የማቋረጥ ጣጣዎች›

‹ክስ የማቋረጥ ጣጣዎች›
መነሻ
ባሳለፍነው ሳምንት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሀገራዊ አንድነት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል የ63 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን ለሚድያ አካላት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ መግለጫውን የሰጡት በተቋሙ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ እንደሚሉት በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ለሀገራዊ አንድነት እና ለለዉጡ የሚኖረውን ፋይዳ ከግምት ዉስጥ በማስገባት እንዲሁም ለህዝብና ለመንግስት ጥቅም ሲባል በወንጀሎች ዉስጥ እንዳሉ የተረጋገጠ ቢሆንም ያስከተሉት ጉዳት እምብዛም መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረውና ምርመራ ተጣርቶባቸው፣ ማስረጃ የተሰበሰበባቸው እና ክስ ተመስርቶባቸው በሙስና ወንጀል ከሜቴክ ጋር በተያያዘ፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተጠረጠሩ ነገር ግን የመሪነት ሚና የሌላቸው፣ ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር ተጠርጥረው ጉዳያቸው እየታየ ያሉ፣ ከሲዳማ፣ ቤንሻንጉል እና የሶማሌ ክልል ግጭቶች ጋር በተያያዘም የተጠረጠሩም ጭምር ክከሳቸው ከተቋረጠው መካከል እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ተከሳሾቹ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረገው ተፈጽሟል በተባለው የወንጀል ድርጊት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ክሱ እንዲቋረጥ ከተደረገላቸው መካከል ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውለው የተከሰሱ ግለሰቦች፣ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ነገር ግን የአመራርነት ሚና ያልነበራቸው ግለሰቦች ናቸው ተብሏል፡፡
በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተፈጸመው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ ተከሰው ከታሰሩ 13 ተከሳሾች ውስጥ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የማዕከላዊ ምክር ቤት አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ (በአዲሱ የድርጅቱ ምርጫ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆኖ ተመርጧል)፣ እንዲሁም አቶ በለጠ ካሳና ሌሎችም የፓርቲው አባላት ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ከእስር ተፈተዋል፡፡
ከኤምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የአክሰስ ሪል ስቴትና የዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር መሥራች የነበሩት፣ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋም ክስ ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል፡፡
በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የሚታወቁት የዓለም ገነት ቆርቆሮ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም፣ ሪቬራ ሆቴልን ለሜቴክ ከመሸጣቸው ጋር በተያያዘ የተከሰሱበት ክስ ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል፡፡
ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ተከሳሾች መካከል የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደም ይገኙበታል፡፡
ኮሎኔሉ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል በመከላከያነት ከቆጠሯቸው መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አንዱ ሲሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራ ብዛት ምክንያት ሳይቀርቡ በመቅረታቸው የክስ መዝገባቸው በተደጋጋሚ ሲቀጠር የነበረ ቢሆንም፣ አሁነ መንግሥት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ክሳቸው ተቋርጦ ሊፈቱ ችለዋል፡፡
በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በጅግጅጋና ሌሎች የክልሉ ከተሞች በተፈጸመ ዘርን መሠረት ያደረገ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማፈናቀል፣ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠልና ንብረት ዘረፋ ጋር በተያያዘ በቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) የክስ መዝገብ የተካተቱት የክልሉ ሕፃናትና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ራህማ መሐመድ፣ እንዲሁም ወ/ሮ ዘምዘም ሐሰንና የሌሎች ክስ ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል፡፡
ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሽን (ሜቴክ) ተከሳሾችም፣ ኮሎኔል ዙፋን በርሄ፣ ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔና ሌሎችም ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ ከደቡብ ክልልም ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የኤጄቶ አባላት የነበሩት አቶ አማኑኤል በላይነህ፣ ተሰማ ኤልያስ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ አቶ አዲሱ ቀሚሶና ሌሎችም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ የተደረገ ሲሆን፣ ሌሎችም በአጠቃላይ 63 ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡
የክስ ማቋረጥ ሒደቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመሩት የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃላፊዎች በተገኙበት፣ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሉባቸውን ውስንነቶች መናገራቸውን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ ገልጸዋል፡፡ ወንጀል በብዙ መንገድ ሊፈጸም እንደሚችል ጠቁመው፣ የመጀመርያው የመንግሥት አካል የተጣለበትን ኃላፊነት አለመወጣት መሆኑን አክለዋል፡፡
ሌላው ደግሞ ወንጀል ፈጻሚ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ተጠያቂ እንደሚሆን ጠቁመው፣ ሕግ የማስከበር ሥራ መጀመርያ መፈጸም ያለበት በመንግሥት መሆኑ በተደረገ ውይይት መተማመን ላይ በመደረሱ፣ ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ወደ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱ፣ ዕቅድ በማውጣት መሥራት መጀመሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ እነ ማን ወንጀል እንደሠሩ፣ እነ ማን እንደተያዙና እነ ማን እንዳልተያዙ፣ ላለመያዛቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግምገማ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ክልል ተወያይቶና በተለይም ወንጀል ሠርተው ስላልተያዙ ተጠርጣሪዎች ላለመያዛቸው መንስዔ የሆነው ማን እንደሆነ ማለትም የፖለቲካ አመራሩ፣ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይስ ሌላ የሚለውን እየመረመሩ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በተቀመጠው አቅጣጫም መሠረት ዕርምጃ ለመውሰድ መርሐ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሥራውን መሥራት ያልቻለ አመራር ያልቻበት ምክንያት ተገምግሞ አሳማኝ ካልሆነ በራሱ ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድበትም ጠቁመዋል፡፡
ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የሚጠቅም ከሆነ ክስ እንደሚነሳለት በተደጋጋሚ ጊዜ የተገለጸ በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በአደባባይ በተናገሩትና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943 አንቀጽ 6(3) ድንጋጌ በተሰጠው ክስ የማቋረጥ ሥልጣን መሠረት፣ የ63 ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በወንጀል ድርጊቱ ተጠቃሚ የሆኑ ተከሳሾች ግን የዕድሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መደረጉንም አክለዋል፡፡
ትኩረት የተሰጠባቸው ወንጀሎች አራት መሆናቸውን የጠቆሙ አቶ ፈቃዱ ግድያ፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ዘረፋዎች፣ አስገድዶ መድፈርና የማነሳሳት ወንጀሎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸም የወንጀሉ ውጤት ተጠቃሚ የሆኑ ዕድሉን እንዳላገኙም አስታውቀዋል፡፡ ክስ ማቋረጥ ማለት ግን የመጨረሻ ውሳኔ አለመሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ክስ የተቋረጠላቸው ተከሳሾ ተመልሰው ወደ ለመዱት ድርጊት የሚገቡ ከሆነ ግን ዓቃቤ ሕግ ያቋረጠውን ክስ ማንቀሳቀስ የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተከሳሾች አንዳንዶች የጤንነት ችግር ያለባቸው፣ ከሕፃናት ጋር ታስረው የሚገኙ፣ የወንጀል ተሳትፏቸው አነስ ያሉ ተከሳሾች መሆናቸውንም አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡
ክስ የተቋረጠላቸው ግለሰቦች
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ከመጡ ወዲህ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የነበሩና በእስር ላይ ኾነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 63 ግለሰቦች ናቸው ክሳቸው የተቋረጠላቸው፡፡ በአቃቢ ህግ መረጃ መሰረት የጤንነት ችግር ያለባቸው፣ የወንጀል ተሳታፊነታቸው አነስተኛ የኾኑ፣ ከልጆቻቸው ጋር የታሰሩና በመሳሰሉ ምክንያቶች ክሳቸው የተቋረጠም አለ። በዋናነት ግን አገርን የሚጠቅም ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የተወሰነ መኾኑ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተገልጿል። ለአገራዊ አንድነትና ለለውጡ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባ፤ እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እርምጃው መወሰዱ ተገልጿል።
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የተቋረጠው የክስ መዝገባቸው እንደሚያመለክተው፤ የኢምፔሪያል ሆቴልን ከሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሆቴሉ ሊያወጣ በማይችል ዋጋ እንዲገዛ አድርገዋል በሚል ነው ወደማረሚያ ቤት የወረዱት። ሕንጻውን ሜቴክ ለእንግዳ ማረፊያነትና ለቢሮነት ሲጠቀምበት የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለቢሮነት እየተገለገለበት እንደሚገኝ ይነገራል።
ክሱ ባለፈው ዓመት ጥር 2011 ዓ.ም ሲመሠረት፤ ከ41 እስከ 51 ሚሊዮን ብር የሚገመተውን የኢምፔሪያል ሆቴል አቶ ኤርሚያስ በ72 ሚሊዮን ብር በመሸጥ 21 ሚሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል እንደነበር ይታወሳል። ሽያጩ የተካሔደው በ2003 ዓ.ም ነበር። በአሁኑ ወቅት ይህ የቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል ስሙ ተቀይሮ “አሞራው ሕንጻ” የሚባል ሲሆን፤ ሕንጻው በገቢዎች ሚኒስቴር ተይዞ ይገኛል። በቅርቡም ገቢዎች ሚኒስቴር ሕንጻውን ከሜቴክ ጠቅልሎ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።
ሌ/ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ
ሌ/ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ተጠርጥረው በነበረው ወንጀል ሲከሰሱ የክሱ ጭብጥ የተለየ ቢኾንም፤ ከዚህ ውስጥ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ የሥልጠና ግዥ ፈጽመዋል የሚል ይገኝበታል።
ሌ/ኮ ቢኒያም ከነባለቤታቸው ምንጩ ያልታወቅ ሀብት አካብተዋል፣ በሙስና የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ በሙስና ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል።
አቶ ክርስቲያን ታደለ
በዛሬው ዕለት ክሳቸው የተቋረጠላቸው ሌላኛው ተጠርጣሪ የነበሩት የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ናቸው። አቶ ክርስቲያን ታደለ ተጠርጥረው የታሰሩበት ምክንያት ወጣቶችን መሣሪያ በማስታጠቅና በማደራጀት ከሚል ድርጊት ጋር በተያያዘ ነበር። አቶ ክርስቲያን በታሰሩበት ወቅት የአብን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፤ በእስር እያሉ ፓርቲያቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አድርጎ በሥራ አስፈፃሚነት እንደመረጣቸው አይዘነጋም።
ከአቶ ክርስቲያን ሌላ ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉት ውስጥ፤ አቶ በለጠ ካሳ የአብን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ፣ አቶ አማረ ካሳ የአብን የአዲስ አበባ የሕዝብ ግንኙነት አባል የነበሩ ናቸው።
ከዚህም ቀደም…
መንግሥት የአገር አንድነትን ለማጠናከር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማስፋት ሲባል ባለፉት ወራት ፣ በተለይ ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሰየሙ ጀምሮ በወሰደው ርምጃ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኖች እና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ለቋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በ2010 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ መለቃቀቸው አይዘነጋም፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል 137ቱ በሽብርተኝነት፣ 31ዱ ደግሞ በሙስና ክስ የታሰሩ ነበሩ።
የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ክሳቸው ከተቋረጠ መካከል የቀድሞዉ የግንቦት 7 የፍትሕ፤የነፃነት እና የዴሞክራሲ ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ የቀድሞዉ የአንድነት ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የልብ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እንዲሁም የግንቦት 7 የፍትሕ፤ የነፃነት እና የዴሞክራሲ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በምህፃሩ ኦ ኤም ኤን ዋና ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ፣ እንዲሁም፣ ኢሳት እና ኦ ኤም ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋሕድ ገብረሥላሴ፣ አቶ ዓለማየሁ ጉጆና ሌሎች ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ይገኙባቸዋል።
ክስ ማቋረጥ እንዴትና ለምን?
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ እንዳይጀመር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሊያዝ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6(3)(ሀ) ላይ ስለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሥልጣንና ተግባር ሲገልጽ ‹‹በሕዝብ ጥቅም መነሻ… የወንጀል ምርመራ እንዲቋረጥ ወይም የተቋረጠው የወንጀል ምርመራ እንዲቀጥል ያደርጋል፤›› ይላል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 42(1) (መ) ላይም ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲል ክስ የመመሥረት ሒደቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ይህ የሚሆነው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ ሪፖርቱንም ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፎ ነገር ግን ክስ ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ ክስ ተመሥርቶ ከሆነ ግን በዚሁ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 122 አማካይነት የክስ ሒደቱን ማቋረጥ ወይም ማንሳት ይቻላል፡፡ የክሱ ሒደት እየተከናወነ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ክሱን ሊያነሳ ይችላል፡፡ ክሱ የሚነሳው በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያነሳ ፍርድ ቤቱ ከመፍቀዱ በፊት ማረጋገጥ ያለበት ነገር ቢኖር ክሱ ላይ የተገለጸው የወንጀል ድርጊት በዓቃቤ ሕግ ክሱ የማይነሳ አለመሆኑን፣ እንዲሁም ዓቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲያነሳ ከመንግሥት የታዘዘ መሆኑን ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው በከባድ የግፍ አገዳደልና በከባድ የወንበዴነት ተግባር የተከሰሱ ሰዎችን ክስ ማቋረጥ ወይም ማንሳት አይቻልም፡፡ ተራ የሰው ግድያ ወይም በቸልተኝነት ሰው የመግደል ወንጀሎችን በሚመለከት ግን ክስ ማንሳት ይቻላል፡፡
ሌላው መንግሥት ክሱ እንዲቋረጥ የወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ የመኖር አስፈላጊነት ነው፡፡ የክሱን መነሳት ሲፈቅድም ወይም ሲከለክል ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው ምክንያት የሆኑትን ነጥቦች መግለጽና መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት መንግሥት ክስ የሚያነሳበትን ምክንያት የመመርመር ሥልጣን ፍርድ ቤት የለውም፡፡ መንግሥትም በምን በምን ምክንያት ክስ ማቋረጥ እንደሚችል አልተገለጸም፡፡ በዚህ ሁኔታ የተቋረጠ ክስ አንድም በሌላ አንቀጽ መልሶና ወዲያውኑ ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የተነሳውን ክስ መልሶ በሌላ ጊዜ በዚያው ክሱ ተመሥርቶበት በነበረው አንቀጽ ክሱን መቀጠል ይቻላል፡፡ በሌላ ጊዜ የክስ ሒደቱን ማንቀሳቀስን አይከለክልም፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ከሆነ መንግሥት ክሳቸውን በቅርቡ ያቋረጠላቸውን ሰዎችና ወደፊትም የሚያቋረጥላቸውን የዚህ ዓይነት ዕጣ ፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ክስ አለመመሥረትም ማንሳትም ቢሆን ከዚህ ሥጋት ውጭ አይደሉም፡፡
‹‹ለህዝብ ጥቅም››
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)(ሠ) ላይ ‹‹የፌዴራል መንግሥትን በመወከል… ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፤ የተነሳውን ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ አገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመርያ ያወጣል፡፡›› ይላል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ክስን የሚያነሳው መንግሥት ነው ቢልም በሕግ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ውክልና መሰጠቱን ነው፡፡
ይሁን እንጂ ሁኔታው አገራዊ ይዘት ካለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመመካከር እንጂ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ብቻ ማንሳት አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ ሁለት አይቀሬ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንዱ ‘ለሕዝብ ጥቅም’ ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ‘አገራዊ ይዘት ያለው የሕዝብ ጥቅም’ ምን ማለት ነው የሚለው ነው፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ክስ ላለመመሥረት ‘ለሕዝብ ጥቅም’ የሚል ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጥ ክስ ለማንሳት ግን ምንም የተገለጸ ቅድመ ሁኔታ የለም፡፡ በአዋጁ ላይ ግን ክስ ማንሳት ወይም ማቋረጥ የሚቻለው ‘ለሕዝብ ጥቅም’ ሲባል እንደሆነ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁም ቢሆን የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን እንደሆነ ትርጓሜም ይሁን ማሳያዎችን አልያዘም፡፡ ስለሆነም ክሱ ላለመመሥረትም ይሁን ለማንሳት ምክንያት የሆነው ጉዳይ የሕዝብ ጥቅም ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ነው፡፡ ክስ በሚነሳበት ወቅት ፍርድ ቤቶች የሕዝብ ጥቅም አለ ወይስ የለም የሚለውን የማጣራት ሥልጣን አልተሰጣቸውምና፡፡
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ምርመራን ለማቋረጥ በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶች የሉም፡፡ ክስን ለማንሳትም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን በርካታ ተከሳሾች ክሳቸው የተቋረጠ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በተመሳሳይ ወንጀል እንደውም በአንድ ክስ ከተከሰሱ ሰዎች ውስጥ የተወሰኑት ክሳቸው ተነስቶ የሌሎቹ ደግሞ ያልተነሳም አለ፡፡
ረቂቅ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ይኼንን ክፍተት በመረዳት ይመስላል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸውን ሁኔታዎች ዘርዝሯል፡፡ ክስ ማንሳትን በተመለከተ ግን በምን በምን ምክንያቶች ዓቃቤ ሕግ ክስ ሊያነሳ እንደሚችል ረቂቅ ሕጉም ላይ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ በረቂቅ ሕጉም ላይ ቢሆን ለአገራዊ መግባባት ወይም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚሉት ወይም እነዚህን የሚመስሉ አገላለጾች በሕዝብ ጥቅም ሥር አልተካተቱም፡፡
ክስ ማቋረጥና ጣጣዎች
የሕዝብ ጥቅምን መሰረት በማድረግና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል የሚደረጉ የክስ ማቋረጦች የሚያመጡት ጣጣም እንዳለ መታሰብ አለበት፡፡ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ አለመመሥረትን እንዲሁም ክስ ማቋረጥን ያለምንም መመርያ (ሕግ) ክፍት አድርጎ መተው ይህንን ሥልጣን አላግባብ ለመጠቀም መንገድ ከፋች እንደሆነ የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
የዓቃቤ ሕግ አሠራር በማናቸውም መልኩ ሥርዓት ያለው፣ አርዓያ የሚሆን ደንቦችን ያሰፈነ፣ ውስጣዊ አሠራሩም ቢሆን ለሕዝብ ተጠያቂነትን ያመቻቸ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በአገሪቱ ያለውን ሕጋዊ አሠራር እንዳይጣስ የኖላዌነት ወይም እረኝነት ኃላፊነት የተጣለበት መሥሪያ ቤት ራሱ የሚሠራቸው ተግባራት ሲበዛ ግልጽ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምን ሕግ፣ በምን ሥርዓት እንደሚሠራ ማሳወቅ የባሕርይው መሆን አለበት፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተቋቋመበት አዋጅ በመግቢያው ላይ ካስቀመጣቸው ግቦች ውስጥ ወጥነት ያለው አገልግሎት መስጠት፣ የሕዝብ ተዓማኒነት ያለው ለሕዝባዊ ተጠያቂነት የሚገዛ እንዲሁም በግልጽነት የሚሠራ የዓቃቤ ሕግ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ የመሆኑ ጉዳይ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በአዋጁ መሠረት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ሲቋቋም ማሳካት ካለበት ግቦች መካከል ጥቂቶቹ ከላይ የተገለጹት ናቸው፡፡
ወጥነት ያለው አገልገሎት መስጠት ከተጓደለ ሕዝብ በተቋሙ ላይ የሚኖረው አመኔታ መቀነሱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ተቋሙ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ሕዝቡ ይህ ተቋም በምን መልኩ እንደወሰናቸው የሚያውቅበት ሥርዓት ከሌለ ግልጽነት የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ አዋጁ ሲወጣ በግብነት ያስቀመጣቸው የሚፃረሩ ይሆናሉ፡፡
በዚሁ በአዋጅ አንቀጽ 11(3)(ሀ) ላይም ይህንኑ ሁኔታ አስፍሮት እናገኛለን፡፡ ዓቃቤ ሕጋዊ አሠራር ለሕዝብ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ መደራጀት፣ የሥራ አመዳደብ፣ የሥራ ዓይነቶቹ፣ ሥራዎቹ የሚመሩባቸው ሥርዓት ሁሉ ለሕዝብ ተጠያቂ መሆንን በሚያሰፍን መንገድ መሆን እንደሚጠበቅበት ተደንግጓል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በማይኖሩበት ወይም በሚድበሰበሱብት ወቅት ለሕዝብ ተጠያቂ አለመሆንን ያስከትላል፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በሚመለከትም ሥርዓት የለሽነትም ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው፡፡
የፍቃድ ሥልጣን አጠቃቀም በሕዝብ ዘንድ የማይገመት ሲሆን፣ ሕዝባዊ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር እየመነመነ ሲሔድ ሕዝብ በተቋሙ ላይ የሚኖረው አመኔታ እየቀነሰ መሔዱ አይቀሬ ነው፡፡
በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተከሰው የተወሰኑት ክሳቸው ተነስቶ የሌሎች አለመነሳቱ በራሱ የእኩልነት መብት ስለሚጋፋ አድሏዊ ይሆናል፡፡ ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ግለሰቦች ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ሆነው ክሳቸው ያልተነሳና በይቅርታ ያልተለቀቁ ሰዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠረር አድሏዊነትን የሚያስከትል መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 42(1)(መ) ላይ ተመርኩዞ ክስ እንዳይመሠረት የማድረጉ ሒደት እንዲሁም በአንቀጽ 122 መሠረት ደግሞ ክስን የማንሳቱ ሥራ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩን፣ የተከሰሱን በአንድነት ሳይለያይ፣ ሳይነጣጥል እየተተገበረ ነው ማለት አይቻልም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe