ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እስከ 9 ሚሊዮን የኮሮና ክትባት እንደምታስገባ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ እስከ 9 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት ለማስገባት እየሰራች መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ይህንን ያሉት ዛሬ፣ ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ለክትባቱ በዋናነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜጎች ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው ብለዋል።

በዚህ መሰረት የጤና ባለሙያዎች፣ የማህበራዊ ጤና ሰራተኞች፣ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ያሉ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ሀይልም የተሳለጠ የክትባት አሰጣጥና ቁጥጥር እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል ዶ/ር ሊያ።

ሚኒስትሯ አክለውም ኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ከኮቫክስ የክትባት ትብብር ተቋም ጋር በመሆን እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝባቸውን ለመከተብ እየሰሩ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ክትባቱን ወደ ሃገር ውስጥ የምታስገባው ‹‹ኮቫክስ›› በተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ሸማች ማህበር በኩል ነው።

ኮቫክስ (COVAX) ምጣኔ ኀብታቸው ደካማና መካከለኛ ለሆኑ አገራት ክትባቱን ለማቅረብ ያለመ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የተመሰረተ ኢኒሼቲቭ ነው።

ሁሉም የአፍሪካ አገራት ይህንን ኢኒሼቲቭ ተቀብለውታል።

ይህም ማለት አፍሪካ በዚህ ኢኒሼቲቭ በኩል ክትባቱ ፍቃድ ካገኘና ከፀደቀ በኋላ፣ 220 ሚሊዮን ክትባቶችን ታገኛለች።

እኤአ በ2021 መጨረሻ ላይ ኮቫክስ 2 ቢሊዮን የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመግዛት እቅድ ይዟል። አፍሪካ ለአህጉሩ የሚሰራጭ ለጊዜው 270 ሚሊዮን ‘ዶዝ’ (መጠን) የኮቪድ-19 ክትባት በአፍሪካ ሕብረት በኩል ማግኘቷ ተገልጿል።

አጠቃላይ የተገኘው ክትባት በዚህ ዓመት ጥቅም ላይ እንደሚውል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ቃል ገብተው ነበር።

ይህ ክትባት ከዚህ ቀደም ቃል ከተገባው 600 ሚሊየን ‘ዶዝ ‘ተጨማሪ ቢሆንም አሁንም ግን ሙሉ አህጉሩን ለመከተብ በቂ አይደለም።

በዚህም የዓለማችን ድሃ አገራት ከሃብታም አገራት ይልቅ ክትባቱን ለመከተብ ረዥም ጊዜ ሊጠብቁ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

ምንም እንኳን በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ዝቅተኛ ቢሆንም በአንዳንድ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በድጋሜ እየጨመረ ነው።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe