ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሴቶች እንዳይወልዱ ያደርጋል በሚል የሚሰራጨው አሉባልታ መሠረተ ቢስ እንደሆነ ባለሙያዎች ገለጹ።
የፋይዘር ክትባት የሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ቀውስ ያስከትላል መባሉ “ምክንያታዊ አይደለም” ሲሉ በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የሚሠሩት ፕ/ር ሉሲ ቻፔል ተናግረዋል።
ክትባቱ ሰውነት በሽታውን የመከላከል አቅም እንዲያዳብር የሚረዳ ነው። ሰዎች በቫይረሱ እንዲያዙ ወይም ዘረ መላቸው እንዲለወጥ አያደርግም።
ፕ/ር ኒኮላ ስቶንሀውስ የተባሉ የቫይረስ ተመራማሪ፤ ክትባቱ የተሠራበት መዋቅር የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት መንገድ የለም ይላሉ።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ ያለው አሉባልታ የሚያጣቅሰው ከዚህ ቀደም በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የወጣ መግለጫን ነው።
መግለጫው እንደሚለው፤ የፋይዘር ክትባትና የመውለድ አቅም ስላላቸው ትስስር መረጃ የለም። ሆኖም ግን ይህ መግለጫ ማሻሻያ ተደርጎበት ክትባቱ የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ጉዳት እንደማያደርስ የሚገልጽ ጽሑፍ ወጥቷል።
ሳይንቲስቶች ስለ አንድ ነገር ሲገልጹ “መረጃ የለም” ካሉ፤ ይህ የሚጠቁመው በጉዳዩ ላይ ገና ጥናት አልተሠራም እንጂ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል ማለት አይደለም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨው አሉባልታ የኮሮናቫይረስ ክትባት የእንግዴ (ፕላሴንታ) ፕሮቲን አለው ይላል። ይህም ፕላሴንታ ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ወሬ ነው የተናፈሰው።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ይህ ወሬ ሐሰት ነው። ክትባቱ ከፕላሴንታ ጋር የሚመሳለል ፕሮቲን ቢጠቀምም ይህ ሰውነትን ግራ የሚያጋባ አይደለም።
ክትባት የሚሠራው ቫይረስን ለይቶ ለማጥቃት ነው።
በነፍሰ ጡር ሴቶች ሕክምና ላይ የሚያተኩሩት ፕሮፌሰሯ እንዳሉት፤ የኮሮናቫይረስ ክትባት በሴቶች ሥነ ተዋልዶ ላይ ጉዳት አያስከትልም።
በእንግሊዝ የሕክምና ባለሙያው ጆናታን ቫንቲም “ሴቶች እንዳይወልዱ ስለሚያደርግ ክትባት ሰምቼ አላውቅም። የተሳሳተ ወሬ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ነፍሰ ጡር ሴቶች በክትባት ሙከራው ወቅት አልተካተቱም። ባለሙያዎች በክትባቱና በነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል ስላለው ትስስር ግልጽ መረጃ ባይሰጡም፤ በከፍተኛ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች ብቻ ክትባቱን እንዲወስዱ ይመክራሉ።