ዓሊ ቢራ – “ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው”

ከ50 ዓመታት በላይ በሙዚቃ ላይ የነገሰው አርቲስት ዓሊ ቢራ ሰሞኑን ታሞ ሆስፒታል መግባቱን ተከትሎ ዘመን አመጣሹ ማህበራዊ ሚዲያ የ‹ሟርት ዜናዎችን› ይዘው መውጣት ጀምረው ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዋቂ ሰዎች መለስተኛ የጤና እክል እንደገጠማቸው በተሰማ ማግስት የሟርት ዜናዎች መነገራቸው እየተለመደ መጥቷል፤ ይህንኑ ልምምድ አንዳንድ ሰዎች ከማጣራና እውነትን ፍለጋ ግራና ቀኝ ከማየት ይልቅ መረጃውን ለሌሎች በማጋራት በወዳጅ፤ በዘመድና በአድናቂዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤና የስነ ልቦና ቀውስ ሲፈጥሩ ይስተዋላል፤

ዓሊ ቢራም አንዴ ያዝ ሌላ ጊዜ ለቀቅ እያደረገ አልጋ በሚያሲይዘው ህመም ሳቢያ ሰሞኑን ወደ ሆስፒታል ማምራቱ እውነት ነው፤ ሆኖም በማህበራዊ ሚዲያው እንደተባለው ሳይሆን በህክምና ባለሙያዎች ክትትል እያገገመ ስለመሆኑ ተነግሯል፤በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑ ባለሙያዎች መሀከል አንዱ የሆነው አንጋፋው ከያኒ ዓሊ ቢራ ማነው?

ስለ አስተዳደጉ፤የሙዚቃ ስራዎቹ፤የፖለቲካ ተሳትፎውና የበጎ አድራጎት ተግባራቱን ከቀደምት ቃለ ምልልሱ ጋር በማጣመር የቁም ነገር መፅሔት ባልደረቦች ስራዎቹን መርምረዋል፤

በበርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጭምር በተጫወታቸው ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው አርቲስት ዓሊ ቢራ በተለይ በአፋን ኦሮሞ በተጫወታቸው በርካታ ሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን በመቻሉ የቋንቋው ምልክት እስከመሆን ደርሷል ይሉታል በርካቶች።

በግንቦት 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ የተወለደው አርቲስት ዓሊ ቢራ ፣በህጻንነቱ የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን እያደመጠ ማደጉን እና ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ እና ለቤተሰቦቹ በማንጎራጎር  ነው የሙዚቃ ህይወቱን የጀመረው።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካ ሀገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርቱን መማሩን ይናገራል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የኦሮሚኛ ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የባህላዊ ሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው። በቡድኑ ውስጥ ሌላ ዓሊ የተባለ ልጅ በመኖሩ ሁለቱን ለመለየት መጀመሪያ ከሚያዜመው “ቢራ ዳ ባሬ” ዘፈን ተወስዶ “ዓሊ ቢራ” የሚለው ሰም ተሰጠው። ዓሊ ስለ አፍረንቀሎ የሙዚቃ ባንድ ሲጠየቅ  ከመስራቾቹ አንዱ መሆኑን  እንጂብቸኛ  መስራች ተብሎ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚጠቀሰውን ያርማል።

አፍረንቀሎን ከመሰረቱት ውስጥ ዓሊ ሸቦ የሚባል እሱም ከሃረማያ ዩኒቨርሰቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል። እኔ ከነሱ ጋር ተቀላቅዬ አፍረንቀሎን መሰረትኩ” ብሏል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት ሰርቷል፤ እንዲሁም ‘አይቤክስ’ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ስራዎቹን በዲ አፍሪካ ሲያቀርብ ቆይቷል። ስለ ፍቅር፣ አካባቢ እና ፖለቲካ በጥቅሉ ከ267 በላይ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል። ዓሊ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኡድ እና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወታል። ከአርባ በላይ ሀገራት (በሁሉም አህጉራት) እጅግ በርካታ በሆኑ መድረኮች የሙዚቃ ስራዎችን ተጫውቷል።

ዓሊ ቢራ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁመው ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

አርቲስት ዓሊ ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ፡ በሐረሪ፣ በአማርኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።አንድ ሰሞን ስለ ራሱ የተናገረው አርቲስት ዓሊ ቢራ “ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው” ብሏል።

የ75 ዓመቱ አርቲስት ዓሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።የተለያዩ ፈተናዎችን ተሻግሮ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት ያደርገዋል።

አርቲስቱ በተስረቅራቂ ድምፁ ዘመን ተሸጋሪ ጥዑም ሙዚቃን ከመጫወት በተጨማሪ የግጥምና ዜማ ደራሲም ነው። አርቲስት ዓሊ ቢራ ባለፉት 50 ዓመታት በኦሮሚኛ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ አንፀባራቂ  ሆኖ ቆይቷል።

ለቋንቋው የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በኪነጥበቡ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ የክብር ዶክተሬት ማዕረግ የተሰጠው አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችን አግኝቷል።

Ø በአጠቃላይ ከሃምሳ በላይ ታላላቅ ሽልማቶች ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋማት ወስዷል።

Ø ከድሬዳዋ እና ከጅማ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል።

Ø በድሬደዋ ከተማ ፓርክ እንዲሁም በአዳማ መንገድ በስሙ ተስይሟል።

Ø የኦሮሚያ ክልል በሙዚቃው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ልዩ የኒሻን ሽልማት አበርክቶለታል።

Ø የመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ተሸላሚም ነው።

Ø የመጀመሪያው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የኪነጥበብ ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚም ሆኗል።

Ø የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከፍተኛ ሽልማት

Ø በካናዳ ቶሮንቶ የአፍሪካን የምንግዜም አንጋፋ ሙዚቀኛ ሽልማት እና

Ø የኦዳ አዋርድ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ነው።

ዓሊ በደርግ ዘመን ከኢትዮጵያ በስደት ከወጣ በኋላ የተለያዩ የኦሮሞ ትግልን የሚደግፉ የትግል ዘፈኖችን ተጫውቷል፤ በምረርጫ 97 ማግስት  ወደ ሀገር ቤት የገባው ዓሊ ከቁም ነገር መፅሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ‹በትግል ወቅት በዘፈንኳቸው ዘፈኖች አልፀፀትም› ማለቱ ይታወሳል፤ ይህም በወቅቱ ከነበረው የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቁጣን ቀስቅሶበት እንደነበርና በአንዳንድ መድረኮች ላይ እንዳይጋበዝ ጭምር ተጽእኖ ተደርጎበት ነበር፤

ዓሊ ከ2010ሩ ለውጥ በኋላ በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተገኘ በሚሰጠው ቃለ ምልልስ የተቃውሞ ድምፆችን ሲያስተናግድ የቆየ ሲሆን በተለይም በ2012 ታዋቂው የኦሮሚኛ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ማግስት በርካታ ንፅሃን በየአካባቢው መገደላቸውን ምክንያት በማድረግ ከኤል ቲቪ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረግው ዓሊ በሰነዘረው አስተያየት ሰፊ ወቀሳ ደርሶበታል፤ ዓሊ በወቅቱ ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነው የሀጫሉ ግድያን በተመለከተ ‹ የተቆጣ ህዝብ ብዙ ነገር ያደርጋል፤ ይህንን ባያደርግ ነበር የሚገርመኝ› ማለቱ ብዙዎቹን አስቆጥቷል፡፡

ዓሊ ላለፉት 15 ዓመታት ከሙዚቃ ስራዎቹ ጎን ለጎን ወደ በጎ አድራጎት ስራ ገብቶ ለብዙዎች ተስፋ የሆነ የትምህርት ቤት ግንባታ ውስጥ ገብቶ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በትውልድ ፊሊፒንሳዊት በዜግነት ካናዳዊ ከሆነችው ከመምህርት ባለቤቱ ሊሊ ማርቆስ ጋር በመሆን በትውልድ ሀገሩ ድሬዳዋና በሮቤ የትምሀርት ቤት ግንባታዎችን እያከናወኑ ነው፡፡ በ1998 ዓም ዓሊ ወደ ባሌ ሮቤ የሙዚቃ ስራዎቹን ሊያቀርብ ባመራበት ወቅትም የዞኑ አስተዳደር አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በስሙ ሰይሞለታል፤ ሊሊ በዓሊ የሙዚቃ ስራዎች መደሰት ብቻ ሳይሆን የጤና እክል በገጠመው ጊዜ ሁሉ ከጎኑ ሳትለይ ላለፉት 25 ዓመታት በትዳር አብራው ዘልቃለች፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe