ከአጣዬው ግጭት ጋር በተያያዘ የተያዙ 81 ተጠርጣሪዎች ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ መደረጉንም ነው ያስታወቀው፡፡
እንባ ጠባቂ ምርጫ ተከናውኖ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እስከሚደረግ ድረስ የሀገሪቷ የጸጥታ ተግባር በተማከለ ኮማንድ እዝ ሊመራ ይገባልም ብሏል፡፡
ከአጣዬው ግጭት ጋር በተያያዘ ተይዘው የነበሩ 81 ተጠርጣሪዎች ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ መደረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከበላይ አካል በተሰጠ ትእዛዝ በሚል መለቀቃቸውንም አስታውቋል፡፡ ይህ መሆኑ ለህግ የበላይነት አለመከበርን እንደሚያመጣ ነው የገለጸው፡፡
ግጭቱ ህዝብ ለህዝብ ነበር የሚል ግምገማ እንደሌለውም በማስታወቅም ከመንግስት አስፈጻሚ አካላት እስከ ግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል፡፡
እንደ ተቋሙ ከሆነ በግጭቱ የ303 ንጹሀን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ 369 ዜጎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ዞኖቹ ሰጡኝ ባለው መረጃ መሰረት ከ50 ሺ በላይ ዜጎች የተፈናቀሉም ሲሆን ከ1 ሺ 539 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡
ሆኖም ተፈናቃዮችን በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ ለማረጋገጥ አለመቻሉን ነው ያስታወቀው፡፡
አል ዐይን አማርኛ በግጭቱ 250 ሺ ገደማ ዜጎች ተፈናቅለዋል መባሉን መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
እንባ ጠባቂ በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ እየደረሰ ባለው ሞትና መፈናቀልን በተመለከተ መንግስትን በቸልተኝነት ወቅሷል፡፡
ህብረተሰቡን ማደራጀትና ማሰልጠን ይገባል በሚል ምክረ-ሃሳብ ቢያቀርብም አሁንም ችግሩ እንደቀጠለ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
በመተከል ሽፍቶች ትጥቅ ሳይፈቱ ድርድር መደረጉ እና ወደ ተሃድሶ መግባታቸው ስህተት እንደነበር እንዲሁም በዞኑ እንዲሰለጥኑ የተደረጉ ከ10 ሺ በላይ ታጣቂዎች በቂ ትጥቅ እንዳልነበራቸውም ገልጿል፡፡
ወለጋን የጸጥታ ስጋት አካባቢ አድርጎ ባለመሰራቱ ምክንያት ንጹሀን መሞታቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡ ከንጹሃኑ ሞት በኋላ “ጉዳት አድራሾች ተደመሰሱ የሚል ዜና ከማግስቱ ጀምሮ መቅረቡ አግባብነት የለውም”ም ብሏል፡፡
የሶማሌ እና በየአፋር ክልሎች የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግብ በቶሎ መፍትሔ ባለማግኘቱ ምክንያት ዛሬም ድረስ ዜጎች እየሞቱ መሆኑን በማስታወስም የከፋ እልቂትና መፈናቀል ከማሰከተሉ በፊት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
መንግስት ለችግሮች መፈጠርና መባባስ ምክንያት የሆኑ አመራሮቹን ሊያጠራና እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ነው ያስቀመጠው፡፡
“የሰላም ሚኒስቴር አደረጃጀት ሊከልስ ይገባል” ሲልም የመፍትሔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ሚኒስቴሩ ሁለት ተቃራኒ ተግባራትን ማለትም የሰላም ግንባታ እና የጸጥታ ማስከበር ሃላፊነት ተሰጥቶታል ነው ያለው፡፡
የሰላም ግንባታ በሂደት እና በተራዘመ ትምህርት እና ግንዛቤ ስራ የሚከናወን ሲሆን በአንጻሩ የጸጥታ መዋቅሩ ግን በቅጽበት በሚወሰኑ ውሳኔዎች እና እርምጃዎች የሚከናወን ነው እንደ እንባ ጠባቂ ገለጻ፡፡
በመሆኑም የጸጥታ መዋቅሩ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ራሱን በቻለ ተቋም ሊመራ አልያም በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ሊሆኑ፤ ምርጫው ተከናውኖ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እስኪደረግ ድረስ የሀገሪቷ የጸጥታ ተግባር በጊዜያዊነት በተማከለ ኮማንድ እዝ ሊመራ ይገባል፡፡
ትላልቅ ከተሞች እና የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግብ ባለባቸው ቦታዎች ከሁሉም ክልሎች በተውጣጣና በፌደራል ፖሊስ ጥላ ስር በሆነ ልዩ የፖሊስ ሀይል ይጠበቁ የሚል ምክረ ሃሳብንም አቅርቧል፡፡
በሁሉም ክልሎች በተለይ በአማራ ክልል ለሚገኙ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተፈናቃዮች የእለት ደራሽ እርዳታ እና በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራም ጠይቋል፡፡