ዘሪሁን አሰፋው  መምህር፤ተመራማሪና የሥነ ፅሑፍ ሐያሲ

በቁጥር የሚተመን ጊዜ አቶ ዘሪሁን አሰፋውንና የሱን መሰሎች በኖሩበት ዘመን ውስጥ የፈጸሙትን ተግባር ቁልጭ አድርጎ አያሳይም፡፡ መሽቶ በመንጋት የተፈጥሮ ኡደት የሚመላለስ ቀን፣ሳምንት፣ወርና ዓመት እየተባለ ቀን ቆጥሮ ዘሪሁን ጥቅምት 10 ቀን 1944 ዓ.ም በደሴ ተወልዶ 71 ዓመት ኖሮ ለየካቲት 28 አጥቢያ አረፈ ብሎ መናገር አቶ ዘሪሁንን (መምህራችን፤ወንድማችንን፣ጎደኛችንን) አይገልፅልንም፡፡ ዘሪሁንን ለመግለጽ ከቀንና ዘመን ቁጥር በላይ የሆኑ እጅግ በርካታ ሥራዎች አሉት፡፡ ዝርዝራቸውን በአጭር በአጭሩ ከማቅረባችን በፊት ግን አባቱ አቶ አሰፋው ጎበናንና እናቱን ወይዘሮ ስህን ጎበናን የወንድማችን የሆነውን እንዲሆን መሠረቶች ናቸውና ስማቸውን በክብር እናነሳለን፡፡

His book
 1. ትምህርት

ወጣቱ ዘሪሁን በደሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመምህር አካለወልድ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃውን ደግሞ በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተማረ፤ በወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት ከመደበኛ ትምህርቱ በተጨማሪ የትምህርት ቤቱ የኪነጥበብ ክበብ አባል ሆኖ በትያትር ትወና፣ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት በመሳተፍ በኋለኛው ዘመኑ እድሜውን ሙሉ ለዋኘበት የሥነጹሑፍ ሙያ መሠረቱን እንዳደላደሉለት የሚታወቅ ነው፡፡

በ1962 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በልዑል በእደማሪያም የመሰናዶ ትምህርት ቤት መማር ከጀመረ በኋላም የጥበብ ጥሪውን ተከትሎ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል አባል በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮት የነበረውን ኪነጥበባዊ ተግባሩን ገፍቶበታል፡፡

በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑ ክፍለትምህርት ከ1963-1965 የሦስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠቃለለ በኋላ በወቅቱ አስፈላጊ በነበረው የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት መርሀግብር በመሳተፍ በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በከረን ከተማ አንድ ዓመት ያህል አስተምሮና ግዳጁን ተወጥቶ ተመልሷል፡፡ ከዚያም በኋላ በ1967 በታወጀው የዕድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ተሳታፊ በሆን በአድዋ እና አካባቢው ተመድቦ ግዳጁን ተወጥቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲ አገልግሎትና በእድገት በኅብረት ዘመቻ ምክንያት ለሦስት ዓመታት ያቋረጠውን ትምህርት ለመማር ቢሞክርም ወቅቱ ልዩ የፖለቲካ ኃይሎች ቁርቁስና ትርምስ፣ ነጭ ሽብር፣ ቀይ ሽብር ምክንያት ተረጋግቶ መማር ባለመቻሉ በአርሲ ክፍለ ሀገር በአሰላ ከተማ አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛና እንግሊዝኛ እያስተማረ ዓመት ያህል ቆይቶ ተመለሰ፡፡ ያቋረጠውንም ትምህርት በሚገባ አጠናቅቆ በ1970 በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን እገኘ፡፡ የሁለተኛ ዲግሪውንም ከዚሁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነጹሑፍ ትምህርት ክፍል ከ1973-1975 ተከተትሎ በሥነጽሑፍ የማስተርስ ዲግሪ ተቀበለ፡፡

 1. ሥራ፣

አቶ ዘሪሁን አስፋው ገና በጠዋቱ በመምህርነት በሥነጽሑፍ አድባር ሰው ለመሆኑ ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርቡት ዝርዝሮች ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ በልጅነቱ በትምህርት ቤት የኪነጥበብ ክበብ የጀመረውን ንቁ ተሳታፊነት ቀስበቀስ እያሳደገና እያጠናከረ የሕይወቱ ድርና ማግ ያደረገ፣ በጥልቅ ተመልካችነትም ሥነጽሑፍን የተጠበበ፣ የመረመረ፣የሔሰ፣ያገራችን እንጋፋና ወጣት ተመራማሪዎችንም ሆኑ ፈጣሪዎች በረቂቅ የአስተሳሰብ መንገድና ያሠራር ብልሃታቸው ያስገኙትን ትሩፋት አንጥሮ ለማሳየት ዘወትር የሚተጋ ነበር፡፡

ከላይ እንደተጠቆመው፣ የአቶ ዘሪሁን አሰፋው ወነኛ ጥሪ መምህርነት በተለይም የሥነጽሑፍ መምህርነት በመሆኑ፣ በበርካታ ቦታዎች በመምህርነት አገልግሏል፡፡ የመጀመሪያውን የማስተማር ሥራውን የጀመረው ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ በዩኒቨርሲቲ አገልግሎት በከረን፣በአድዋም  በመሠረቱ ትምህርት፣ የአርሲ ክፍለ ሀገር በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ በ1971 ዓ.ም ተቀጥሮ እስከ ሌክቸረርነት ደረጃ በማደግ እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ ሕይወቱ እስካለፈበት ዕለት ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው ዓ.ም የኢትዮጵያ ቋንቋ ሥነጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት ውስጥ በተለያዩ ማዕረጎች የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግሏል፡፡ ይህም ማለት፤

 • ከ1975 – 1986 በሌክቸረርነት
 • ከ1986 – 1993 በረዳት ፕሮፈሰርነት
 • ከ1993 – ጀምሮ ሕይወቱ እስካለፈበት ድረስ በተባባሪ ፕሮፈሰርነት ሊያገለግል ቆይቷል፡፡

አቶ ዘሪሁን በተለይ በሥነጽሑፍና ከሥነጽሑፍ ጋር ተያያዝ የሆኑ ኮርሶችን ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የዶክተሬት ዲግሪ ድረስ በማስተት በርካታ ምሁራንን አፍርቷል፡፡ ካስተማራቸው ኮርሶች መካከልም፣ የሥነጽሑፍ መሠረታዊያን፣ የዝርውና ሥነግጥም ፈጠራ ድርሰት፣ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ቅኝት፣ የህጻናት ሥነጽሑፍ፣የሥነጽሑፍ ምርምር፣የአማርኛ ሥነጽሑፍ ታሪክና ዕድገት፣ የሥነጽሑፍ ታሪክና ዕድገት፣ የሥነጽሑፍ ሒስ እንዲሁም ሒስ እንዲሁም የፎክሎር ቴዮሪ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የአቶ ዘሪሁን አስፋው ተቀዳሚ ሥራ ጥናትና ምርምር ነበር፡፡ በዚህ ረገድም በርካታ ተሳትፎና አበርክቶ የነበረው ሊቅ ነበር፡፡ ምርምርን ከማስተማር በተጨማሪ 143 የመጀመሪያ ዲግሪ ፣ 60 ማሰተርስ ዲግሪ ፣ 20 የዶክተሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በምርምር ሥራዎቻቸው አማክሯል፣  በማማከር ላይ ነበር፡፡  እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ በባህርዳር የኒቨርሲቲ የማስተርስና ዶክትሬት ተማሪዎችን የምርምር ሥራዎች በመገምገም፣ ዩኒቨርሲቲዎች የሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍሎችን ሲያቋቁሙ መርሀግብሮቻቸውን በመገምገም፣ የጥናትና የአሠራር እንዲሁም የአተገባበር ብልሃቶችን በማመላከት አስተዋፅኦ ማድረጉን  የተጠቀሙ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡

አቶ ዘሪሁን ተማሪዎችን በምርምር ከማገዝም አልፎ በግሉ ሠርቶ ያቀረባቸው ለህትመት ያበቃቸው ብዙ ሥራዎች አሉት፡፡ ከሥራዎቹ መካከል አምስት መጻህፍት፣

 • የሥነጽሑፍ መሠረታውያን፣
 • ልቦለድ አዋጅ የቀደምት ደራስያን አጫጭር ትረካዎች፤
 • ሥነጽሑፍ ለማኅራዊ ለውጥ ከፖፑሌሽን መገናኛ ማእከል ጋር፣
 • ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ፣ ሥነጽሑፍዊ ተህዝቦት፣
 • በሥነጽሑና በፎክሎር ላይ የተሠሩ ዲግሪ ማሟያ ጥናቶች አጠቃሎዎች ስብስብ፣

ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

ከዚህ  መጻሕፍና በተጨማሪ እጅግ በርካታ  የምርምር ጽሑፎች በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ መጽሔቶችና መድበለ ጉባኤዎች ላይ ታትመውለታል፡፡ በምርምር ሥራዎቹ ያልተዳሰሱ ሥነጽሑፋዊ ርእስ ጉዳዮች ቢኖሩ ምናልባት ጥቂቶች ሆነው በቀጠሮ ተራቸውን የሚጠብቁ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መገመት የሚቻል ይመስላል፡፡ ያልታተሙትን የጥናት ሥራዎቹን በየጭብጣቸው አደራጅቶ ተከታታይነት ባላቸው ቅፆች ለማሳተም በማለም በአይነት በአይነታቸው አዘጋጅቶ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ያውቃሉ፡፡

 

አቶ ዘሪሁን ከላይ የተጠቀሱትን የታተሙትንም ሆነ ያልታተሙትን የምርምር ስራዎቹን በበርካታ ሀገራዊና  አለም አቀፋዊ ጉባኤዎች አቅርቧል፤በግል ማህደሩና ከቤተሰቡ ከተገኙት መረጃዎች ላይ መመልክት እንደተቻለው አያሌ ጥናትና ምርምር ካቀረበባቸው መድረኮች ዋና ዋናዎቹ መሀከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፤ ትምህርት ሚኒስቴር፤ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ፤ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር፤ፖፕሌሽ ሚዲያ ሴንተር፤ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፤ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ፤ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲና ማይነር ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሾች ናቸው፤

 

አቶ ዘሪሁን ከእነዚህ የወል መድረኮች በተጨማሪ በግል ተጋብዞ ልምዱንና እውቀቱን  ያካፈለባቸው መድረኮች አሉ፤ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ባህል እየተለመደ የመጣው በመፅሐፍ ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ በመገኘት ጎልማሶች ይበልጥ እንዲበረቱ ወጣቶች በእውቀትና በልምድ እንዲበለፅጉ ሙያዊ ፍኖት በማሳየት በእጅጉ የሚተገ ቸር መምህርና ተመራማሪ ነው፤

አቶ ዘሪሁን ለረጅም ዓመታት በነበረው የመምህርነት፤ በምርምር ስራዎቹና በማህበራዊ አገልግሎቱ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት በርካታ የምስጋና የምስክር ወረቀቶች ተበርክተውለታል፤ ከእነዚህም መሀከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂውማኒቲና ቋንቋዎች ተቋም፤የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ኮሌጅ፤ የአፍሪካ ሴቶች ደራሲያ ማህበር፤ የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት፤እና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ይጠቀሳሉ፡፡

ከጥናትና ምርምር መደበኛ መድረኮች አለፍ ሲልም አቶ ዘሪሁን እውቀቱንና ልምዱን  ለሀገር መስጠትና ለህብረተሰብ

ንቃት ለማዋል ሳይታክት ይሰራ እንደነበር ቀደም ባሉት ዓመታት በራዲዮና በቴሌቪዥን ይሰጣቸው የነበሩ ገለፃዎችና  ሙያዊ ማብራሪያዎች ህያው ምስክሮች ናቸው፤ አቶ ዘሪሁን ከጥናትና ምርምር ስራው ጎን ለጎን በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ በአማካሪነትና በሙያዊ ዳኝነት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ ከዚህም ውስጥ፡-

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

 • የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ፅሁፍ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር (ከ1986- 1988)
 • የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ዲን (ከ1988- 1993)
 • የኢትዮጵያ ጥናትና ምርመር ተቋም የቦርድ አባል (ከ1993 – 1994)
 • የኢትዮጵያ ጥናትና ምርመር ተቋም ኤዲቶሪያል ቦርድ አባል (ከ1988- 1994)
 • የ13ኛው የዓለም አቀፍ ጥናት ጉባኤ የስነፅሁፍ ዘርፍ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ
 • የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ( በአካዳሚው አደራጅ ኮሚቴ እስከ ህይወት ዘመን ተሳትፎ)
 • የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሑፍ ዓመታዊ መፅሔት ዋና ኤዲተር (ከ2003 -2007) ሆኖ አገልግሏል፡፡

አቶ ዘሪሁን የእርሱ ብቻ ተብሎ የሚጠቀስለት ልዩ ባህሪ አለው፡፡ የማስታወስ ችሎታው ፡፡ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ዕድሜ ድረስ ያለፈባቸውን ሁነቶች፤ አብሯቸው የተማራቸውን ሰዎች ፤በልዩ ልዩ አጋጣሚ የተዋወቃቸውን ግለሰቦች ከብዙ ዓመታት በኋላ እንኳ ሲያገኛቸው በስማቸው ጠርቶ ነው የሚናግራቸው፡፡

በመምህርነት ተመድቦ ባስተማረባቸው ቦታዎች ሁሉ ካስተማራቸው ተማሪዎች መሀከል በድንገት ቢያጋጥሙት በስማቸው ጠርቶ ማናገር የተለመደ  ባህሪው ነው፤ በተለይ በዩኒቨርሲቲ ያስተማራቸው ተማሪዎችን ስም፤ የተመካሪዎችን የጥናት ርዕስ በዝርዝር ማስታወሱ የስራ ባልደረቦቹን መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ስብዕና የተላበሰ ሰው ነው፡፡

የስራ ባልደረቦቹን እንደ ወንድምና እህት፤ ተማሪዎቹን እንደ ልጅና እንደ ጓደኛ ያይ የነበረው አቶ ዘሪሁን ከመልካም ስነ ምግባሩ ስልጡን በነበረው ስብዕናው ሳይሰስነት እንዳካፈለ ፤በኑሮ አጋጣሚ የሚያጋጥሙትን አንዳንድ መጥፎ አጋጣሚዎች  በሆደ ሰፊነት ቀለል አድረጎ በማሳለፍ አንዳንዱንም በፈገግታና በዝምታ  በማሳለፍ  በስራ አካባቢ በሚፈጠር ጊዜያዊ ችግር አንድም ቃል ክፉ ቃል ከአፉ ሳይወጣው  ሰዎችን አክብሮ እንደተከበረ በቅርብ ጓደኞቹ ‹ዘሪቾ› በተማሪዎች ‹ጋሽ ዘሪሁን› እንደተባለ 2015ን መዝለል ተስኖት አካላዊ ፍፃሜው ሆነ፡፡

አቶ ዘሪሁን ከውድ ባለቤቱ ወይዘሮ የትምወርቅ አክሊሉ ጋር ትዳር መስርቶ ከ40 ዓመታ በላይ የኖረ ሲሆን ከትዳሩም አንዲት ሴትና ሶስት ወንድ ልጆችን አፍርቷል፡፡

በድንገተኛ ሕመም በተወለደ በ71 ዓመቱ ሰኞ፣ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ያረፈው አቶ ዘሪሁን አስፋው፣ ከማረፉ ሦስት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሰው መሆን ፊልሞች ጋር በመተባበር ለሚሠራው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ባለ 48 ክፍል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ሙያዊ ሐሳቡን ሲያካፍል ውሎ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበረው ዘሪሁን አስፋው ሥርዓተ ቀብር ረቡዕ፣ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

(ይህ የአቶ ዘሪሁን አስፋው የህይወት ታሪክ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ያነበበው ነው፡፡)

(ቁም ነገር መፅሔት ቅፅ21 ቁጥር 428 ሚያዝያ 2015)

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe