“የህወሓት ደጋፊዎች ገንዘብ የሚያሰባስቡት የትግራይን ሕዝብ በጦርነት ለማስጨረስ ነው” – ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም

“በውጭ አገር የሚገኙ የህወሓት ደጋፊዎች ገንዘብ የሚያሰባስቡት የትግራይን ሕዝብ በጦርነት ለማስጨረስ ነው” ሲል ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋ ማርያም ገለጸ።

የትግራይ ወጣት ለተወሰኑ ሰዎች ሀሳብ ብሎ ራሱን መስዋዕት ማድረግ የለበትም ብሏል።

ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርጓል።

በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር እርምጃው በኋላ መንግስት በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች እያደረገ ያለው ሰብአዊ ድጋፍ በአብዛኞቹ አካባቢዎች ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝ ጋዜጠኛ አርአያ ገልጿል።

ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች “የህወሓት ርዝራዦች” ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀበሉ የማስፈራራት ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ ብሏል።

ላለፉት 30 ዓመታት በነበረው የህወሓት አገዛዝ የትግራይ ሕዝብ የራሱን ሀብት እንዳያመነጭና በእርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ እንዲኖር መደረጉን አመልክቷል።

የህወሓት አመራሮች ለትግራይ ሕዝብ ከሚሰጠው እርዳታ ላይ በመስረቅ በጭቆና እንዲኖርና “የትግራይ ሕዝብ እንዳይሞት ግን እንዳይናገር” በሚል ሀሳብ ትንሽ ድጋፍ በማድረግ ከእርዳታ እንዳይወጣ ሲሰሩ እንደነበር ተናግሯል።

“በውጭ የሚገኙ የህወሓት ደጋፊዎችም በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ የሚያሰባስቡት ለሕዝቡ አዝነው ሳይሆን ውጊያውን በማስቀጠል ንጹሃንን ለማስጨረስ ነው” ሲል ነው ጋዜጠኛ አርአያ የገለጸው።

ገንዘቡ የሚሰበሰበው ለበጎ ዓላማ ባለመሆኑ ሁሉም የሚመለከተው አካል ይህንን የማጋለጥ ሃላፊነት አለበት ብሏል።

በተጨማሪም “በውጭ የሚገኙ የህወሓት ደጋፊዎች” መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር የገባበትን ምክንያት በተዛባ መልኩ በማቅረብ መንግስትን ጥፋተኛ የማድረግ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

የሕግ ማስከበር እርምጃው መንስኤ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመው ጥቃት እንደሆነ በግልጽ ማስረዳት ይገባል ነው ያለው ጋዜጠኛ አርአያ።

ህወሓት በስልጣን በነበረበት ወቅት የትግራይን ሕዝብ የጠቀመው ነገር የለም፤ የጠቀመው የራሱን የተወሰኑ አመራሮች ነው ብሏል።

የትግራይ ወጣት ይህን በመረዳት በተወሰኑ ሰዎች ሀሳብ የጥፋት መጠቀሚያ መሆን እንደሌበት የገለጸው ጋዜጠኛ አርአያ የራሱን መጻኢ ጊዜ የሚወስንበትን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ተናግሯል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ባለው የሰብአዊ መብት ጉዳይ የሚያወጣው ሪፖርት ሁሉንም አካላት ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ ጋዜጠኛ አርአያ ገልጿል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ትናንት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ክልል ወጣቶች መጻኢ ዕድላቸው ብሩህ እንዲሆን ለ”ጥፋት ቡድኑ ተላላኪ” ከመሆን መቆጠብ እንዳለባቸው ማስገንዘባቸው ይታወሳል።

Sourceኢዜአ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe