ከብስራተ ወንጌል ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ሬድዮ በልጆች ፕሮግራም አዘጋጅነታቸው የሚታወቁት ጋሽ ሰሎሞን ገብሥላሴ ህዳር 12 2018 በ83 ዓመታቸው ማረፋቸውን ቤተሰቦቻቸው ለተወዳጅ ሚድያ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
በ2014 በሚድያና ጋዜጠኝነት የበጎ ሰው ተሸላሚ የነበሩት ጋዜጠኛ ሰሎሞን ገብረሥላሤ የሕይወት ታሪካቸው በሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ ( መዝገበ አእምሮ ) ቅፅ አንድ ላይ ከ179 ባለሙያዎች ጋር መሰነዱ ይታወሳል። አቶ ሰሎሞን የራሳቸውን ግለ-ታሪክ አምና በህዳር ወር 2017 ፅፈው አሳትመዋል።
ጋሽ ሰለሞን ገብረስላሴ የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ቅድስተማሪያም›› በሚባል ስፍራ ነበር ፡፡ ጊዜውም በሐምሌ 1934 ፡፡ጋሽ ሰለሞን ገብረስላሴ ገና የ 7 አመት ልጅ ሳሉ ቦንብ በመፈንዳቱ 2 እጃቸውንና አንድ ዓይናቸውን በአደጋው ምክንያት ካጡ በኋላ በአሰላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል፡፡
በ1959 አ.ም የልጆች ፕሮግራምን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ፣ፈተናውን ተፈትነው እንዳለፉ ወዲያውኑ የልጆች ፕሮግራም ማዘጋጀት የጀመሩበትን አጋጣሚ ዛሬ ድረስ አይዘነጉትም፡፡ ከእርሳቸው በፊት አንድ ባለሙያ የልጆች ፕሮግራም ለማዘጋጀት ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ነበር አቶ ሰሎሞን የተተኩት፡፡
የልጆች ፕሮግራም በየሳምንቱ ቅዳሜ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ከ10 ደቂቃ ጀምሮ የሚቀርብ ፕሮግራም ሲሆን ከልጆች ዓለም የሚለውንም ስያሜ ያገኘው ደርግ ብሥራተ ወንጌልን ከወረሰው በኋላ በደርግ ጊዜ ነበር፡፡ ጋሽ ሰሎሞን አብረዋቸው የሠሩ ልጆችን በፍጹም አይዘነጓቸውም፡፡ እንደ ልጆቼ ነበር የማያቸው ሲሉ ለልጆቹ ያላቸውን ፍቅር ገልፀው ነበር ፡፡ አቶ ሰሎሞን ከ40 ዓመት በላይ ከልጆች አለምን ሲያዘጋጁ ለትውልድ አንድ ትልቅ መሰረት እያስቀመጡ እንደሆነ ያስቡ ነበር፡፡ ከሬድዮ አድማጮች ባሻገር ከእርሳቸው ጋ ሆነው ፕሮግራሙን የሚሠሩት ልጆች ላይም አንድ በጎ ተጽእኖ ማሳረፋቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ከእርሳቸው ጋር ሆነው ከልጆች አለምን ሲያሰናዱ የነበሩ ታዳጊዎች ዛሬ ትልቅ ቦታ ደርሰው ሀገራቸውን ለማስጠራት ችለዋል፡፡ .ቀብራቸው ቅዳሜ ህዳር 13በጴጥሮስ ወጳውሎስ ከ 6-7 ተፈፀማል፡፡

