የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው የቀብር ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሙዚቀኛው አድናቂዎች እና ዘመድ ወዳጆቹ ተገኝተዋል።

ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱን ‘ሜጀር ክላርኔት’ በማድረግ የተመረቀ ሲሆን የአልቶ ሳክስፎን እና ክራር ተጨዋችም ነበር።

በአስደናቂ ክላርኔት ጨዋታው የሚታወቀው ዳዊት ፍሬው በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው፣ የታላላቅ ሙዚቃ አቀናባሪዎች /ኮምፖዘሮችን/ የክላርኔት ሥራዎች ተጫውቷል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ውስጥም በክላርኔት እና አልቶ ሳክስ ተጨዋችነት ለተወሰኑ ዓመታት በማገልገል በግሉ የመጀመሪያውን በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ አልበም፣ በፈለቀ ኃይሉ አቀናባሪነት ለማሳተም ችሏል።

ከ2000 እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ከተቋቋመው የ”አዲስ አኩስቲክስ” ባንድ ጋር አልበም የማሳተም እና በበርካታ ሀገራት ኮንሰርት የማቅረብ ዕድል ነበረው።

በተከታታይ ሦስት የመሣሪያ ቅንብር ሥራዎችን በአልበም ያሳተመው ዳዊት ፍሬው ለሙዚቃ ሥራ በሄደበት ጣሊያን ሮም ከተማ በ44 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በድንገት በሞት መለየቱ ይታወቃል።

አስከሬኑ በክብር ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ የተለያዩ የሽኝት መርሐ-ግብሮች ተሰናድተውለት በዛሬው ዕለት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብሩ መፈጸሙን ኢዜአ ዘግቧል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe