አንድ መንግስት ሰራተኛ ተመዝኖ እና ስልጠናም ወስዶ ከሚጠበቀው ዝቅተኛ ውጤት ካመጣ ከስራ ይባረራል፡- መኩሪያ ኃይሌ
በሲቭል ሰርቪስ ማሻሻያ መሠረት የሚያርፈድና ከስራ የሚቀር ሰራተኛ ከደሞዙ እንዲቆረጥ ይደረጋል ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሶስት ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለህዘብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
በዚህም የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ የሰራተኛ ምዘናን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሰራተኞቹን ለመመዘን የሚያስችል 144 ሺህ አከባቢ ጥያቄዎች መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ሰራተኛው የሚመዝነው በሁለት ነገር መሆኑን ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ ገልፀው 1ኛው ባህሪ ሚዘና ሲሆን 2ኛው ደግሞ የተማረው ትምህርት ያንን ስራ ያሰራል ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ የስራ ዘርፍ ምዘና ይመዘናል ብለዋል።
በዚህ ተመዝኖ ከሚጠበቀው ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጣ ከሆነ ስልጠና ይሰጣል ብለዋል። በተደጋጋሚ ስልጠና ወስደው ማለፍ ያልቻለ ከስራ ይባረራል እንዲሁም ይህንን ፈተና አልፈተንም ያለ የመንግስት ሰራተኛም ከስራ ይባረራል ብለዋል።
ለዚህም ሁለቱም አካላት ማለትም መንግስትም ወጪ አውጥቶ ሰራተኛ መድቦ ስልጠና መስጠት አለበት፣ ሰራተኛውም ለተልዕኮ ራሱን ማዘጋጀት አለበት ተብሏል።
ይህ ምዘና ሰራተኛውን ለመቀነስ ሳይሆን ለተቋማት ተልዕኮ ለማዘጋጀት ዓላማ ያለው እና ክፍተትን ማዕከል ያደረገ ስልጠና በመስጠት ሰራተኛን ለማብቃት እንደሆነ አብራርተዋል።
የስልጠናው ፕሮግራም በሚንስትሮች ምክር ቤት ተወስኖ ስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶለታል ተብሏል።
አምስት ተቋማት ማለትም አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሲቭል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ፣ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት እና የአፍርካ ልህቀት አካዳሚ የባህሪ ብቃት መገንባት የሚያስችሉ 125 ሞጁሎችን በማዘጋጀት ለስልጠና ዝግጁ አድርገዋል በማለት አብራርተዋል።

