የሚካኤል ታምሬ 4 መልኮች

ከታሪካችን በበቂ ሁኔታ ካልተማርን ተመልሰን ያንኑ ድርጊት መድገማችን አይቀርም፤›

ሚካኤል ታምሬ በአራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ አራት የተለያዩ ገጸ ባህሪያትን በመጫወት አድናቆትን ያገኘ አርቲስት ነው፤ ሚካኤል ከ30 አመት በፊት የነበረውን የደርግ ስርአት ዋና ከሳሽ አቃቤ ህግ ሆኖ በኢቲቪ ሲተውን ትወናው ድራማ መሆኑን ያስረሳል፤ ‹ምን ልታዘዝ?› በተሰኘውና ከካፌ አስተዳዳሪነት ወደ እስር ቤት ታራሚነት በተቀየረው መቼት ሚካኤል እንደ አያልቅበት ሆኖ በሃገሬ ቲቪ ይታያል፤ በአርትስ ቲቪ ደግሞ ‹በህግ አምላክ› ድራማ ላይ እንደ ውዳጄ፤ እንዲሁም በዲኤስ ቲቪ ‹በአስኳላ› ላይ እንደ ክፍሌ በመተወን አራት መልኮችን ያሳያል፤ ተጫዋች ከስዎች ጋር ተግባቢና የተሰጠውን ገጸ ባህሪ ጥንቅቅ አድርጎ የሚሰራው ሚካኤል በ‹ምን ልታዘዝ?›ና በ‹ግራ ቀኝ› ድራማ ላይ ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ፐሮዲውሰርም ሆኖ ነው የመጣው፤ በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት ቴአትር መማር ፈልጎ ሲያመለክት ‹አንተማ ፉንጋ ስለሆንክ ቴአትር መማር አትችልም› መባሉን የሚያነሳው ሚካኤል በጥረቱ ህልሙን ለማሳካት መቻሉን ዛሬ በኩራት ይናገራል፤ በድራማዎቹ ገጸ ባህሪያት፤ ይዘት፤አሰራርና ቀጣይ ሂደት ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፤

ቁም ነገር፡አስኳላ፤ በህግ አምላክ፤ግራ ቀኝና ምን ልታዘዝ? በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ የመጡ

ድራማዎች ናቸው፤ በአራቱም ላይ አለህበት፤በአጋጣሚ ነው ወይስ ታሰቦበት የሆነ ነው?

ሚካኤል ፡በአጋጣሚ የሆነ ነው፤ የሚቀድመው ስራዬ ምን ልታዘዝ ነው፤ በፋና ቴሌቪዥን ላይ ከአራት አመት በፊት የተጀመረ ድራማ ነው፤ ፋና ላይ ሲታይ ቆይቶ ሲ ቋረጥ ነው አሁን እንደገና በአዲስ መልክ በሃገሬ ቲቪ ላይ የጀመርነው፤

ቁም ነገር ፤ ግራ ቀኝስ?

ሚካኤል ፤ ግራ ቀኝ አሁን በቅርቡ መታየት ይጀምር እንጂ ስለስራው መነጋገር ከጀመርንና ለመስራት ስናስብ አንድ ሁለት አመት ይሆነናል፤ እኔ በድራማው ላይ ተዋናይ ብቻ ሳልሆን ፕሮዲውሰርም ስለሆንኩ ቀረጻ ራሱ ከመጀመራችን በፊት በቂ ዝግጅት አድርገንበታል፤ ድርሰቱም ለድራማ በሚሆን መልኩ አስቀድሞ ተጽፎ

ያለቀ በመሆኑ መታየት የጀመረው ቀረጻ ከጨረስን በሃላ ነው፤

ቁም ነገር ፤ አስኳላስ? ሚካኤል ፤የምን ልታዘዝ ክሩ ነው አስኳላን የሚሰራው፤ ምን ልታዘዝ? ድራማ በወቅቱ ሲቀረጽ ደራሲው በሃይሉ ዋጄ ነው ትኩረቱን ትምህርትና የነገው ትውልድ ላይ አድርጎ የጀመረው፤ እናም የተወሰን ሲዝን ከሄዱ በኋላ ነው እኔ ወደ ድራማው የገባሁት፤በህግ አምላክ ከድራማው ፕሮውዲውሰሮች መሀከል አንዱ

አርቲስት አበበ ባልቻ ስለሆነ ለግራ ቀኝ ድራማ ጉዳይ እርሱ ጋር ስሄድ ነው ለምን ይህቺን ፓርት አትጫወታትም ብሎኝ የጀመርኩት፤ ቁም ነገር ፤ግራ ቀኘ ድራማን በኢቲቪ ላይ ለማቅረብ እንዴት አሰባችሁ? ድራማው ፖለቲካዊ ሽሙጥ በመሆኑ ትንሽ ከሄደ በኋል እንቸገራለን ብላችሁ አላሰባችሁም?

ሚካኤል ፤ኢቲቪን የመረጥነው በአጋጣሚ ነው፤ ኢቲቪ ጋር ከመሄዳችን በፊት የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ለማነጋገር ሞክረን ነበር፤ በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ሲቀር ነው ከኢቲቪ ጋር ተነጋግረን ተቀባይነት ያገኘው፤

ቁም ነገር ፤ ድራማውን ቀርጻችሁ ማለት ነው?

ሚካኤል ፤ ቀረጻ አልጀመርንም፤ ስክሪፕቱን ይዘን ነው ያነጋገርናቸው፤ እንደሚታወቀው ኢቲቪዎች አዲስ ህንጻ እየሰሩና ሪፎርም እያደረጉ ስለነበር ከመግባባት ላይ ልንደርስ ችለናል፤

ቁም ነገር ፤ ስምምነታችሁ ምንድነው? የማስታውቂያ ክፍፍል ነው?

ሚካኤል ፤አይደለም፤ ኢቲቪ የድራማው ኤክስኪዩቲቭ ፕሮውዲውሰር ነው፤ ለእኛ በቁርጥ ክፍያ ከፍሎን ነው ድራማውን የሚያሳየው፤

ቁም ነገር ፤የዩቲዩብ ገቢስ?

ሚካኤል ፤ የእነርሱ ነው፤

ቁም ነገር ፤ እንግዲህ እነዚህ አራት ድራማዎችን የሰራሃቸው ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ነው፤ በዛሬ ጊዜ አንድ ፊልም እንኳ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሁለትና ሶስት አመታት ይፈጃል፤ አንተ በምን ጊዜህ ነው የሰራሃቸው?

ሚካኤል ፤ጊዜን በተመለከተ እኔ ጊዜዬን በአግባቡ ነው የምጠቀመው፤ የብዙ ሰዎች ችግር የጊዜ እጥረት ሳይሆን

የጊዜ አጠቃቀምን አለማወቅ ይመስለኛል፤በፕሮግራም የምትመራ ከሆነ የያዝከውን ስራ ማጠናቀቅ ይኖርብሃል፤ ለምሳሌ ግራ ቀኝ ድራማን 12ቱ ክፍል ተፅፎ አልቆ ስለነበር ቀረጻ የጀመርነው በሳምንት ቢያንስ ሁለት ክፍል እንቀርፅ ነበር፤ አልፎ አልፎ ካጋጠሙን መስተጓጎሎች በቀር በፕሮግራማችን መሰረት ነበር የሄድነው፤

ቁም ነገር ፤ እንዴት ተሳካላችሁ?

ሚካኤል ፤ በመጀመሪያ ደርጃ ስክሪፕቱ ተጽፎ አልቋል ብዬሃለሁ፤ስለዚህ ተዋናዮችን ከአዘጋጁ ጋር ሆነን ከመረጥን

በኋላ ስክሪፕቱ እንዲጠና ነው ያደረግነው፤ እንደሌላው ድራማ እዛው በእዛው እየተናበብን አይደለም የተሰራው፤

ቁም ነገር ፤እንደ መድረክ ቴአትር አጥንታችሁ ማለት ነው?

ሚካኤል ፤ አዎ፤ ድራማው ሳታየር ኮሜዲ ስለሆነ አጥንተህ ከሆነ የምትሰራው ከራስህ የሆነ ቃል አምጥተህ የመጨመር እድል አይኖርህም፤በእዛ ላይ ድራማውን እንዳየኸው እኔ የምናገርው ወይ በጠበቃው

አልያም በዳኛው ንግግር ላይ ተነስቼ ነው፤ እነርሱም የሚናገሩት በተመሳሳይ መልኩ ነው፤ በመሆኑም ከተጻፈው ውጭ ለመናገር አይቻልም፤ ለዚህም ነው በሳምንት ሁለት ቀን እየተገናኘን እንናበብ የነበረው፤ ስንናበብ

የሚስተካከል ነገር ካለ ያኔ ተነጋግረን እናስተካክለዋለን፤

ቁም ነገር ፤ የተዋናይ ምርጫ ላይ እንዴት ሶስታችሁ ተገናኛችሁ?

ሚካኤል ፤እኔ እንግዲህ እንደ ተዋናይ ብቻ ሳይሆን እንደ ፕሮዲውሰርም ከአዘጋጁ ጋር እናወራ ነበር፤ እናም የዳኛውን ገፀ ባህሪ አቤ ቢጫወተው በሚል ሄጄ ሳናግረው አቤ በአጋጣሚ መጽሃፉን ያውቀው ስለነበር በጣም ነው ደስ ያለው፤ ግሩሜም ለቦታው በጣም ተስማሚ ሰው ስለነበር ተሟላ ማለት ነው፤ በነገራችን ላይ አቤ የዳኛውን ገጸ ባህሪ አልጫወትም ቢል ኖሮ ድራማውን ፕሮዲውስ እኔ ላላደርገው ሁሉ እችል ነበር፤

ቁም ነገር ፤ሶስታችሁ ከአሁን በፊት አንድ ላይ የሰራችሁት ድራማ/ፊልም አለ?

ሚካኤል ፤የለም፤ በተናጠል አንዳችን ከሌላችን ጋር በተለያየ ፊልም ላይ ሰርተናል፤ ሶስታችንም በአንድ ስራ ላይ ስንገናኝ ግን የመጀመሪያችን ነው፤

ቁም ነገር ፤ደራማው በመጽሃፉ ላይ የተመሰረተ ነው ብትሉም በመጽሃፉ ውስጥ የሌለ ታሪክ አካታችሃል፤

ሚካኤል ፤ምን?

ቁም ነገር ፤ የበጓ ተከሳሽነት፤

ሚካኤል ፤ ትክክል ነው፤ መጽሃፉ 11 ክፍል ብቻ ነው ያለው፤ 12ኛ ክፍሉን ቀደም ካሉት ክፍሎች ጋር ሊናበብ በሚችል መልኩ እኛ ነን ጨም ረን የሰራነው፤

ቁም ነገር ፤ አልተጋነነም?

ሚካኤል ፤ይሄ የበጓ ፓርት ብቻ ሳይሆን ድራማው በአጠቃላይ ተጋኗል የሚሉ አሉ፤ ግን ከታሪካችን በደንብ

ስላልተማርን ነው የተጋነነ የመሰለን፤ ከታሪካችን የተማርን ቢሆን ኖሮ ከ40 አመታት በኋላም ያንኑ የመሰለ

ነገር ደግመን አንሰራም ነበር ብዬ አምናለሁ፤ካለፉት ታሪኮቻችን በጣም ብዙ ልንማርባቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ፤

በታሪኮቻችን ውስጥ እኮ በድራማው ውስጥ ከተጠቀሱት ነገሮች በላይ የሆኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፤ ወጣቶች ተገለው መንገድ ላይ ይጣሉ የነበረበት ታሪክ ነበረን፤በደርግ በኢሕፓና በሜኤሶን መሀከል መገዳደሎች ነበሩ፤ በእዛም በእዚህም ወገን የወደቁት የእኛው ልጆች ናቸው፤ የፍትህ ሂደቱም ፖለቲካ ሲገባበት ምን ሊመስል እንደሚችል ያሳያል፤ ያኔ ብቻ ሳይሆን ለአሁኑም ጊዜ ይሰራል፤ ከታሪካችን በበቂ ሁኔታ ካልተማርን ተመልሰን ያንኑ ድርጊት መድገማችን አይቀርም፤

ቁም ነገር ፤ በድራማው ላይ የሚነሳ የኮፒራይት ጥያቄን በምን መልኩ ነው ያስተናገዳችሁት?

ሚካኤል፤ ድራማውን በዚህ መልኩ ወደ ቴሌቪዥን ልናመጣው ስንወስን ደራሲውን አቶ እያሱንም ሆነ

ተርጓሚዋን ህይወት ታደሰን አነጋግረናል፤ ፈቃደኝነታቸውንም ጠይቀን አስፈላጊውንም ክፍያ ፈጽመን ነው የሰራነው፤ ህይወት እንደውም ድራማውን ስንቀርጽ እየመጣች ታየን ነበር፤

ቁም ነገር ፤ ምን ልታዘዝ ደራማ ላይ ተዋናይ ብቻ አይደለህም፤ ፕሮዲውሰርም ነህ፤ ከፋና ቴሌቪዥን የወጣችሁበት

ምክንያት ምንድነው?

ሚካኤል ፤ ያው ድራማው ሲትኮም በመሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ይነሱበታል፤ በእዛ ላይ መቼቱ ካፌ ነው፤ እና ወደ መጨረሻ ላይ አንዳንድ ጫናዎች መምጣት ሲጀምሩ ድራማውን ባለበት መልኩ ለማስኬድ አልተቻለም፤ በዚህ ምክንያት ቆይ እስኪ ትንሽ ጊዜ እናቁመው በሚል ነው ያቆምነው፤

ቁም ነገር ፤ ድራማውን ሰርታችሁ ስታስገቡ ይህንን አውጡ፤ ይህንን ቁረጡ የሚል ነገር ነበር?

ሚካኤል ፤ የለም፤ እኛ ቀድሞውኑ ለእንደዚህ አይነት አስተያየት እድል ላለመስጠት ጊዜውን አጣበን ነበር

የምናስገባው፤ ቁም ነገር ፤ማለት?

ሚካኤል ፤ማለት እሁድ ለማስተላለፍ ቅዳሜ ማታ ነበር የምናስገባው፤ በእዚህ አጭር ጊዜ አይተው አወጡ ለማለት ጊዜ አይኖራቸውም፤ቢሉንም የምናወጣው ነገር አይኖርም፤ ምክንያቱም የደራሲው ነጻነት መጠበቅ ይኖርበታል፤

ቁም ነገር ፤ ግን ከፋና እንዳቆማችሁ ለምን በራሳችሁ ዩቲዩብ ላይ አልቀጠላችሁትም የሚል አስተያየት

አልነበረም?

ሚካኤል ፤ነበረ፤ትክክለኛ አስተያየት ነው፤ እኛ ግን እስካቆምንበት 34ኛው ክፍል ደረስ በካፌው ውስጥ መባል ያለበትን ነገር ሁሉ ብለናል ብለን እናስባለን፤ ለእዛ ነው መቀጠል ያልፈለግነው፤

ቁም ነገር ፤አሁን ድራማውን በሀገሬ ቲቪ ላይ ነው የጀመራችሁት፤ መቼቱ እስር ቤት ነው፤ የመቼቱ መቀየር ምንድነው የሚነገረን?

ሚካኤል ፤እንግዲህ ድራማው

የተመለሰው ከአራት አመታት በኋላ ነው፤ እንደ ደራሲ ያለፉትን አራት አመታት ስታስብ በጣም ብዙ ነገሮች የተለዋወጡበት መሆኑን ታስባልህ፤ እናም ደራሲው ከአራት አመታት በኋላ አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያውያን በሆነ እስር ቤት ውስጥ መሆናችንን ለማሳየት ነው መቼቱ እስር ቤት ውስጥ የሆነው፤ ከዚህ አስር ቤት ውስጥ እንዴት እንወጣለን የሚለው እንግዲህ በድራማው ሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው፤

ቁም ነገር ፤በካፌው ውስጥ ሴት ገጸ ባህሪያት ነበሩ፤ እስር ቤቱ ግን የወንዶች ብቻ ሆኗል፤ እና ሴት

ታሳሪዎችስ?

ሚካኤል ፤ እንደሚታወቀው በእውኑ አለም ወንድና ሴት እስረኞች ለየብቻ ነው የሚታሰሩት፤ እንግዲህ የደራሲው ምናብ የሚያመጣቸው ከሆነ የሚታይ ነው የሚሆነው፤

ቁም ነገር ፤ ድራማው አሁን እየታየ ያለው ሀገሬ ቲቪ ላይ ነው፤

እንዴት መረጣችሁት?

ሚካኤል ፤ የሀገሬ ቲቪ ሃላፊዎች

ቀደም ሲል ጀምሮ ለድራማው ጥሩ አስተያየት ነበራቸው፤ ለምን አቆማችሁት ሁሉ ይሉን ነበር፤ በመሃል በአዲስ መልክ ለመጀመር ስናስብ ከእነርሱ ጋር ነው የተነጋገርነው፤ ደስተኞች ሆነው ነው በፕሮውዲውሰርነት የተቀበሉን፤ ቁም ነገር ፤ በአስኳላ ድራማ ላይ በእስተርጅና ትምህርት ቤት የገባ የክፍሌ ገፀ ባህሪን ወክለህ ነው የምትጫወተው፤

እንዴት አገኘኸው?

ሚካኤል ፤ እንዳልኩት ከተወሰነ ሲዝን በኋላ ነው እኔ እነ ዋጄን የተቀላቀልካቸው፤ እንደሚታወቀው የሃገራችን ችግር መነሻው ትምህርት ነው የሚል እምነት ነው ያለን፤ዛሬ ትምህርት ቤት ያሉ ታዳጊዎች ላይ ካልተሰራ ነገ ምን አይነት ትውልድ ልናፈራ እንደምንችል ያለንበት እውነታ ይናገራል፤ ዛሬ 12ኛ ክፍል ላይ የሚታየው ችግር እታች ክፍል

ላይ ተኮትኩቶ ያለማስተማር ውጤት እንደሆነ ደራሲው ለማሳየት ሞክራል፤

ቁም ነገር ፤ድራማው በትምህርት ላይ የማተኮሩን ያህል በቀጥታ ከሚመለክተው ትምህርት ሚኒስቴር ያገኛችሁት ድጋፍ ወይም አስተያየት አለ?

ሚካኤል ፤ እኔ ወደ ድራማው ከመምጣቴ በፊት አላውቅም፤ እኔ ከመጣሁ በሃላ ግን ተገናኝተን እንነጋገር የሚል አስተያየት ስለመኖሩ አላውቀም፤

ቁም ነገር ፤ እነዚህን ድራማዎች እየሰራህ ሌላ የሰራኽው ፊልም/ቴአትር አለ?

ሚካኤል ፤አዎ፤ የተሻለ ወርቁን አንድ ፊልም ሰርቻለሁ፤

ቁም ነገር ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለህ ቴአትር መማር ፈልገህ

የጠየቅኸው አንድ መምህር ተዋናይ መሆን እንደማትችል ነበር የነገረህ፤ እንዴት ቻልክ?

ሚካኤል ፤ አዎ፤ መምህሬ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰስ ነው፤ በወቅቱ የአንደኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን እንደጨረስን የዲፓርትመንት ምርጫ ከማድረጋችን በፊት የየዲፖርትመንቱ መምህራን እየመጡ ገለጻ ይሰጡን ነበርና ከቴአትር ዲፓርትመንት የመጣው ጋሽ ተስፋዬ ነበር፤ ጋሽ ተስፋዬ ብዙም ገለጻ ሳያበዛ ቴአትር መማር የምትፈልጉ ተማሪዎች መመዝገብ ትችላላችሁ ብቻ ነበረ ያለው፤ ወዲያው እንደወጣን ጋሽ ተስፋዬ ተከትዬ ‹እኔ ቴአትር መማር ነው የምፈልገው› ስለው ‹አንተ ፉንጋ ነህ ለትያትር አትሆንም› ነበር ያለኝ፤

ቁም ነገር ፤ ቃል ይገነባል፤ ቃል ያፈርሳል፤ አንተ በወቅቱ ወጣት ነህ፤እንዴት ሞራልህ አልተነካም?

ሚካኤል ፤ በወቅቱ እኮ ጋሽ ተስፋዬ እንደዛ ያለኝ እኔን እልህ ለማሰያዘ ብሎ ነው፤

እኔ በወቅቱ ያለ እኔ ድራማ የሚሰራ ማነው እያልኩ የምጎርር ነበርኩ፤ያንን አይቶ ነው ጋሽ ተስፋዬ እልህ አስይዞኝ ቴአትር እንዳጠና ያደረገኝ፤

ቁም ነገር ፤ በኋላ ግን ጋሽ ተስፋዬ ምን አለህ?

ሚካኤል ፤ይሄው አትችልም ብለኸኝ ገባሁ ስለው አእኔም ይህንን ነው የፈለኩት ብሎኛል፤

ቁም ነገር ፤ በወቅቱ ያንተ ባች እነማን ነበሩ?

ሚካኤል ፤ብዙ ልጆች ነበሩ፤ ፍቅር ይልቃል፤ ማንተጋፍቶት ስለሺ፤ነብዩ ባዬ ነበሩ፤

ቁም ነገር ፤ማስተርስ ዲግሪ አልቀጠልክም፤ ምነው?

ሚካኤል ፤ አዎ፤ መጀመሪያ በተማርኩት ትምህርት የተወሰነ ነገር ልስራ ብዬ ነው ያልቀጠልኩት፤በዚህ ትምህርት

መቀጠሉንም ብዙም አላመንኩበትም፤

ቁም ነገር ፤አመሰግናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe