‹‹ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ›› ተብሎ ከሚጠራ ሐሰተኛ የፈጠራ ተቋም፣ ሐሰተኛ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ እንዲሰጥ አድርገዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤት አቀረቡ፡፡
ጄኔራሉ በጠበቃቸው አማካይነት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ እንደገለጹት፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና 112 ድንጋጌ መሠረት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ የሚያቀርበው ክስ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል አይቶና ለይቶ መልስ ለመስጠትና መከላከል እንዲችል የወንጀል ዝርዝር ሁኔታዎችን መያዝ አለበት፡፡
ድንጋጌው አስገዳጅም ስለመሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) ተደንገጎ እንደሚገኝ፣ ምንም እንኳን በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ የሚገኘው በዋናነት በቂ ቢሆንም፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ትርጉም በመስጠት እንዳጠናከረውም የጄኔራሉ ጠበቃ በመቃወሚያቸው አስታውሰዋል፡፡ ይህ የሚረዳው ደግሞ ለተከሳሹ ብቻ ሳይሆን፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በክርክር ሒደት ላቀረበው የወንጀል ክስ፣ በሕግ የተጣለበትን የማስረዳት ሸክም (Burden of Proof) የመወጣት አለመወጣቱን መሥፈርት ፍርድ ቤቶች የሚለዩበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በክሱ የሜቴክ የትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም መመርያ፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት መመርያ፣ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የከፍተኛ ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ እንዳሉ ከጠቀሰ በኋላ መመርያዎቹ በደንበኛቸው እንደተጣሱ ከመግለጽ ውጪ፣ የትኛው መመርያ በማንና በምን መልኩ እንደተጣሰ ያቀረበው እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በአንድ በኩል የትምህርት ተቋሙ ሕገወጥ መሆኑን እየገለጸ በሌላ በኩል፣ ‹‹በኮርፖሬሽኑ የትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም መመርያ መሠረት፣ ትምህርቱን የተማሩ ተማሪዎች የውል ግዴታ አልፈረሙም፤›› ማለቱን፣ እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ የሰው ሀብትና ሥልጠና ማንዋል ቁጥር 9 ከሚፈቅደው ውጪ፣ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ያልሆኑ ሌሎች በተቋሙ መማራቸውን መግለጹን የጄኔራሉ ጠበቃ ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ከመመርያዎቹ አንፃር ዓቃቤ ሕግ የትምህርት ተቋሙን ሐሰተኛ ሊያስብል የሚችለውን የመመርያ ቁጥር፣ ከደንበኛቸው ተሳትፎ አንፃር ለያይቶና ግልጽ አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
እንደ ጠበቃው መቃወሚያ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በኢትዮጵያም ውስጥም ሆነ በአሜሪካ ከማይታወቅ ሐሰተኛ የትምህርት ተቋም ጋር በመመሳጠር፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አሽሽተዋል መባላቸው፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ጠቅሶ ካቀረበው የሕግ ድንጋጌ ጋር አይገናኝም፡፡ ክሱን ከሕግና ከሕግ ጋር ብቻ መርምሮ ማቅረብ ሲገባው፣ ከሕጉ ባፈነገጠ መንገድ ማቅረቡ ተገቢ ስላልሆነ ክሱ መሻሻል እንዳለበትም በመቃወሚያቸው አክለዋል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ቀድመው በመገናኘት፣ በመመሳጠር፣ በሚስጥራዊ መንገድ በመከፋፈል፣ በእጅ አዙር የጥቅም ተካፋይ ስለመሆናቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ቢገልጽም መቼ? የት ቦታ? የት እንደተወሰነ? በሚስጥር ማለት ምን ማለት እንደሆነ? የተካፈሉት ምን እንደሆነ? ወይም ስንት እንደሆነ? በግልጽ አለማስቀመጡንም ጠበቃው አመልክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተከሳሹ የትኛውን ፍሬ ነገር ለይተው መከላከል እንዳለባቸው እንዳያውቁ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ መርምሮ ከመዘናቸው ማስረጃዎች ተነስቶ ማቅረብ ሲገባው፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111(1ለ) ድንጋጌ መሠረት፣ የወንጀሉን መሠረታዊ ነገርና ሁኔታዎች በመግለጽ ፈንታ፣ ‹‹የማይታወቅ ሐሰተኛና የፈጠራ ተቋም፣ ብቃቱም ሆነ አቅሙ የሌለው፣ በሚስጥር በቱሪስት ቪዛ በሕገወጥ መንገድ በማስገባት፤›› የሚሉትን ሐረጎች መጠቀሙ፣ የየትኛው ክስ ማቋቋሚያ እንደሆነ እንደማይገልጽ በክስ መቃወሚያቸው አስረድተዋል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ያላግባብ ተገልግለዋል የተባለው ሥልጣን የትኛው እንደሆነ ተለይቶና ተገልጾ እንዳልቀረበ የጠቆሙት ጠበቃው፣ በመጀመርያ ‹‹በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ወንጀል የሚኖረውና የተከሳሹ ኃላፊነት በቀጥታ የሚያያይዘው ከተጠያቂነት ጋር ሲሆን፣ የተጠያቂነት ወሰን (Scope of Responsibility) ክስ በማንና በምን አግባብ ወይም መነሻ የሚለውን ድንበር ለማበጀት ነው፡፡ መሥፈርቱ የሥልጣኑ ምንጭ የሆነው ሕግ፣ የሥራ ቅጥር ውል፣ የሥራ መዘርዝር፣ የሥነ ምግባር ደንብ፣ ወይም ከኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራር ቦርድ የተሰጠ ሥልጣን ሲሆን ብቻ ነው፤›› ሲሉ ጠበቃው በመቃወሚያቸው ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ የደንበኛቸውን ሥልጣን ምንጭ አለመግለጹን በመጠቆም፣ በግልጽና በተጨባጭ በክሱ መግቢያ ላይ የተገለጸውን ኃላፊነት ያላግባብ ተገልግለዋል ወይም አልተገለገሉም የሚለውን በግልጽ ለመረዳት እንዲቻል፣ የጄኔራሉን ሥልጣን በግልጽ ዘርዝሮ ሊያቀርብ እንደሚገባ ጠበቃው በመቃወሚያቸው ጠይቀዋል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ክንፈን ጨምሮ ሰባት የሜቴክ ኃላፊዎችና አንድ ግለሰብ በሐሰተኛ ተቋም የተማሩ በማስመሰል ሐሰተኛ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ በመስጠት፣ በአጠቃላይ ከ76.3 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ክስ እንደተመሠረተባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡