የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ አረፉ

ለረጅም ጊዜ በከባድ የጤና ችግር በሕክማና ላይ የቆዩት የ88 ዓመቱ አዛውንት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፓፕ ፍራንሲስ ማረፋቸውን ቫቲካን አስታወቀች።
ወደ ጵጵስናው መንበር ከመምጣታቸው በፊት ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ በመባል ይታወቁ የነበሩት ጳጳሱ፤ ቀዳሚያቸው ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2013 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ የተመረጡት።
ፖፕ ፍራንሲስ ለወራት በሕክምና ላይ በነበሩበት ጊዜ ከአደባባይ ርቀው ከቆዩ በኋላ እሁድ ዕለት በተከበረው የትንሳዔ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ለተሰበሰበው ምዕመን በአካል ተገኝተው የትንሳዔ በዓል መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ጳጳሱ ዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም. በፋሲካ በዓል ማግስት ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ካዛ ሳንታ ማርታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በ88 ዓመት ዕድሜያቸው ማረፋቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች።
ብጹዕነታቸው ካርዲናል ፋረል በጳጳሱ ሞት ሐዘን ውስጥ ሆነው “የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣ የቅዱስ አባታችን ፍራንሲስ ሞትን በጥልቅ ሐዘን አሳውቃለሁ” ሲሉ የጳጳሱን ሕልፈት ይፋ አድርገዋል።
ዛሬ ሰኞ ጠዋት 7:35 ላይ ቫቲካን ውስጥ ማረፋቸውን የጠቀሱት ካርዲናል ፋረል “ፍራንሲስ ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰዋል። ሕይወታቸውን ለጌታ እና ለቤተክርስቲያናቸው ሰውተው ነበር” ብለዋል።
የጳጳሱ ህልፈት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በመላው ዓለም ያሉ ካቶሊኮች እና ሌሎችም ሐዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ታላላቅ የአገራት መሪዎችም ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።
የሆላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ስኮፍ “ፖፕ ፍራንሲስ በሁሉም መስኮች የሕዝብ ሰው ነበሩ” ያሉ ሲሆን፣ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ ደግሞ “የሌሎችንም ገጽ የሚያፈካው ፈገግታቸው በመላው ዓለም የሚሊዮኖችን ለመማረክ ችሏል” ብለዋል።
የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይሳክ ሄርዞህ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን “ወሰን የሌለው ርህራሄ” ባለቤት ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
የስዊትዘርላንድ ፕሬዝዳንት ካሪል ኬለር-ሱተር ደግሞ ፖፕ ፍራንሲስን “ታላቅ መንፈሳዊ መሪ፣ የማይደክማቸው የሰላም ተከራካሪ” በማለት በህልፈታቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል።
የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስተር ጆን ስዊኒም በተመሳሳይ ጳጳሱን “የሰላም፣ የመቻቻል እና የዕርቅ” ድምጽ ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ምንጭ፦BbC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe