የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ 25 አባላት ያሉት አዲስ ካቢኔ አዋቅረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ የቀድሞ ካቢኔያቸውን ባለፈው እሁድ መበተናቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ባዋቀሩት ካቢኔ ውስጥ ሁለት ሚኒስትሮችን ከወታደራዊ ሀይል እና ሌሎችን ደግሞ ከቀድሞ አማጺ ቡድን አካተዋል።
ይህም ባለፈው አመት ጥቅምት ወር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ የተፈጸመ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በካቢኔያቸው ውስጥ የፍትህና እኩልነት እንቅስቃሴ የተሰኘው ቡድን መሪና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጂብሪል ኢብራሂምን የገንዘብ ሚኒስትር በማድረግ አካተዋል፡፡
በተጨማሪም የቀድሞውን የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ የሆነችውን መሪያማ አል ሳዲቅ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል ፡፡
አዲስ የተዋቀረው ካቢኔ ሃገሪቱ ብሄራዊ ምርጫ እስከምታካሂድበት የፈረንጆቹ 2024 ድረስ በስልጣን ላይ የሚቆይ መሆኑም ነው የተገለጸው።