የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ “አዲስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት” አሳትሟል።በምረቃው ዕለት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ እንዲሁም የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሣ ተገኝተዋል።
መዝገበ ቃላቱ በመጀመሪያ እትሙ ከ30 በላይ ከሚሆኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የተመረጡ 11,600 ሙያዊ ሥያሜዎችን በአቻ የዐማርኛ ሥያሜዎች ፈቷቸዋል።
ይሄ ከ140 በላይ ምሁራንን ያሳተፈው እና በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ የታተመው መዝገበ ቃላት የሞባይል መተግበርያም እየተዘጋጀለት ነው። ይህ ደግሞ መዝገበ ቃላቱን በእያንዳንዱ ሰው ቤት ማዳረስ ከማስቻሉ በላይ፤ ሥራውን የማይቋረጥ፣ የሚያድግ፣ የሚሻሻል ያደርገዋል።
ሐሳብ አፍላቂዎቹ፣ ፕሮጀክት መሪዎቹ፣ የየሙያው ተርጓሚዎች፣ ገምጋሚዎች እና አርታዒዎችን ያሳተፈው ይህ መዝገበ ቃላት
ለትምህርት ቤቶች፣ ለከፍተኛ የትምህርት እና የምርምር ተቋማት፣ ለመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል
አካዳሚው ይህንን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንግሊዝኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ያዘጋጀው የሳይንስ ዕውቀትን በማስፋፋትና ሳይንሳዊ ባህልን በማዳበር ኺደት ዓይነተኛ ግብአት ለማበርከት ዐልሞ ነው፡፡
ፕሮጀክቱን ሲነድፍም መዝገበ ቃላቱ ወደ ፊት በሌሎች ሀገርኛ ቋንቋዎችም ተተርጉሞ ሰፋ ላለ ኅብረተ ሰብ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታሳቢ አድርጓል፡፡
በአንድ ኅብረተ ሰብ ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ከሚስፋፋባቸውና ሳይንሳዊ ባህልም ከሚዳብርባቸው መንገዶች አንዱ በኅብረተ ሰቡ ውስጥ በስፋት የሚነገሩ ሀገራዊ ቋንቋዎች ሳይንሳዊ ፅንሰ ሐሳቦችን ወርሰው መግለጽ በሚችሉበት ደረጃ ሲበለጽጉ እንደሆነ ይታወቃል።
ይህ መዝገበ ቃላት ከማጣቀሻ ሥራነቱ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ የአእምሯዊ መሠረተ ልማት እና የወደፊት ብልጽግና ላይ የዋለ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት መሆኑን ምሁራን ይስማሙበታል።
መዝገበ ቃላቱ በመጽሐፍ ቅርጽም ይሁን፣ በመተግበርያ ሲሰራጭ
· ኢኖቬሽንን ያፋጥናል፦ ለኢኖቬተርስ እና ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለኢንዱስትሪ ወሳኝ ግብዓት ኾኖ ያገለግላል፤ ግልጽ ሳይንሳዊ ተግባቦትን ያመቻቻል፤ እንዲሁም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በአገር አቀፍ ደረጃ በወሳኝ ዘርፎች ውስጥ በቀላሉ እንዲተገበር ያግዛል።
• የዕውቀት ክፍተቶችን ያጠብባል፦ የሳይንሳዊ ዕውቀትን ተደራሽነት የሚያሰናክሉ የቋንቋ እንቅፋቶችን በእጅጉ በመቀነስ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሳይንስ ዲስኮርስ/ተዋስኦ ውስጥ በምልዐት እና በብቃት እንድትሳተፍ ይረዳል።
• ትምህርትን ያልቃል፦ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቃላትን በአገር ውስጥ ቋንቋ በማስተዋወቅ በተማሪዎች፣ በመምህራንና በተመራማሪዎች ዘንድ ጥልቅ ግንዛቤን ያሳድጋል።
• አገራዊ ቋንቋዎችን ያበለጽጋል፦ ለመነሻ ያህል ሙያዊ ስያሜዎችን ከእንግሊዝኛ ወደ ዐማርኛ ለመተርጎም ጥረት የተደረገበት ይህ የመዝገበ ቃላት ፕሮጀክት፣ ወደፊት በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለሚዘጋጁ መዛግብተ ቃላት መሠረት ይጥላል፡፡ በዚህም የቋንቋዎቻችንን የሳይንሳዊ ዕውቀት ማስተላለፊያነት ዐቅም ያጎለብታል፡፡
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አጋርነት ለፍሬ የበቃው ይህ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት እጅ ለእጅ ተያይዞ ዕውቀትን እና ኢኖቬሽንን ለማሳደግ ያግዛል።
ተወዳጅ ሚድያ በዕለቱ በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ ታድሞ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች እንዳሉት እንዲህ ዓይነት መዝገበ ቃላት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይልና ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ መንግሥትም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ቢቀጥልበት ተገቢ ነው ብለዋል።
በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ ታላላቅ ምሁራን ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ዶክተር ሽመልስ ማዘንጊያ፣ ዶክተር ታዬ አሰፋ፣ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ተገኝተዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት ተመረቀ
Source(ተወዳጅ ሚድያ)

