የስኳር ህመም ምንድን ነው?

ህዳር 04 – ዓለም አቀፍ የስኳር ቀን ነው!
ዛሬ አለም አቀፍ የስኳር ቀን ነው፡፡ እለቱን ምክንያት በማድረግም ጥቂት ስለ ስኳር ህመም መረጃዎችን ልናካፍላችሁ ወደናል፡፡
የስኳር ህመም ምንድን ነው?
የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ኢንሱሊን የተባለውን ንጥር ነገር በበቂ ሁኔታ ማምረት ሲያቅተው ወይንም የተመረተው ኢንሱሊን ስራዉን በአግባቡ መስራት ሳይችል ሲቀር ነው፡፡
የስኳር ህመም አይነቶች
1. አይነት አንድ የስኳር ህመም፡- ቆሽት ውስጥ የሚገኙ ህዋሶች ኢንሱሊን የተባለውን ንጥረ ነገር ማምረት ሳይችሉ ሲቀሩ የሚከሰት ሲሆን፣ በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ህመም ነው፡፡
2. አይነት ሁለት የስኳር ህመም፡- በቆሽት ውስጥ የሚመረተው ኢንሱሊን በቂ ሳይሆን ሲቀር ወይንም በአግባቡ የማይሰራ ሲሆን የሚከሰት የስኳር ህመም ነው፡፡ በአብዛኛው ከ30 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎችን ያጠቃል፡፡
3. በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም፡- በነፍሰጡር እናቶች ላይ የሚከሰት የስኳር ህመም አይነት ሲሆን፣ በአብዛኛው ከወሊድ በኋላ ወደ ትክክለኛው የስኳር መጠን ይመለሳል፡፡
4. ሌሎች የስኳር ህመም አይነቶች፡- ምክንያታቸው ሳይታወቅ የሚከሰቱ የስኳር ህመም አይነቶች እና ሌሎች ህመሞችን ተከትለው የሚመጡ ለምሳሌ የኤች አይ ቪ ህመምን እና የቆሽት ህመምን ተከትለው የሚመጡ ናቸው፡፡
ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም ተጋላጭ የሆኑ እነማን ናቸው?
ማናቸውም እድሜያቸው 45 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም የመጋለጥ አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፡-
• ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት መጨመር
• ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል፣ በተለይም ጣፋጭ ምግቦች አዘውትሮ መመገብ
• አካላዊ እንቅስቃሴ በተገቢው አለማድረግ
• ሲጋራ ማጨስ
• አልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መውሰድ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣
• በዘር ወይንም በቤተሰብ ሊወረስም ይችላል፡፡
የአይነት ሁለት የስኳር ህመም ዋና ዋና ምልክቶች
አይነት ሁለት የስኳር ህመም በአብዛኛው ምልክት የማያሳይ ሲሆን አልፎ አልፎም በጥቂት የአይነት ሁለት የስኳር ታማሚዎች ላይ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡
• ቶሎ ቶሎ ውሃ መጠጣት
• ውሃ ሽንት ወዲያው ወዲያው መምጣት
• ቶሎ ቶሎ የረሀብ ስሜት መሰማት
• ያልተጠበቀ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት መቀነስ
• የድካም ስሜት መጨመር ናቸው፡፡
አይነት ሁለት የስኳር ህመም የሚስከትላቸው የረጅም ጊዜ ጉዳቶች
አይነት ሁለት የስኳር ህመም ቀስ በቀስ ስር እየሰደደ የሚሄድ በመሆኑ በአብዛኛው የረጅም ጊዜ ጉዳቶቹ መገለጫዎቹ ይሆናሉ፡፡ እነሱም፡-
 የኩላሊት ህመም
 የልብ ህመም
 የነርቭ በሽታ
 የዓይን ስውርነት ብሎም
 ያልተጠበቀ ድንገተኛ ሞት ናቸው፡፡
አይነት ሁለት የስኳር ህመምን እንዴት መከላከል ይቻላል?
እድሜቸው 45 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ቢያንስ በአመት አንድ ጊዜ የስኳር ህመም ቅድመ ምርመራ በማድረግ ወይም የስኳር መጠናቸውን በመለካት የስኳር ህመምን መከላከል ይቻላል፡፡ በተጨማሪም፡-
 የሰውነት ክብደት መጠንን መቆጣጠር
 ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል፣ በተለይም ጣፋጭ ምግቦችን አዘውትሮ አለመመገብ
 አካላዊ እንቅስቃሴ በተገቢው ማድረግ
 ሲጋራ አለማጨስ
 አልኮል መጠጥ ከልክ በላይ አለመውሰድ፣ ዋነኞቹ የስኳር ህመም መከላከያ መንገዶች ናቸው፡፡
የስኳር መጠኖን በመለካት፣ የስኳር ህመም እንዳለብዎት ወይም እንደሌለብዎት በጊዜ ይወቁ!
(አአዩ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe