የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝደንት በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ጉዳይ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር በካርቱም ተወያዩ

ኦሉሴጉን አቦሳንጆ “የአፍሪካ ችግሮች እንደማንኛውም ችግር በውጭ አካል ሊፈቱ አይችሉም” ሲሉ ገልጸዋል

የቀድሞው ፕሬዝደንት አቦሳንጆ “አፍሪካ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉትን ልዩነቶች ዝም ብላ አታይም” ብለዋል

በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው የድንበር ውዝግብ በካርቱም ውይይት በመካሄድ ላይ መሆኑን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ ባለው የድንበር ቀውስ ዙሪያ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ኃላፊዎች እና ከሱዳን ሚኒስትሮች ጋር በካርቱም ተወያይተዋል ፡፡

ኦባሳንጆ ከሉዓላዊው ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዱክ ጋር በሁለት የተለያዩ መድረኮች ተገናኝተው መክረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ፣ ሃምዶክ ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የሰብአዊ ውይይት ማዕከል (በግጭት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለማግባባት የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት) ልዑካን ጋር መወያየታቸውን አስታውቋል፡፡

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት በውይይቱ ላይ “አፍሪካ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት” አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡ አክለውም “አፍሪካ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉትን ልዩነቶች ዝም ብላ አታይም” ብለዋል፡፡

በሉዓላዊ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር በአል-ቡርሀን እና ኦባሳንጆ መካከል የተደረገውን ውይይት በተመለከተ የወጣው መግለጫ ደግሞ “ስብሰባውበአህጉሪቱ እየደረሱ ያሉትን ችግሮች ለማሸነፍ እና መፍትሔ ለማምጣት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ምክክር ለማድረግ ያለመ ነው” ብሏል፡፡

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በዚህ ስብሰባ ላይ “የአፍሪካ ችግሮች እንደማንኛውም ችግር በውጭ አካል ሊፈቱ አይችሉም ፤ ወይም ለአህጉሪቱ ላይጠቅሙ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም እኛ እንደመሪዎች በአፍሪካዊ ሁኔታ ለጉዳዮቻችን መፍትሄ መፈለግ አለብን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሁለቱም መግለጫዎች የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ካርቱም የገቡበትን ቀን እና አብረዋቸው የመጡ ልዑካን አባላትን አልጠቀሱም፡፡

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ “ሱዳን ለዓመታት በኢትዮጵያ ተይዞብኝ ነበር” የምትለውን የ “አል-ፋሻቃ” የድንበር አካባቢ (የምስራቅ) መሬቶችን ሙሉ በሙሉ በጦሯ ማስመለሷን መግለጿ የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ሱዳን በትግራይ የተፈጠረውን ግጭት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወረራ እንደፈጸመችባት በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡

ከድንበር ውዝግብ በተጨማሪ ፣ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሌላ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe