ፈረንሣይን እኤአ ከ2007 እስከ 2012 የመሩት ኒኮላስ ሳርኮዚ ለምርጫ ቅስቀሳቸው ከሟቹ የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል ተከሰው ባለፈው ሳምንት የአምስት ዓመት እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡ ሳርኮዚ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት የተከራከሩ ቢሆንም የፍርዱን ውሳኔ ማስለወጥ ባለመቻላቸው በዛሬው ዕለት ወደ እስር ቤት በመግባት የመጀመሪያው የፈረንሳይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ለአምስት ዓመታ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሳርኮዚ ለቪአይፒ ሰዎች ወደ ተገነባው የላ ሳንቴ እስር ቤት የእስር ጊዜያቸውን ለመጀመር ፓሪስ 16ኛ ጎዳና ከሚገኘው ቪላ መኖሪያ ቤታቸው ሲወጡ በበራቸው ላይ 100 የሚሆኑ ደጋፊዎቻቸው ተገኝተው እስራቸውን ተቃውመዋል፡፡
በጣም አወዛጋቢ በሆነው የሊቢያ የገንዘብ ቅሌት ጉዳይ ሳርኮዚ ንፁህነታቸውን በመግለፅ ክሱን በመቃወም የተከራከሩ ሲሆን የፍርዱ ዕለት በ X ገፃቸው ላይ “አልጠራጠርም። እውነት ያሸንፋል። ” የሚል መልዕክት አስፍረው ነበር።
የ70 አመቱ ኒኮላስ ሳርኮዚ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ወደተገነባው በሞንትፓርናሴ ወረዳ እስር ቤት በር ላይ ሲደርሱ በደርዘን በሚቆጠሩ የፖሊስ መኮንኖች ታጅበው ሲገቡ ታይተዋል፡፡ ሳርኮዚ የታሰሩበት ክፍል አንደኛ ፎቅ ላይ የሚገኝ ገለልተኛ ህንፃ ሲሆን የክፍሉ ስፋት ከ9-11 ካሬ ሜትር ይሆናል ተብሏል፡፡ክፍሉ መጸዳጃ ቤት፣ ሻወር፣ ጠረጴዛ፣ የኤሌትሪክ ምግብ ማሞቂያ፤ ፍሪጅና ትንሽ ቲቪ ያለው ሲሆን ሳርኮዚ ለዚህም በወር 14 ዩሮ (£12) ክፍያ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሳርኮዚ የቤተሰብ ጉብኝት የተፈቀደላቸው ሲሆን በጽሑፍ እና በስልክ የመገናኘትና መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ነገር ግን በቀን አንድ ሰዓት ብቻ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚፈቀደው የእስር ቤቱ መመሪያ በስፖርት ሰዓት ከማንም ጋር መገናኛትና ማውራት እንደማይችሉ ይከለክላል፡፡ ይህ የእስር ቤቱ መመሪያ የወጣው በእሳቸው የስልጣን ዘመን እንደሆነ ይነገራል፡፡

