ጥንዶች የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ሰርተፊኬት ሳይዙ ህጋዊ ጋብቻ መፈፀም ክልክል ሊሆን ነው
አሰራሩ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር በመመካከር ሥራ ላይ የሚውል ነው
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የፍቺ ቁጥር ለመቀነስ ፣ የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ሰርተፊኬት ሳይዝ ማንም ሰው ወደ ጋብቻ እንዳይገባ የሚያደርግ አሰራር ሊጀምር መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
አሰራሩ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር በመመካከር ሥራ ላይ የሚውል ነው መባሉን ሸገር ኤፍ ኤም ዘግቧል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሮበሌ አሰራሩን በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት አድርገናል ሲሉ ለጣቢያው ተናግረዋል።
አክለውም ለተጋቢዎች የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ በቤተሰብ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሥራቸውን ውጤታማ ለማድረግ የጋራ ፎረም መመስረታቸውን ጠቁመዋል።
ለብዙ ትዳሮች መፍረስ ዋነኛው ምክንያት ስለ ትዳር ያለው የግንዛቤ ዕጥረት ነው ያሉን አቶ ተስፋዬ ሮበሌ፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት የስልጠና ማኗሎችን መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
ለሀገር ለውጥ ከቤተሰብ መጀመር አለብን ያሉት ኃላፊው በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ ቤተሰቦች እንዳሉም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት የትዳር ፍቺ ካለፉት አመታት አንፃር 54 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ሲል መግለፁን ዘገባው አስታውሷል።
የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ሰርተፊኬት ሳይዝ ማንም ሰው ወደ ጋብቻ እንዳይገባ የሚያደርግ አሰራር ሊጀመር ነው

