የበሬ እርድ – ‹ለባንክ ዘራፊያን?›

ህግ ወጥነት ኢትዮጵያን ወዴት እየወሰዳት ነው?

‹ሚስጥራዊው› የመንግስትና የኦነግ ስምምነት ኢትዮጵያን ወዴት እየወሰዳት ነው?

‹‹የሰው ደም ካላፈሰሳችሁ እሺ የማትሉ ከሆነ በእናንተ ጠብ ንፁሃን በየቀኑ ከሚሞቱ እኔን ሽማግሌውን እረዱኝና ታረቁ››

አንድ የኦሮሞ አባት የተናገሩት

መነሻ አንድ – አዲስ መንገድ

ሰሞኑን በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ 18 ያህል የመንግስትና የግል ባንኮች ስለመዘረፋቸው ተሰምቷል፡፡ የኦሮሚያ መንገስትም ይህንኑ

አምኗል፡፡ ከዘረፋው በስተጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን ድረስ ሃላፊነት ያለበት መንግስት ማረጋገጫ አይስጥ እንጂ በመንግስትና በኦነግ መሀከል መወነጃጀል ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ግን ለምን?

ይህንን ተከትሎም በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኦነግና ኤዴፖ በኦሮሞ አባገዳዎች አማካይነት የእርቅ ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸው በተገለፀበት መድረክ ላይ ‹በሬ አርደንም ቢሆን እርቁ ይፈፀማል› ተብሏል፡፡ በህገ ወጥ እንቅስቃሴው የሰዎች ህይወት ያጠፉና ባንኮችን የዘረፉ አካላት ተገቢው ቅጣት ባልረተሰጠበት ሁኔታ በሬ አርዶ መስማማት የኦዴፖን ለህግ የበላይነት መቆም ጥያቄ ምልት ውስጥ የሚከት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደስልጣን መውጣት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፈጠራቸው አዲስ መንገዶች መካከል አንዱ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ወደ ሰላማዊው የትግል መስመር እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ በቅድሚያም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዓመታት አሸባሪ ብሎ የፈረጃቸውን ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከዚህ ስያሜ ነጻ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹም ርምጃው አዎንታዊና አበረታች መሆኑን የተናገሩት ወዲው ነበር። የአሸባሪነት ስያሜው ከተነሳላቸው ድርጅቶች መካከል የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ)፤ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እንዲሁም አርበኞች ግንቦት ሰባት ይገኙበታል፡፡

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በወቅቱ «መነሳቱን በበጎ ዓይን ነው የምናየው። ሆኖም በዚህ ግንባር ላይ ይኽ አዋጅ ብቻ አይደለም የታወጀው፤ በ1992 ከቻርተሩ ተገፍተን ስንወጣ በጊዜው የኢፒአርዲኤፍ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ጦርነት ነው ያወጁብን፤ ይኼ ጦርነት እስካሁን አልተነሳም በእኛ ላይ ይሄ እንዲነሳ ሦስተኛ አካል ባለበት ቦታ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ለዚህ መደምደሚያ እንድናደርግ አሁን መንግስት ላይ ላሉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥሪ አድርገናል፤ እየጠበቅን ነው» ብለው ነበር፡፡

መንግሥት ፍረጃውን ለማንሳት በምክንያትነት ከጠቀሳቸው አንዱ ድርጅቶቹ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ በመሆናቸው ነው። የመንግስት ውሳኔ በሀገሪቱ ቀጣይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚኖረው ሚና ምን እንደሚመስል በጊዜው የተጠየቁት የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ «ወደትጥቅ ትግል ተገፍተን ነው የገባነው፤ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት አባል ነበርን፤ አብረን ነው የሽግግር መንግሥቱን ያቋቋምነው፤ ከዚህ ነው ገፍተው ወደ ትጥቅ ትግል ያስገቡን በግዴታ። የትጥቅ ትግሉ የመከላከል ጦርነት ነው እስካሁን ድረስ እየተደረገ ያለው። ሌላው ደግሞ ትጥቅ ይዞ እንደ መንግሥት ሽብር ሲያፋፍም የነበረው ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ነው። እግዜር ይስጣቸው ጠ/ሚኒስሩም ይህንን ተናግረዋል። እና አሁን መደምደሚያ እናድርግ እና ከፖለቲካ ሜዳ ኃይል መጠቀምን ለማውጣት ስምምነት ይጠይቃል» ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባትን በ2003 ዓ.ም ነበር ሽብርተኛ ሲል የፈረጃቸው። ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ድርጅቶቹን አሸባሪ ሲል የፈረጀው አዋጅ ሲታወጅ በኦሮሞ ሕዝብ እና በድርጅቱ ላይ አሳዛኝ ነገር መድረሱን፣ በዚህ አማካኝነትም በርካቶች የኦነግ አባል በመሆናቸው ብቻ ለእስራት፣ ለስቃይ እና እንግልት እንዲሁም ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አቶ ዳውድ ኢብሳ ተናግረው ነበር።

መነሻ ሁለት – ስምምነት

‹ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ተስማማ› የሚለውን ዜና የሰማነው ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ነው፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ የተመራው የልዑካን ቡድን ወደ አሥመራ ተጉዞ ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር መሪ ዳዉድ ኢብሳ ጋር ተገናኝቶ ውይይት አካሄዷል።

አራት ሰዓት በቆየው ውይይት ላይ ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በአገሪቱና በኦሮሚያ ክልል ጉዳዮች ላይ በሰላማዊ መንገድ ለመስራት እንደተስማማ በወቅቱ የኦነግ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ቶሌራ አዳባ ለዶይቼቬሌ ተናግረው ነበር። አቶ ቶሌራ፣ «ኦነግ ወደ አገር ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ እንዲሰራ ተስማምተናል። ከዚህ በኋላ በኦሮሞና በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በሰላማዊ መንገድ ተባብሮ ይሰራል። በስምምነቱ መሰረት፣  ኦነግ ካሁን በኋላ በሀገሪቱ በነፃ፣ ሳይፈራ መንቀሳቀስ ይችላል።»

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ኤርትራን በጎበኙበት ጊዜ  ከኦነግ ልዑካን ቡድን ጋር ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም ተገናኝተው መወያየታቸዉም ይታወሳል። ግንባሩም ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ማወጁም አይዘነጋም። «አንድ ሌላ የተስማማንበት ጉዳይ ደግሞ ከዚህ በኋላ በኦነግ ስም ምንም አይነት የጦር ርምጃ እንዳይወሰድ ነዉ። ከዛሬ በኋላ በመካከላችን ሲካሄድ የነበረዉ የኃይል ርምጃም በይፋ እንዲቆም ተስማምተናል። የኦነግ ሰራዊትን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ወደፊት በጥልቀት እንወያይበታለን።  አሁንም ግን የኦነግ ሰራዊት እንደ ኦነግ ሰራዊት ባለበት ይቆያል» ሲሉ አቶ ቶሌራ ተናግረው ነበር፡፡

ከመነሻው የጀመረ ውዝግብ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ልዑካን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በአስመራ ተገናኝተው መወያየታቸውና ኦነግ የተኩስ አቁም ለማድረግ መወሰኑ ከተሰማ በኋላ ቀናትን ሳይቆይ ኦነግ ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ ጎን የሰላም ድርድር እያለ በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የግንባሩ ጦር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉን የመከላክያ ሰራዊት እያሰማራ እንደሚገኝ በመግለጽ ሁኔታውን አውግዞ ነበር።
የኦነግ ሥራ አስፈፃሚ አባልና ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ በወቅቱ «የእርቅ ዉይይቱን ወደ ፊት ለመዉሰድ ግንባሩ ግዜያዊ ቱክስ አቁም አዉጀዋል። ግን ከአዋጁ ወዲህ የኦነግ ሠራዊት ከተለያዩ ርምጃዎች ራሱን ቆጥበዋል። ይህን እድል በመጠቀም የኢትዮጵያ መንግስት በሦስት አቅጣጫዎች፣ ማለትም በከጋምቤላ ወደ ደቢዶሎ፤ ከነቀምት ወደ ጊምቢና ማንድ አካባቢ እንዲሁም ከአሶሳ ወደ ቤጊ ትልቅ ሠራዊት በማሰማራት ስልታዊ የሆኑት ቦታዎችን መቆጣጠር ቀጥሎአል። የኦነግ ሠራዊት ይህን እንቅስቃሴ ያይ ነበር። ይሁን እንጅ ለእርቁ ሲባል ምንም ርምጃ አልወሰደም። ይህ ደግሞ ሕዝብም ሆነ ሠራዊቱን ያሳስበዋል» ብለው ነበር፡፡

ይህ የመንግስት ርምጃ ከሠላም ዉይይቱ ጋር የሚጻረር ስለሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ሠራዊት ወደ ቦታ ማሰማራት አስፈላጊ አልነበረም የሚሉት አቶ ቶሌራ ከዚህ በኋላ ለሚፈፀመዉ ነገር መንግስት ሃላፊነቱ የመንግስት መሆኑን ለማሳወቅ መግለጫ ማዉጣታቸዉንም አክለዉ ገልጸው ነበር።

“የእኛ ለውጥ ነው››

ከዚህ ውዝግብ በኋላ በአስመራ ከነአቶ ለማ መገርሳ ጋር ውይይትና ስምምነት አድርጎ ወደሀገር ለመግባት የወሰነው ኦነግ አዲስ አበባ ሲደረስ እጅግ ደማቅ ሚባል አቀባበል ነው የጠበቀው፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ “ሰላማዊ በሆነ መንገድ ግቡን እንዲመታ” ድርሻውን ለመወጣት ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ግንባሩ አስታውቆ ነበር፡፡ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የኦነግ ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በኢትዮጵያ ታይቷል ላሉት ለውጥ ኦነግ እና ሰራዊቱ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

“የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ቄሮ ቢልሱማ ኦሮሞ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ወጣቶች እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኸንን ለውጥ ለማምጣት ሙሉ በሙሉ ተሳትፈውበታል። በዚህ ለውጥ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አለን። የእኛ ለውጥ ነው ብለን ስላመንን ነው የመጣንው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ቡድኖች ይኸንን ለውጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲሔድ ወስነው ለዚህ በር ስለከፈቱ ከእነዚህ ጋር ሥምምነት አድርገን፣ ይኸ ለውጥ በጣም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ግቡን እንዲመታ፣ የእኛን ተሳትፎ ለማድረግ ነው ወስነን የመጣንው” ብለዋል የኦነግ ሊቀመንበር።

የኦነግን የአጭር ጊዜ እቅድ በተመለከተ ሊቀመንበሩ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ በኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አካሔድ ላይ ከድርጅቱ አባላት፤ ከወጣቶች እና ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል። በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በሁሉም መስክ ግቡን የሚመታበትን መንገድ ለመቀየስ ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚፈልግም አቶ ዳውድ አስታውቀዋል።

“በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለብዙ ዓመት ትግል የተደረገበት እና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። በዚህ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። ይኸ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እና ሕዝቡ በራሱ መሪዎቹን ከታች እስከ ላይ እንዲመርጥ እና የፖለቲካ ሥልጣኑን በእጁ እንዲያስገባ ዋንኛ ምኞታችን እና የታገልንበት ነው። በሩቅ ግባችን ከመንግሥት እና ከሌሎች ኃይሎች ጋር ይኸ ሥራ ላይ እንዲውል ምኞታችን እና እቅዳችን ነው” ሲሉ ሊቀመንበሩ አስረድተው ነበር።

አቶ ዳውድ በጋዜጣዊ መግለጫቸው የሕግ የበላይነትን በተመለከተ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ተሳትፎ ማድረግ አለበት ብለዋል። ከ42 አመታት በፊት የተመሠረተው ኦነግ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይመራ የነበረው ደርግ ሲወድቅ የሽግግር መንግሥት ከመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነበር። በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ አራት የምኒስትርነት ቦታዎች የነበረው ፓርቲው ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር ከገጠመው አለመግባባት በኋላ ለቆ የወጣ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት የመከፋፈል ዕጣ ገጥሞታል።

‹ስምምነት ተጣሰ›፣ የትኛው ስምምነት?

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ግንኙነት በተለይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ክፉኛ ሲሻክር ታይቷል። የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እርስ በርስ ሲወነጃጀሉም ሰንብተዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል በተባሉ የምዕራብ እና የምሥራቅ ወለጋ ዞኖች በተፈጠሩ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በአካባቢው ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ የትምህርት እና የጤና ማዕከላት የሚሰጡት ግልጋሎት ተስተጓጉሏል። ግጭት እና ኹከት በጠናባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች መሠረታዊ የጤና ግልጋሎት ለመስጠት መቸገሩን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ “የጤና ባለሙያዎች ሆስፒታሎች፣ በጤና ኬላዎች መሥራት እየቻሉ አይደለም። ስፔሻሊስቶቻችን ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎቻችን በዛ አካባቢ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ የመስራት ፍላጎት የላቸውም። እየተመለሱ ነው ያሉት። አዲስ መመደብም እየተቻለ አይደለም። በአምቡላንስ እጦት ቤታቸው እየወለዱ የሚሞቱ እናቶች ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል። በተለያየ ቦታ መድሐኒቶችን ለማድረስ ችግር ሆኗል። የማሕጸን በር ካንሰር የሚከላከል ክትባት እየተሰጠ ነበር። በእነዚህ ዞኖች ውስጥ መስጠት አስቸጋሪ ነው። የሕፃናት ክትባት መስጠት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከሳምንት በፊት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ በስድስት ዞኖች የሚገኙ 810 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን አስታውቆ ነበር። ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው ስድስት ዞኖች መካከል ምሥራቅ ወለጋ፤ ቄለም ወለጋ ሖሮ ጉዱሩ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሹማምንት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከዚህ ቀደም የተፈረመውን ስምምነት እያከበረ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ። የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ቃል-አቀባይ አቶ ታዬ ደንደዓ በአቶ ዳውድ ኢብሳ በሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር “ከ 30 በላይ አመራሮች ተገድለዋል” ሲሉ ወቅሰው ነበር። አቶ ታዬ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የፈረመውን ስምምነት ባለማክበሩ ምክንያት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የጸጥታ መናጋት መፈጠሩን ከሁለት ሳምንት በፊት ተናግረው ነበር።

ኦነግ በበኩሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ብሏል። ግንባሩ “ጽሕፈት ቤቶቹን ከፍቶ በኣግባቡ እንዳይንቀሳቀስና እንዳይሰራ ለማደናቀፍና ለመገደብ” ጫና እየተደረገበት እንደሆነም አስታውቋል። ኦነግ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት ተከፍቷል ሲል ወንጅሏል።

በርካቶች መንግሥት ከኦነግ ጋር አሥመራ ላይ የደረሰውን ዝርዝር ስምምነት ለህዝብ ይፋ አላደረገም በማለት መንግሥትን ይወቅሳሉ። የኦነግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳም በቅርቡ ለሃገር ቤት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በሁለቱ ወገን የተደረሰው ስምምነት ለህዝብ ግልጽ እንዳይሆን እያደረገ ያለው መንግሥት ነው ብለዋል።

የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የተደረሰው ስምምነት ሆን ተብሎ ዝርዝሩ ከህዝብ ተደብቋል የተባለው ከእውነት የራቀ ነው ያሉ ሲሆን፤ የስምምነቱ ተፈጻሚነትም በፈለጉት ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ኦነግ ከመንግሥት ጋር በተኩስ አቁም ስምምነት መከበር ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አስከባሪ እና ደህንነት አካል ገለልተኛ እንዲሆን ማድረግ፣ የኦነግ ሠራዊት ወደ መንግሥት ኃይል እንዲካተት ማድረግ ላይ የተስማማ ቢሆንም አለመከበራቸውን ግን ይናገራል።

ኦዲፒ በበኩሉ በተለያዩ የክልሉ ዞኖች ውስጥ እንደ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ እንደሆነ በመግለፅ፤ የኦነግ አመራር በጠቅላላው ሰላማዊ ትግልን እንደ አማራጭ አድርጎ መቀበሉ አጠራጥሮናል በማለት የወነጀለው ሲሆን የኦነግ አመራር እና በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የጦር አመራሮች የሚሰጡት መግለጫዎች የተለያዩ ናቸው ብሏል።

አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች እና በኤርትራ መሽገው የነበሩ ታጣቂዎች ባለፈው መስከረም ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም ሁለቱ ወገኖች የደረሱበት ስምምነት ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

ስርዓት አልበኝነት እስከ ባንክ ዝርፊያ

ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ማለትም ጥር 4 እና 5 ቀን 2011 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ባንኮች እንደተዘረፉና ንብረታቸው እንደወደመ እንዲሁም የወረዳ ጽህፈት ቤቶች በእሳት እንደጋዩ ታውቋል።

በሆሮ ጉዱሩ ዞን፤ ሆሮ ቡሉቂ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ሰባት መሥሪያ ቤቶችን የያዘ የወረዳ ጽህፈት ቤት መቃጠሉም ተነግሯል፡፡ የአካባቢው ባለስልጣናት እንደሚሉት የታጠቁ ኃይሎች የሆሮ ቡሉቂ ወረዳ ዋና ከተማ ወደሆነችው ሰቀላ ከተማ በመግባት መሥሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውንና አዋሽ ባንክን መዝረፋቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች የአዋሽ ባንክ ሥራ አስኪያጅን ቤቱ ድረስ ሄደው በማምጣት ባንኩን ያስከፈቱት ሲሆን ባንኩ ቢከፈትም የካዝናው ቁልፍ የባንኩ ሥራ አስኪያጅ እጅ ስላልነበረ ካዝናውን መክፈት ባለመቻላቸው ያገኙትን ገንዘብ ሰብስበው የባንኩን ሥራ አስኪያጅ አፍነው መሄዳቸው ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ከባንኩ ጥበቃዎች ሁለት ክላሺንኮቭ መዝረፋቸውም ተነግሯል።

በምዕራብ ኦሮሚያ እና በቄለም ወለጋ በሚገኙ አሥር የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ኅብረት ባንክ እና አዋሽ ባንክ ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው ባንኮች መካከል ይገኙበታል፡፡ የአካባቢው ባለስልጣናት እንደሚሉት ዘረፋዎቹ የተፈጸሙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሌለባቸው ስፍራዎች ነው።

በምዕራብ ኦሮሚያ ላለው የጸጥታ መደፍረስ ተጠያቂው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መሆኑን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የኦፕሬሽን ኃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ባለፈነው አርብ በሰጡት መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል። የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፤ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ በኦሮሚያ በተለያዩ ስፍራዎች ይዘርፋል፣ አዲስ የኦነግ ጦር ይመለምላል፣ የክልል የመንግሥት ተቋሞችን ሥራ ያስቆማል፣ እንዲሁም የአካባቢውን አመራሮችን ይገድላል ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።

አቶ ሚካኤል ቦረና የኦነግ ሸኔ የሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። አቶ ሚካኤል ‹‹ኦነግ ለበርካታ ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ሲታገል የቆየ ድርጅት ነው። ኦነግ በምንም አይነት ሁኔታ እንዲህ ያለ ተግባር አይፈጽምም›› ይላሉ።

አቶ ሚካኤል የተፈጸመው ተግባር ሆነ ተብሎ የኦነግን ስም ለማጥፍት ነው ያሉ ሲሆን፤ ”መንግሥት ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ በርካታ ጦሩን አሰማርቷል፤ በየአካባቢው እየተካሄደ ስላለው ነገር ሙሉ መረጃ ለማግኘት ቸግሮናል” ይላሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኦነግ የምዕራብ ዕዝ የጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ ወይም በቅጽል ስሙ መሮ፤ የክልሉ መንግሥት ኦነግ ላይ ያቀረበውን ወቀሳ በማስመልከት ለቢቢሲ ይህን ብሎ ነበር።

”. . . የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከደረስን በኋላ ኦነግ በራሱ ተነሳሽነት መንግሥት ላይ ተኩስ ከፍቶ አያውቅም፤ አጸፋዊ እርምጃ ካልወሰድን በቀር። ይህ ሁሉ ክስ ግን ሃሰተኛ ነው። መንግሥት ይህን ክስ የሚያቀርበው በዚህ አካባቢ ላይ ጦሩን በማዝመት ጦርነት ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት ሲያከናውን ነው እንጂ ኦነግ ያፈረሰው የመንግሥት ሥርዓት የለም፤ የዘረፈውም የጦር መሳሪያ የለም”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe