” የቡድን እና የነፍስወከፍ መሳሪዎችን የማስፈታቱ ሂደት ዘግይቷል ” – የብሔራዊ መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን

የፕቶሪያውን የህወሓትና የፌደራል መንግስትን ስምምነት ተከትሎ ህወሓት ታጥቋቸው የነበሩ ከባድ መሳሪያዎችን የማስፈታት ሥራው በተሳካ ሁኔታ ቢፈፀምም፣ የቡድንና የነፍስወከፍ መሳሪዎችን የማስፈታቱ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን የብሔራዊ መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው።

የተሀድሶ ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፤ አገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ ማለፏን ጠቅሰው ጦርነቱ ያስከተለውን ጥፋት በማየትና ካለፍንባቸው ችግሮች መማርና ወደ ሰላም መምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው፤ የፕሪቶያውን ስምምነት ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ትጥቅ መፍታታቸውን ጠቁመዋል።

የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ግን በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ማስፈታት ሳይቻል መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ለመዘግየቱ ዋነኞቹ ምክንቶች ፦ ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ስራ ስለነበረበት፣ በትግራይ ክልል የሽግግር መንግስት ሳይቋቋም በመቆየቱና ሌሎች አንዳንድ መሰናክሎች እንደነበሩ ነው ያስረዱት፡፡

አሁን ግን ሁኔታዎች እየተስተካከሉ በመሆኑ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ተግባራት ይፈፀማሉ ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ዶ/ር ጌታቸው ጀንበርን ጨምሮ ሌሎች የሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት ተገኝተው እንደነበር ዶቼ ቨለ ሬድዮ ዘግቧል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe