የቤት ኪራይ መክፈል ያልቻሉ ሠራተኞች ተደብቀው ቢሮ ውስጥ እንደሚያድሩ ተሰማ

ኑሮ የከበዳቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓትን በቤተ እምነቶች እያሳለፉ መሆኑ ተነገረ

መንግሥት የሚከፍላቸው ወርኃዊ ደመወዝ አልበቃ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓታቸውን ወደ ቤት እምነቶች በመሄድ፣ እንዲሁም ቤት ተከራይተው መኖር የማይችሉት ደግሞ ቢሮ ውስጥ ተደብቀው እንደሚያድሩ ተገለጸ፡፡

በ2010 ዓም ተሻሽሎ ወደ ሥራ ገበቶ የነበረው ባለ 106 አንቀጽ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ፣ ከስድስት ዓመታት አገልግሎት በኋላ፣ በ160 አንቀጾች ተዋቅሮ በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡

ለመንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች የበዛ ሥልጣን የሚሰጥ፣ ለሠራተኞች ችግር ደግሞ መፍትሔ የማያመጣና ተቋማዊ አሠራርና አደረጃጀት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው የሚል ትችት በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀርቧል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛውን ሕይወት የሚቀይር ሥራ እንጂ አዋጅ ማውጣት ብቻ አገርን አይቀይርም የሚሉ ድምፆችም ተሰምተዋል፡፡

ለመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛና ሊያኖር የማይችል ከመሆኑም በላይ፣ በበርካታ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ደመወዝ መክፈል ተስኗቸው ሠራተኞች ለወራት ደመወዝ ሳይከፈላቸው መቆየታቸውን፣ እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ከሚቀጥሉት ዓመታት በጀት ተበድረው ደመወዝ እየከፈሉ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ደግፌ በሰጡት አስተያየት፣ በከተማ አስተዳደሩ 70 ያህል የመንግሥት ተቋማት ላይ ክትትል እንደሚያደርጉና ሥልጠና እንደሚሰጡ ጠቅሰው የሠራተኛው ሕይወት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በከተማ አስተዳድሩ አንድ ከፍተኛ የሚባል ባለሙያ ያልተጣራ ደመወዙ 9,056 ብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ከዚህ ግብር ተከፍሎበት በእጁ የሚደርሰውን ገንዘብ አስልታችሁ ድረሱበት፤›› ሲሉ ተሳታፊዎችን ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ደመወዝ የቤት ኪራይ የከተማዋ ጫፍ እንኳ ቢኬድ 10,000 ብር መድረሱን፣ ነገር ግን ይህ ከፍተኛ ባለሙያ ሙሉ ደመወዙን ለቤት ኪራይ ላድርግ ቢል ገንዘቡ እንደማይበቃው አስረድተዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ ያለ አንድ ሠራተኛ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይቻላል ወይ?  ተፈጥሯዊ ሁኔታውስ በራሱ ይፈቅድለታል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ችግር ደመወዝ በመጨመርም ይፈታል ብለው እንደማያስቡ ገልጸው፣ በሌሎች አማራጮች እንዲጠቀም ቢደረግ ችግሩ ሊቀል ይችላል እንጂ 2,000 ብር ቢጨመር እንኳን ሕይወቱ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህም የተነሳ ሠራተኞች አንዳንዴ ቢሮ መጥተው ያለቅሱብናል፣ ምሳ  የምንበላበት የለም በማለት በግልጽ ይናገራሉ፤›› ብለዋል፡፡

ገንዘብ አልበቃቸው ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች በምሳ ሰዓት ወደ ቤተ እምነቶች ሄደው እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ታማኝ ግብር ከፋይ ቢሆንም፣ ነገር ግን የሠራተኛውን ሕይወት የሚቀይር ነገር እስካልመጣ ድረስ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት ሊሰጥ እንደማይችል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ይልማ፣ ‹‹የረቂቅ አዋጁን መዘጋጀት የሰማ የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪ አለ የሚል አዝማሚያ እየሰማን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው የረቂቅ አዋጁን ዝርዝር የማየትና የመስማት ፍላጎት እንደሌለው ጠቅሰው፣ ‹‹አዋጁ ቶሎ ተዘጋጅቶ ሠራተኛው የሚጠቀምበት አሠራር ካልተዘረጋ በቀጣይ ከሠራተኛው ጋር የምንጋፈጠው እኛው ነን፤›› ብለዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ተስፋ መቁረጡንና ችግር ውስጥ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰሎሞን፣ ‹‹አሁን ስለአዋጁ ወይም ዝርዝር እንድናወራለት ፍላጎት የለውም?›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ውስጥ የሚሠሩና ደንብ የሚቆጣጠሩ ከ6,500 በላይ ኦፊሰሮች በወር 3,934 ብር እየተከፈላቸው ለአሥር ዓመታት በተመሳሳይ ደመወዝ እያገለገሉ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በዚህ የተነሳ መሄጃ እያጡ ቢሮ ምቹ ሁኔታ አለ በሚል እየተደበቁ የሚያድሩ አሉ ብለዋል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኞች መነሻና መድረሻ ደመወዝ ሊስተካከል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
(ሪፖርተር)

Sourcereporter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe