የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እና የአምባሳደር ዲና ሙፍቲ ምላሽ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፥መንግሥት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይቻል ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች መልዕክት መተላለፉን አስታውቀዋል።

በቂ ግንዛቤ ካለመፈጠሩ የተነሳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ስላለው ጉዳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል ብለዋል።

በስብሰባው በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያሰቡ አገራት ጉዳያቸው እንደማያስኬድና እውነታውን በቅጡ እንዲረዱት የሚያስችል ገለፃ በአምባሳደሮቻቸው በኩል እንደተደረገላቸው ገልፀዋል።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ተወካይ አገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮቻቸው ጋር በተለይ ትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ማብራሪያ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

በማብራሪያው መንግሥት በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች እያደረገ ስላለው ድጋፍ እና በዛ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ያተኮረ መሆኑን ያስታወቁት አምባሳደር ዲና፣ ጉዳዩን በመረጃ በተደገፈ መልኩ እንዲረዱት ለማድረግ ተሞክሯል ብለዋል።

ሁኔታውን በሚገባ ካለማወቅም ይሁን በማወቅ በፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በአጀንዳነት እንዲያዝ የሚጥሩ አገራት የኢትዮጵያ መንግሥትን እርምጃዎች በአግባቡ እንዲገነዘቡት የሚያስችል ሰፊ ማብራሪያ መሰጠቱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት 40 ቢሊዮን ብር በመመደብ 70 በመቶ የሚሆነውን የትግራይ ክልል ሰብአዊ ዕርዳታ እያቀረበ መሆኑን ለአምባሳደሮቹና ተወካዮቻቸው ተብራርቷል፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአካባቢው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በፈቀደበት ሰዓት የኢትዮጵያ ጉዳይ በፀጥታው ምክር ቤት በአጀንዳነት እንዲያዝ ጥረት መደረጉ ስህተት መሆኑ ተነግሯቸዋል።

ከዚህ ይልቅ 30 በመቶ ብቻ ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ተቋማት ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ጥሪ መደረጉን ገልፀዋል።

እንደ አምባሳደር ዲና ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆኖ እንዲነሳ የሚገፉ አገራት በኢትዮጵያ የሚከሰት ችግር በቅድሚያ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚመለከት መሆኑን እንዲገነዘቡ ተደርጓል።

ከፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት መካከል 10ሩ ተለዋጭ አባላት ሲሆኑ አምስቱ ቋሚ አባላት ናቸው ያሉት አምባሳደሩ፣የየአገራቱ ተወካዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላቸውን ጥያቄ እና አስተያያት እንዲሰነዝሩ ዕድል ተሰጥቷል።

በኢትዮጵያ በኩል ከተሰጠው ገለፃ እና ከግንዛቤ ማስፋት ሥራው በኋላ የፀጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራትም ኢትዮጵያን የሚደግፍ አቋም እንደሚኖራቸው እምነት መኖሩን ገልፀዋል።

<<በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማያስፈልግ መናገራቸው የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ያደረጉት ሥራ ነው>> ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ሌሎቹ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራትም የሦስቱን አገራት ተሞክሮ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe