የተናቀው ኮሮና ቫይረስና አስደንጋጭ ውጤቱ

በአሜሪካ በሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የወረርሽኝ በሽታዎች አጥኚ የሆኑት ኢያን ሊፕኪን ከባለቤታቸውና ከሳይንቲስቱ ወዳጃቸው ጋር የእራት ግብዣ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ በቻይና ከሚገኝ ጥብቅ የመረጃ ምንጫቸው አንድ ምሥጢራዊ የስልክ መልእክት ይደርሳቸዋል፡፡ በዉሐን ከተማ በኖቭል ኮሮናቫይረስ አማካኝነት የተከሰቱ የሳንባ ምች መሰል ሕመሞች መታየት ጀምረዋል የሚል ነበር መልእክቱ፡፡ የመረጃ ምንጫቸው በሽታው ተላላፊ ስለማይመስል ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነ ጨምሮ ነግሯቸዋል፡፡ ሊፕኪን ሁኔታውን ሲያስታውሱ ‹‹ስለ በሽታው መጨነቅ እንደሌለብኝ ነበር የተነገረኝ›› ይላሉ፡፡

በኋለኛው ሥሙ ‹SARS-Cov-2› ተብሎ የተጠራው ያ ቫይረስ ነው እንግዲህ በዓለማቀፍ ደረጃ ከሦስት ሚሊየን በላይ ሰዎችን ለሞት በመዳረግና ዓለማቀፍ የጤና ሥርዓቱን በማናጋት ዛሬም ድረስ ለያዥ – ለገራዥ አስቸጋሪ የሆነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1918 ከገጠማት የኢንፍሎዌንዛ ወረርሽኝ ወዲህ ዓለም እንዲህ ያለ የበሽታ ክፉ ተመልክታ አታውቅም፡፡

የተሳሳቱ ድምዳሜዎች

ለመሆኑ በሽታው በዚህ መጠን ዓለምን ማስጨነቅ የቻለበት ምክንያት ምን ይሆን? የቫይረሱ ጠባይ ይሆን? በንክኪ መተላለፉ ይሆን? ሰዎች መታመማቸውን ከማወቃቸው በፊት ወደ ሌሎች መተላለፍ መቻሉ ይሆን? ሰዎች በሽታውን ለመቋቋም የሚያስችል ተፈጥሯዊ የመከላከል አቅም ስለሌላቸው ይሆን? በበርካታ ሀገራት የታየው በሽታውን ለመከላከል የመዘግየት እንዲሁም በሳይንስ ያልተደገፈና በድንጋጤ የታጀበ መልስ አሰጣጥስ ቫይረሱ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ የነበረው ሚና ምን ያህል ነው?

<የጀርመን የቴክኖሎጂ ኩባንያ በዐይን የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ይፋ አደረገ>

በርካታ የዓለም ሀገራት ለበሽታው በቂ ትኩረት ሰጥተው ለመከላከል ያደረጉት ጥረት እጅግ አነስተኛ ቢሆንም ምሥጢራዊ አመጣጡ ቀድሞ የገባቸው ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ከእነኚህ መካከል አንዷ ደግሞ በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች አጥኚ የሆኑት ማሪያ ቫን ኬርሆቭ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 ዓመት የመጨረሻ ቀናት የደረሳቸው የኢሜይል መልእክት በቻይናዋ ዉሐን ከተማ 44 ሰዎች በሳንባምች በሽታ ተይዘው ሆስፒታል መግባታቸውን የሚጠቁም ነበር፡፡ ይህ መረጃ ከደረሳቸው ከአራት ቀናት በኋላ ከቻይና የወጡት ዘገባዎች የኮሮናቫይረስን መከሰት ይፋ አደረጉ፡፡

በሽታው እ.ኤ.አ በቻይና ተከስቶ ከነበረውና በዓለማቀፍ ደረጃ ለስምንት መቶ ሰዎች ሞት ምክንያት ከሆነው ሳርስ (SARS) የተባለ በሽታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ታወቀ፡፡ በሳርስ በሽታ ላይ የሚሠሩትና ስታንሌይ ፐርልማን የተባሉት የአዮዋ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ በሽታው እንደ SARS-1 ዓይነት ገዳይ እና የመተላለፍ አቅሙ ውሱን ነው የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ በአንድ የጥናት መጽሔት ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍም አዲሱ በሽታ የመተላለፍ አቅም የሚኖረው በታማሚው ሳንባ ላይ ከፍተኛ ችግር ካስከተለ በኋላ መሆኑንም ገልጸው ነበር፡፡ ፐርልማን ዛሬ ላይ ሆነው ያንን ድርጊት ሲያስታውሱ ‹‹ተሳስቼ ነበር›› በማለት ይናገራሉ፡፡ የሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲው የተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪው ማይክል ኦስቴርሆልምም እርሳቸው በሚያውቋቸው እንደ SARS እና MERS ያሉ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ ተላላፊ በሽታዎች የተያዙ ሰዎች ምልክቱ መታየት እስከሚጀምርባቸው አምስትና ስድስት ቀናት ድረስ በሽታውን ወደሌሎች አያስተላልፉም፡፡ ኮሮናቫይረስም እንዲህ መስሏቸው ከተሸወዱት ታላላቅ የሕክምና ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡

ላለፉት 40 ዓመታት የኮሮናቫይረሶችን ጸባይ ሲያጠኑ የኖሩት የፒንሲልቬኒያ ዩኒቨርሲቲዋ ምሑር ሱዛን ዌይስ በዚህ ሁሉ ዓመት ልምዳቸውም ቢሆን ኮቪድ – 19 በዚህ መጠን ሊስፋፋ እንደሚችል መገመት አልቻሉም ነበር፡፡ ‹‹ዓለምን እንዲህ ያጥለቀልቃል ብዬ አላሰብኩም፡፡ እንደ ሳርስ በሽታ በቁጥጥር ስር ይውላል የሚል ገራገር ሐሳብ ነበረኝ›› በማለት ይናገራሉ፡፡

ከግምት በላይ የሆነው ኮቪድ – 19

ከእነኚህ ሁሉ የዩኒቨርስቲ ምሑራን የተሳሳቱ ድምዳሜዎች በኋላ በኮቪድ – 19 ሕይወታቸው ያለፈው የመጀመሪያው ሰው በቻይናዋ ዉሐን ከተማ ተገኙ፡፡ የ61 ዓመቱ ሰው በከባድ የጉበት በሽታ ተጠቅተው የነበረ ሲሆን ሰውየው በከተማዋ የሚገኝ የባሕር ምግቦች የሚሸጡበት የሸቀጣሸቀጥ መደብር ደንበኛ የነበሩ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ከቀናት ልዩነት በኋላ ደግሞ የቫይረሱ ተጠቂ ከቻይና ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በታይላንድ መገኘቱ ተነገረ፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ልዑካን ወደ ጣሊያን ተጉዘው ባደረጉት ጥናት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ መሆኑን ማረጋገጥ ቻሉ፡፡ እ.ኤ.አ ጥር 22 ቀን 2020 የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አድሃኖም ጉዳዩ በዓለማቀፍ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን ለማወጅ ውሳኔ የሚሰጥ አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላም የቻይና በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ማዕከል በበሽታው የተጠቁት ዜጎች ቁጥር 830 መድረሱንና 25 ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉን ይፋ አደረገ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይ፣ ማሌዥያ፣ ኔፓል፣ ቪየትንሐም፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ በበሽታው ማዕበል መመታት የጀመሩ ሀገራት ሆኑ፡፡

<በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሳቢያ የሚመጡ ግጭቶችን ለመቀነስ ፖለቲከኞች ከስሜታዊነት የፀዱና የተገሩ…>

በዚህ ወቅት ከቻይና ውጪ ሞት የተመዘገበባቸው ሀገራት ባይኖሩም በ18 የዓለም ሀገራት የታዩት 82 የበሽታው ሕሙማን የዓለም ጤና ድርጅት በሽታው ዓለማቀፍ ስጋት መሆኑን ያውጅ ዘንድ ግድ አሉት፡፡ እንደ ሳርስ ባሉ የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች በተለያዩ ጊዜያት የተሰቃዩት ቻይናውያን የኮቪድ – 19ኝን አሳሳቢነት ተረድተው በአሥር ቀናት ውስጥ የተጠናቀቀና አንድ ሺህ ሕሙማንን ማስተናገድ የሚችል ሆስፒታል ገነቡ፡፡ የጥንቃቄውንም መጠን በከፍተኛ ደረጃ አከናውነው በሽታውን በቁጥጥር ስር ማዋል ቻሉ፡፡

የበሽታውን ጸባይ ለማጥናት በተደረጉት ጥረቶች የተለያዩ መላምቶች መሰማት ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ በሽታው ከሌሊት ወፍ ሳይመጣ እንዳልቀረ ሲጠቁሙ ሌሎቹ ደግሞ አየር – ወለድ ሊሆን እንደሚችል ተናገሩ፡፡ እንዲህ ያሉ መላምቶች በሳይንስ እስከሚረጋገጡ ድረስ ቫይረሱ ካለ ከልካይ እጅግ በከፍተኛ ፍጥነት መዛመቱን ቀጠለ፡፡

እ.ኤ.አ በመጋቢት 25 ቀን 2020 በዩናይትድ ስቴትስ በበሽታው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ከአንድ ሺህ አለፈ፡፡ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሀገራቸው በሽታውን ለመቆጣጠር የሌሎች ሀገራት የጤና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጋቸው ገለጹ፡፡ ኃያሏ ሀገር በዚህ መጠን ብርክ ብርክ ይላታል ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም፡፡ ዛሬ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ መጽሔታችን ለሕትመት እስከበቃችበት ጊዜ ድረስ ብቻ እንኳን ከ32 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ ተይዘውባታል፡፡ ከአንድ ሚሊየን በላይ ዜጎቿንም በሞት አጥታለች፡፡ እርሷን ተከትሎ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ፈረንሳይና ሩሲያ በበሽታው ክፉኛ የተጠቁ አምስቱ የዓለማችን ሀገራት ሆነዋል፡፡

በዓለማቀፍ ደረጃ በበሽታው የተያዙት ዜጎች ቁጥር ከ138 ሚሊየን በላይ ደርሷል፡፡ ወደ ሦስት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙባት ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ በላይ ዜጎቿን በሞት አጥታለች፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃም በበሽታው ከተጠቁ ሀገራት መካከል 64ኛ ደረጃ ይዛለች፡፡

እነኚህ ሁሉ ቀውሶች ሲታሰቡ ታዲያ ‹የኮቪድ – 19 ጉዳይ እነ ኢያን ሊፕኪን መረጃውን ባገኙበት ወቅት ተደርሶበት ቢሆን ኖሮ ለዚህ ሁሉ ጉዳት ከመዳረጉ በፊት በቁጥጥር ስር መዋል ይችል ነበር ይኾን?› የሚል ቁጭት ውስጥ ያስገባል፡፡

(የጽሑፉ ዋነኛ ምንጭ ዘ – ዋሽንግተን ፖስት መሆኑን መግለጽ እንወዳለን)

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe