የተገደሉት የኢዜማ አባል “ማስፈራሪያ እና ዛቻ” ይደርስባቸው ነበር ተባለ

ባለፈው ዕሁድ በቢሾፍቱ ከተማ የተገደሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አባል ላይ ቀደም ሲል ዛቻና ማስፈራሪያ ተፈጽሞባቸው እንደነበር ተገለጸ።

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኢዜማ የቢሾፍቱ ከተማ የአድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ግርማ ሞገስ እሁድ ዕለት መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ በጥይት ከመገደላቸው ቀደም ብሎ ማስፈራራሪያ ይደርሳቸው ነበር።

የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ታሪኩ ለገሰ ትናንት ሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ እሁድ በግምት ከምሽቱ 3፡00 ላይ መምህር ግርማ ሞገስ የተባሉ ግለሰብ “ለጊዜው ማንነቱ ባልታወቀ ተጠርጣሪ” በጥይት መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

የከተማው ፖሊስ ጥቃቱን የፈጸመውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ተናግሯል።

የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ እንደገለፁት፣ “አቶ ግርማ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከሚያደርጉት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ማንነታቸውን ከማያውቋቸው ሰዎች ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስባቸው እንደነበር ለፓርቲው ሪፖርት አቅርበው ነበር።”

ፓርቲውም በቀረበው ሪፖርት መሰረት ክትትል ሲያደርግ እንደነበርም ተናግረዋል።

ኮማንደር ታሪኩ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ከመምህር ግርማ ጋር ግጭት የነበራቸው ግለሰቦች ያስፈራሯቸው እና ይዝቱባቸው እንደነበር መረጃ መገኘቱን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

ማስፈራሪያ እና ዛቻ ያደርሱ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ገልፀዋል።

እሁድ ምሽት የተፈፀመው ግድያ፣ ሲደርስባቸው ከነበረው ማስፈራሪያና ዛቻ ጋር ይያያዛል ወይስ አይያያዝም? የሚለውን ጉዳይ ማጣራት እንደሚያስፈልግው አቶ ናትናኤል ገልፀው፤ ኢዜማ ማጣራቱ ተደርጎ እንዳበቃ በይፋ እንደሚገልፅ አቶ ናትናኤል አሳውቀዋል።

ኢዜማ ከግድያው ጋር በተያያዘ ከመንግሥት ኃላፊዎች እና ከአካባቢው የፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ንግግር እያደረገ እንደሚገኝ አሳውቋል።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe