የታለመ የነዳጅ ‘ ቅሸባ’?

መነሻ

አቶ ተስፋሁን ፀጋዬ በነዳጅ ትራንስፖርተርነት ከ20 ዓመታት በላይ የስራ ልምድ ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ አቶ ተስፋሁን የራሳቸውን የነዳጅ ቦቴ ገዝተው አገልግሎት መስጠት ከመጀመራቸው በፊት በነዳጅ አመላላሽነት ለበርካታ አመታት ሰርተዋል፤ ከጅቡቲ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ነዳጅ በማዳረስ ስራ ላይ እንደመቆየታቸው ከነዳጅ ላይ የሚገኘው ትርፍ አነስተኛ መሆኑን ይገነዘባሉ፤ በመሆኑም በርካታ የሚባሉ የነዳጅ ቦቴ አሽጀከርካሪዎች በመደበኛ ደሞዛቸው ቤተሰባቸውን ሊያስተዳድሩ ስለማይችሉ የነዳጅ ቅሸባ ውስጥ እንደሚገቡ ይናገራሉ፤

ይህንኑ ጠንቅቀው ስለሚያውቁም አሁን ራሳቸውን የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ገዝተው ለሹፌር ሲሰጡ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በጥንቃቄ እንደሚከታታሉ ይናገራሉ፡፡ አቶ ተስፋሁን እንደሚሉት አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ነዳጅ ቀድተው የሚወጡት መጠንና ለነዳጃ አዳይ ጣቢያ የሚያስረክቡት መጠን ልዩነት አለው፤ ይሄ ደግሞ የሚሆንበትን መንገድ እንዲህ ያብራራሉ፡፡

‹አንድ ነዳጅ ቀጂ አሽከርካሪ ነዳጅ የሚቀዳበትን ቦቴ ወደ ጅቡቱ አስገብቶ ነዳጁን ሲቀዳ በወረቀት ላይ የታዘዘው ሊትር  40 ሺ ሊትር ቢሆን ከጅቡቲ ከወጣ በኋላ ከ2 እስከ 3ሺ ሊትር ያህል ነዳጅ ከቦቴው ላይ ይቀንስና ይሸጣል፤ እናም የጎደለውን ነዳጅ ይዞ ወደሚያራገፍበት የነዳጅ ማደያ ከተማ መግቢያ ላይ ሲደርስ መኪናውን ያዝ ለቀቅ እያደረገ በመንዳት ነዳጁ አረፋ እንዲያወጣ ያደርገዋል፤ ልክ ነዳጅ ማደያ ጣቢያው ጋር ሲደርስ የጎደለው ቦቴ አረፋ ደፍቆ

ስለሚደርስ የነዳጅ ተረካቢዎች መኪናው ላይ ወጥተው በሰነድ ላይ የተፃፈውንና የመኪናውን የነዳጅ መጠን በሚመለከቱበት ወቅት ቦቴው ሞልቶ ስለሚታይ 40 ሺ ሊትር እንደመጣ በመቁጠር ፈርመው ይረከባሉ፤ ነገር ግን እነርሱም የተረከቡትን ነዳጅ ለየመኪናዎቹ ሲሸጡ የነዳጅ ትርፍ ህዳጉ በጣም አነስተኛ ስለሆነ የየራሳቸው ቅሸባ በማካሄድ ስለሚሸጡ የመጨረሻ ተጎጂው በተጠቃሚው ይሆናል› ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ አንዳንድ የድጎማው ተጠቃሚ የሆኑ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ቀድተው ቀኑን ሙሉ የትራንስፖር አገልግሎት ሰጥተው ከሚያገኙት ትርፍ ይልቅ መኪናቸውን አቁመው በመዋል ነዳጁን በትርፍ ቢሸጡ የበለጠ ትርፋማ በመሆናቸው በየዕለቱ ነዳጅ በድጎማ በአነስተኛ ዋጋ እየገዙ መኪናቸው እንደተበላሸ በማስመሰል በየመንገዱና በየመንደር መተላለፊያዎች ውስጥ በማቆም ጫት ሲቅሙ የሚውሉ አሉ፡፡በመሆኑም ስራ ሰርቶ ገቢ ከማግኘት ይልቅ መኪና አቁሞ የሚገኘው ትርፍ የተሸለ በመሆኑ የትራንስርት አገልግሎቱ ላይ ትልቅ ተፅእኖ ይፈጥራል፡፡

ሌላው የነዳጅ ቅሸባ ክስተት ደግሞ ጉዳዩን እንዲቆጣጠሩ ሃላፊነት ከተሰጣቸው የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር በመመሳጠር የሚፈጸም ስለመሆኑ የትራንስፖርት ዘርፍ አሽከርካሪዎች ይናገራሉ፡፡ እንደ አብነትም ከአዲስአበባ ወጣ ባሉ እንደ ሀዋሳ ፤አርሲ ነገሌ፤ ድሬዳዋ ኮምቦልቻ፤ ማርቆስና ናዝሬት ባሉ ከተሞች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ በሆኑ ተሸከርካሪዎች ፋንታ የቤት መኪናዎች ሳይቀር ነዳጅ የሚቀዱበትን ሂደት በመፍጠር ሌሎች የግል መኪና አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጥረት ሲቸገሩ ነዳጅ በእጥፍ እንዲገዙ የሚገደዱበት ሁኔታ አለ፡፡ በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነ  አንድ የግል ዩኒቨርሲቱ መምህር በሳምንት ለአንድ ሙሉ ቀን ነዳጅ ለመቅዳት መድቦ እንድሚውልና ሳያገኝ የሚመለስበት አጋጣሚ እንደሚበዛ ይናገራል፤ ‹አንዳንድ ቀን ነዳጅ ለመቅዳት ከቤቴ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እወጣለሁ፤ ወረፋው ግን የሚደርሰኝ ከቀኑ 12 ሰኣት ላይ ሊሆን ይችላል፤ በመሀል እየገቡ የሚቀዱትን ተሸከርካሪዎች የሚቆጣጠሩት የመንገድ ትራንስፖርት

ሰዎችና ፖሊሶች ናቸው፤ እኛ ለምሳ እንኳ ከወረፋችን መውጣት ስለማንችል ምግብ አስመጥተን እዛው መኪና ውስጥ ስንመገብ እነርሱ ግን በአካባቢያችን ባሉ ስጋ ቤቶች ነው ምሳቸውን የሚበሉት› ሲል ይናገራል፡፡

መንግስት የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን በየጊዜው ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ መሠረት በማድረግ እያስተካከለ ወደ ተጠቃሚው ለማስተላለፍ የወጠነው ውጥን ተግባራዊ መደረግ ቢጀምርም የታሰበውን የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት ከማቀላጠፍ ይልቅ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የትራንስፖርት ፈላጊዎች ሰልፍ ከመቶ ሜትር በላይ ሲሆን እየታየ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት መንግስት የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ወደ ተጠቃሚው ሳያስተላልፍ በመቅረቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ ጫና ሲያስከትል ቆይቷል ባይ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ ክለሳ እየተደረገ ሲሆን በሂደት ወደ ተጠቃሚው በሚደረገው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ በተለይም ዝቅተኛ የመግዛት አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑ እየታየ ነው፡፡የመንግስት እቅድ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት አነስተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ሳይጎዳ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ቢሆንም በድጎማው ተጠቃሚ የሆኑ የግልና የመንግስት ቀሻቢዎች መፈጠራቸው የኢኮኖሚው ራስ ምታት ሆኗል፤

ስርዓቱን ለመተግበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡትን ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተሸከርካሪዎችን በመለየት እና በታለመ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም ጀምሮ ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ የመጀመሪያ ደረጃ የትግበራ መርሃ ግብር መስከረም 30/2015 ዓ.ም ተጠናቆ ሁለተኛው መርሃ ግብር ጥቅምት 01/2015 በማስጀመር ወደ ሶስተኛው ትግበራ ተግባራዊ እየተደረገ ቢሆንም ውጤቱ ግን አሁንም አመርቂ አለመሆኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚሰጡት አስተያቶችና ተጨባጭ ችግሮች መረዳት ይቻላል፡፡እስከ ህዳር 6/2015 ዓ. ም ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቴሌ ብር በተካሄደ የነዳጅ ግብይት፤ ድጎማ ተጠቃሚ ከሆኑ ተሸከርካሪዎች ውስጥ መካከለኛ የከተማ ህዝብ ማመላለሻ(midi bus) 39% ሚኒ ባስ ተሸከርካሪ (mini bus) 37% ግብይት ድርሻ እንዳላቸው ያሳያል፡፡

ነዳጅን የማስመጣትና ስርዕቱን የመቆጣጠር ሃላፊነት የተጣለበት የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የታለመ የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን አድርጊያለው ቢልም አሁንም ድረስ ችግሩ እንዳለ ነው፡፡ መ/ ቤቱ የሁለቱን ምዕራፍ አፈጻፀም ግምገማ መረጃዎች እ ን ደ ሚ ያ ሳ ዩ ት ከሆኑ የታለመ ነዳጅ ድጎማ ስርዓት ትግበራን በተመለከተ በ የ ደ ረ ጃ ው ለሚገኙ ለሁሉም ክልሎች የንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ትግበራው ከመጀመሩ አስቀድሞ የነዳጅ ግብይት ሪፎርም አፈጻጸምን፤ የነዳጅ የነዳጅ ውጤቶች ስርጭት፣ርክክብና ሽያጭ አፈጻጸምን፤ ማደያ በሌለባቸው ከተሞች እና አከባቢዎች የነዳጅ የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር በተመለከተ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል ብሏል፡፡

በድጎማ ስርዓት ተጠቀሚ እንዲሆኑ የተለዩ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጪ ተሸከርካሪዎች የነዳጅ ግብይትን  ቴሌብር እንዲያከናውን የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት 1060 ማደያዎች የተሌብር ግብይት መፈፀም የሚያስችላቸውን ምዝገባ ያደረጉ ሲሆን ባለፉት አምስት ወራት 966 የነዳጅ ማደያዎች በቴሌብር ግብይት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡ 187,757 ተሸከርካሪዎች በቴሌብር ግብይት ለመፈፀም የተመዘገቡ ሲሆን፤ የታለመ ነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከተደረገበት ሐምሌ 1/2014 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 10/2015 ዓ.ም በድጎማ ነዳጅ የቀዱ ተሸከርካሪዎች 113,229 ናቸው፡፡ከሐምሌ 1/2014 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 10/2015 ዓ.ም በመንግስት ለድጎማ የተከፈለ ብር 3,726,907,041.58 መሆኑ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት በታለመ ነዳጅ ድጎማ ትግበራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መሠረት በማድረግ በሂደት ወደ ተጠቃሚው ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከነዳጅ ሽያጭ የሚሰበሰበው ታክስ በመጨመር ባለፉት አምስት ወራት 21 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል፤ ከዚህ በተጨማሪም የአገር ውስጥ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ በመደረጉ ከጎረቤት አገራት መሸጫ ዋጋ ጋር መቀራረቡ ኮንትሮባንዱ እንዲቀንስ ማድረጉ፤ በነዳጅ ግብይቱ ይስተዋል የነበረውን ኮንትሮባንድ ለመቆጣጠር የሚያስችል የኮታ ስርዓት በመተግበር በአጠቃላይ ወደ ሀገሪቱ ይገባ ከነበረው ነዳጅ በድንበር አከባቢ ይሰራጭ የነበረን 11.3 በመቶ ድርሻ ወደ 4.5 ዝቅ እንዲል በማድረግ ኮንትሮባንድ ለመቀነስ ተችሏል ይላል፡፡ የነዳጅ ርክክብ መመሪያ ተግባራዊ መደረጉም፤ በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በየወሩ ከ10-15 ቢሊየን ብር ይመዘገብ የነበረውን ዕዳ ወደ አምስት ቢሊየን ብር ማውረድ መቻሉ ተገልጧል፤ ባለስልጣኑ በነዳጅ ድጎማ ስርዓት የተገኙ ስኬቶችን ቢዘረዝርም በአተገባበር ሂደቱ የታዩ ሰፊ ችግሮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ እንደ አብነትም በወረዳ ንግድ ቢሮ በተመደቡ ባ ለ ሙ ያ ዎ ች ቅዳሜና ዕሁድ በማደያዎች ተገኝቶ ነዳጅ ርክክቡን

ለመፈጸም ላይ አ ለ መ ቻ ላ ቸ ው ፤ የትራንስፖርት እጥረት ባለባቸው እና የቦታ ርቀት ባ ለ ባ ቸ ው አ ከ ባ ቢ ዎ ች እንዲሁም በስራ መውጫና መግቢያ ሠዓት በታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ__የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በታሪፍ ከተፈቀደ በላይ ሲያስከፍሉ የሚመለከታቸው የመንገስት ተቆጣጣሪዎች አይተው እንዳላየ ማለፋቸው እንዲሁም ማደያ ባለባቸው አከባቢዎች ነዳጅን ከማደያ ውጪ በህገወጥ መንግድ ሲሸጥ ለማስቆም

ፍላጎት ማጣት እና ከነዳጅ ማደያዎች በጀሪካን እና በርሜል ፈቃድ ሳይኖር እና ፈቃድም እያላቸው ከተፈቀደ መጠን በላይ መቅዳት በስፋት የሚታይ ችግር ነው፡፡ ያም ሆኖ በጥር ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ አዲስ የዋጋ ማስተካከያ የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር በየጊዜው የሚያስታውቅ ሲሆን ሚኒስቴሩ ከታኅሣሥ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚሆን የነዳጅ

ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ክለሳ አድርጓል።

በዚሁ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ የሚሆነው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ፦ ቤንዚን በሊትር – 61 ብር ከ29 ሣንቲም፤ነጭ ናፍጣ በሊትር – 67 ብር ከ30 ሣንቲም፤ኬሮሲን በሊትር – 67 ብር ከ30 ሣንቲም ፤ቀላል ጥቁር ናፍጣ ፤ 49 ብር ከ67 ሣንቲም ፤ከባድ ጥቁር ናፍጣ፤ 48 ብር

ከ70 ሣንቲም፤የአውሮፕላን ነዳጅ ፤ 67 ብር ከ91 ሣንቲም መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ

ትሥሥር ሚኒስቴር ገልጿል። ይህ የነዳጅ ዋጋ እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ የሚሰራ ስለመሆኑ

ሚኒስቴሩ አስውቋል፤  በዚሁ መሠረት በአንድ ሊትር ቤንዚን ሲሰጥ የነበረው ድጎማ ከብር 15.76 ወደ ብር 17.33 እንዲሁም የአንድ ሊትር ናፍጣ  ድጎማ ከብር 19.02 ወደ ብር 22.68 ከፍ እንዲል መደረጉ ተገልጿል። በዚሁ አግባብ በመንግሥት የሚሰጠው ድጎማ በወር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተገምቷል።  በመሆኑም የደሃውን ኅብረተሰብ የኑሮ ጫና ለመደገፍ መንግሥት ነዳጅ ላይ እያደረገ ያለው ድጎማ ኅብረተሰቡ ዘንድ በትክክል እንዲደርስ እና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ የሚመለከታቸው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እና በየደረጃው የሚገኙ ተቆጣጣሪ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ቢያሳስብም አሁንምድረስ በከተሞች ረዣዥም ሰልፎችን መመልከት ብርቅ አልሆነም፡፡ ስራ ሳይሰሩ መኪናዎቻቸውን አቁመው የነዳጅ ድጎማ የሚያገኙና ነዳጁን ወደ ክፍለ ሀገር ልክው በውድ ዋጋ የሚሸጡ አሽከርካሪዎች መታየታቸው አፋጣኝ እርምጃ የሚሻ ጉዳይ

ነው። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የነዳጅ  አዳዮችም ከጅቡቲ የተረከቡትን ነዳጅ በተለይ ቤንዚንን በማደያ ላይ በመንግሥት በተተመነው ለተሽከርካሪዎች ዋጋ ከመሸጥ ይልቅ በአሳቻ ሰዓት በበርሜልና በጄሪካን በመቸርቸር እጥረት እንዲፈጠር የሚያደረጉና በቴሌ ብር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰው ሠራሽ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ተስተውሏል፡፡

ኢትዮጵያ በኣመት ለነዳጅ መግዢያ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የምታደርግ ሲሆን ወደ ሀገር ቤት ብር ሲመነዘር ወጪው ከ250 ቢሊዮን በላይ ይደርሳል፤ ነዳጅን ከቅሸባ ለማዳን በሚል ግብይቱን በቴሌ  ብር ለማድረግ እቅድ የተነደፈ ቢሆንም ማሽን ተበላሸ፤በመንገድ ተዘጋ በሚል ነዳጅ በማደያቸው ይዘው የማይሸጡ ነዳጅ አዳዮች መኖራቸው ችግሩን ይፈታዋል ወይ ያሰኛል፤ ለሀገር ኢኮኖሚ አዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነው ነዳጅ በድጎማ ስርዓት ሙሉለሙሉ ወደ ተጠቃሚው ሳይተላለፍ ገና በጅማሮ ላይ ሆኖ የዚህ አይነት ችግሮች ከተስተዋሉ መንግስት በእቅዱ መሠረት ሙሉ ለመሉ ራሱን ከድጎማ ስርዓቱ ሲያወጣ ኢኮኖሚውን ሊያኮማትረው እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ፤ በመሆኑም ነዳጅ እንደማንኛው ሸቀጥ ተቆጥሮ በነፃ ገበያ ይሸጥ ከመባሉ በፊት የህዝብ ትራንስፖርት አግልግሎት ሰጪዎችን በስፋትና በተደራሽነት ማስፋፋ ከወዲሁ ሊታሰብብት የሚገባ እቅድ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ አለበለዚያ

ህብረተሰቡን ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሳይሆን ለታለመለት የነዳጅ ‹ቅሸባ› እያጋለጠ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe