ይልቅ ወሬ ልንገርህ:- ስለ ታማኝ በየነ ‹ሿ ሿ›

የከተማ ልጆች ሿ ሿ ይሉታል፡፡ በተለይ በህዝብ ማመላለሻ ታክሲ ላይ የሚፈፀምን  ማጭበርበር፡፡ ታክሲ ተሳፍረው ከሆነ በተቀናጀ፤ በተጠናና የእርስዎን ቀልብ ሊያስት በሚችል መልኩ የሚፈፀም  ይህ የዘረፋ ስልት ተራ ኪስ የማውለቅ ስራ ነው፤ ብዙዎች በታክሲ ላይ የሿ ሿ ሰለባ መሆናቸውን የሚያውቁት አውራ ጎዳና ላይ ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለሻ የመሳፈሪያ ሳንቲም እያዋጡላቸው መሆኑን ሲገነዘቡ ነው፡፡

ይህ ክስተት በአዲስ አባባ በተለያዩ አካባቢዎች በየዕለቱ የሚፈፀም ክስተት  ይሁን እንጂ ሀገራዊ መልክ ይዞ በአደባባይ በመንግስት ባለስልጣናት ሽፋን  ይፈፀማል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የዚህ አይነት አዋራጅ ተግባራት በታዋቂ ሰዎች ላይ ሳይቀር መፈፀሙ የነገሩን አሳሳቢነት በአደባባይ አንድንወያይበት ያደርገናል፡፡

በዚህ ረገድ በአደባባይ ሿ ሿ ከተሰሩ ታዋቂ ሰዎች መሀከል የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ አሁን ያለው የለውጥ ሀይልን ሀገሪቱ ለማዋለድ ምጥ ላይ በነበረችበት ጊዜ በቀድሞው እናት ድርጅታቸው ኦህዴድ አማካይነት አንዳች የምስራች እንዲደርሳቸው ተደርጎ ነበር፡፡ ከመንግስት ስልጣን ከተሰናበቱ በኋላ ታክሲ እየጠበቁ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ ለነበሩት ለዶ/ር ነጋሶ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የ2018 ዘመናዊ ኒሳን  መኪና መሸለማቸውን የሚያመለክት ዜና ይፋ ሆነ፡፡ መገናኛ ብዙሃኑም የግል ጥቅም ሳያጓጓቸው ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ላገለገሉት ዶ/ር ነጋሶ ‹ይገባቸዋል› በሚል ስሜት አየሩን ሞሉት፡፡ ከመኪና ሽልማቱ በተጨማሪም ሙሉ የህክምና ወጪያቸውን በውጭ ሀገር እንዲያደርጉ መፈቀዱን ይፋ ሆነ፡፡ ይህን ተከትሎም  ‹ተሸለሙ ›የተባሉትን መኪና ምስልና ቁልፍ ሲረከቡ የሚታዩበትን ፊልምም በማሳየት ሀገር፤ ህዝብና መንግስት ውለታቸውን መለሱላቸው አስባሉ፡፡

<“የግድቡን ጉዳይ ወደ ማይመለከታቸው የአረብ ሀገራት ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት አንቀበልም” ውጭ…>

ከጥቂት ወራት በኋላ ግን  ‹ተሸለሙ › የተባሉትና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር የታየው መኪና የውሃ ሽታ መሆኑን ዶ/ር ነጋሶ ራሳቸው ሲቃ እየተናነቃቸው ለቁም ነገር መፅሔት እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፡፡

‹መኪና የተባለው በኦሮሚያ ምክር ቤት ትርፍ ስላለ ለጊዜው በዚህ ተጠቀም ሌላ ይገዛልሃል ነው ያሉኝ፡፡ነገር ግን እስካሁን አልተገዛም፤አሁንም በውሰት መኪና ነው እየተገለገልኩ ያለሁት፡፡ ያው የጤንነቴ ጉዳይም ቢሆን በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር የማደርገውን ህክምና በራሴ ወጪ እንጂ በተገባልኝ ቃል መሠረት አይደለም እየታከምኩ ያለሁት›

ይህ ሀገርና ህዝብን  ያገለገሉ ሰዎችን በሽልማት ስም የማሸማቀቅ ተግባር ዛሬም መልኩን ለውጦ መምጣቱ እየታዘብን ነው፡፡ ተወዳጁ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከ22 ዓመታት ስደት ኑሮ በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ሃገሩ ሲገባ በሀገር ፍቅር ስሜት የነደዱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  መንገዱን ሞልተውት ‹እንኳን ደህና መጣህ!› እንዳሉት እናስታውሳለን፡፡ በየትውም የሀገሪቱ ስፍራ የሚኖር ዜጋ ሁሉ ወገኔ ነው ብሎ የሚያምነውና ለዘመናትም ኢትዮጵያዊነትን ያለማቋረጥ ሲያቀነቅን የኖረው ታማኝ ከአዲስ አበባ በኋላ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሄድ የወገን ፍቅሩን ብቻ ሳይሆን የሀገር ናፍቆቱን ሲወጣ ነበር፡፡

ታዲያ በየሄደበት ቦታ ሁሉ ለሀገርሩና ለወገኑ ላበረከታቸው አስተዋፅኦዎች ልዩ ልዩ ሽልማቶች ከባለቤቱ አርቲስት ፋንትሽ በቀለ ጋር ሲቀበል ነበር፡፡  የዚህ አይነት የክብር ሽልማቶች በስፋት ከተበረከተላቸው አካባቢዎች መሀከል አንዱና ምናልባትም ግንባር ቀደሙ የአማራ ክልል ነበር፡፡ ታማኝ ወደ ከትውልድ መንደሩ ከጋይንት ጀምሮ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች በሙሉ ህዝቡ አደባባይ እየወጣ ‹እንኳን ለሀገር አበቃህ!› ይሉት ነበር፡፡

ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ታማኝ ተወልዶ ወደ አደገባት ‹ላይ ጋይንት› ከተማ ሲደርስ የነበረው ትዕይንት ልዩ ነበር፡፡  ከ114 ሺ በላይ ህዝብ በመንገዱ ግራና ቀኝ ቆሞ ከ22 ዓመታት ስደት በኋላ ታማኝ ወደ ውድ ሀገሩ በመግባቱ ህዝቡ  ደስታውን በጭፈራ ይገልፅ ነበር፡፡ ከዚያስ ?

ከዚያማ የከተማው አስተዳደር የአካባቢው ህዝብና የአማራ ክልል ባለሃብቶች እንደ ስሙ ታማኝ ሆኖ በፅናት  ለታገለው ታማን በየነ የስጦታ አይነት  ይበረከትለት ጀመር፡፡

<“ገዢው ፓርቲ የዘንድሮውን ምርጫ የማሸነፍ እድል የለውም” እናት ፓርቲ>

የከተማው አስተዳደር ታማኝ ወደ ላይ ጋይንት መግባቱን ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ ያሳየውን የደስታ ስሜት መሠረት በማድረግ ለታማኝ የክብር አቀባባል የተደረገበትን ሰላም የስፖርት ማዘውተሪያ ‹ ታማኝ በየነ ስታዲየም› ብሎ በማኔጅመንት ደረጃ በመሰየም ለህዝብ ይፋ አደረገ፡፡

የአካባቢዊው ነዋሪዎችም ለሚወዱት ለሚያከብሩትና እንደ ጀግና ለሚመለከቱት ግለሰብ የሚያበረክቱትን  የማዕረግ ፈረስ ከእነ ጦርና ጋሻው  በሽልማት እነሆ አሉ፤ የደለበ በሬም ተበረከተለት፡፡ የነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር ለታማኝና ለውድ ባለቤቱ የክብር ካባ ደረበላቸው፡፡ የአማራ ክልል ባለሀብቶችን በመወከል የተሰባሰቡ የሀብት መጠናቸው እንደ መጋዘን በር የከበዱ ባለሃብቶች ደግሞ በጥበብ በማዝናናት፤ የወገኖቹን የሰብዓዊ መብት ጥሰት  በማስተጋባትና በበጎ አድራጎት ተግባራት ስራ ላይ በመሰማራት ለሰራው የላቀ አስተዋፅኦ ለታማኝ በየነ ጂኤምሲ የተሰኘች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላት የ2019 ዘመናዊ አውቶሞቢል መኪና ተበረከተለት፡፡ ሽልማቱን በወቅቱ ለታማኝ ያስረከቡት የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሟቹ ዶ/ር አምባቸው መኮንን ነበሩ፡፡

ይህ በክልል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ በህዝብ ፊት የተሰጠው ሽልማት ግን ታማኝ እጅ አለመግባቱን የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን? ታማኝ በየነ እንደ ስሙ የታመነ ለሽልማት፤ ለክብርና ለውዳሴ ብሎ የማይሰራ  ለወገኖቹ ያለውን ፍቅር በማውራት ሳይሆን ሲቸገሩ በመርዳት በተግባር የሚያሳይ ሰው ነው፡፡ ታማኝ በየነ የእርሱ ምኞት፤ ጉጉትና ረሃብ በወገኖቹ መሀል መገኘት እንጂ ለታይታ በአደባባይ ‹አከበርነው› ከሚሉ ሰዎች ጋር መታየት አልነበረም፡፡

ታማኝ በየነ በአሜሪካ የረዥም ዓመታት የስደት ኑሮው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ለደቂቃም ቢሆን ረስቶ አያውቅም፡፡ በረሃብ፤በጦርነት በበሽታና በድህነት ለስደት ለመፈናቀልና ለእርስ በእርስ ግጭት ስንዳረግ የእርዳታ አኮፋዳቸውን ይዘው አደባባይ ከሚቆሙ ኢትዮጵያውያን መሀከል ቀዳሚው  ታማኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አብረን ስንቆም ብቻ እንደሚያዋጣንና በዘር በጎሳና በብሔር ስንከፋፈል ተያይዘን እንደምንወድቅ ደጋግሞ የሰበከ ሰው ነው፡፡ ታማኝ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለዘመናት ሲያገለግሉ ኖረው በዕድሜያቸው ማምሻ ላይ መታከሚያ አጥተው በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የተያዙ የሀገር ባለውለታዎችን ለማሳከም ሲታትር የኖረ ሰው ነው፡፡ ‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር › እንዲሉ  ከ22 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ሀገሩ ሲገባ በህዝቡ አቀባበልና ፍቅር ቢደሰትም ስሜቱን የሚያጎሹ ነገሮች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡

ባላፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በብሔራዊው ጣቢያ  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀረበ ‹በእኛ ፋታ› በተሰኘ ሳምንታዊ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት የቀረበው ታማኝ ከአርቲስቶች ፤ ከአድናቂዎቹና ከሙያ ጓደኞቹ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ ነበር፡፡ ከጠያቂዎቹ መሀከል አንዱ ‹የተሸለምከውን መኪና ስትነዳ አላየሁም፤ለምንድነው? › የሚል ጥያቄ ሰንዝሮ ነበር፡፡

<ዓለምፀሐይ “አድርጉ” አላለችንም፤ ራሷ ያሰበችውን በተግባር ፈፅማ አሳይታናለች – አቶ ደመቀ…>

ለሌሎች እንጂ ለራሱ ተጨንቆ የማያውቀው ታማኝ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከራሱ ጋር ሲታገል በቴሌቪዥኑ ስክሪን ላይ  ይታይ ነበር፡፡ማፈር ካለባቸወ ማፈር ያለባቸው ሽልማቱን ‹ሸልመናል› ብለው በህዝብ ፊትና በሚዲያ ያስነገሩት የክልሉ ባለሃብቶች መሆን ሲገባቸው ተሸላሚው የሚጨናነቅበትና የሚያፍርበት ዘመን ላይ መድረሳችን አስገራሚ ሆኗል፡፡ታማኝ ከብዙ ማመንታትና መጨነቅ በኋላ የሰጠው መልስ አጭር ነበር፤‹ይህንን ጥያቄማ  ሸለምን ያሉ ሰዎችን ጠይቋቸው› የሚል ነበር፡፡በአጭሩ ታማኝ በየነ ሿ ሿ ተሰርቷል፡፡

ከ40 ዓመታት በላይ በመድረክና በአደባባይ ሲጮህ ለኖረው ለታማኝ ሽልማት ሲያንሰው እንጂ የሚበዛበት አልነበረም፡፡ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሀገርና መንግስት ሊያከብሩት የሚገባ ሰው ነው፡፡ የዛሬ 30 ዓመት ‹ህዝብ ለህዝብ› በተባለውና የኢትዮጵያን ባህላዊ ጨዋታዎች ለማስተዋወቅና በወቅቱ ተከስቶ ለነበረው ድርቅ እርዳታ ለሰጡ መንግስታት ምስጋና ለማቅረብ  በአውሮፖና በአሜሪካ በተዘዋወረው ቡድን ውስጥ ታማኝ አባል ነበር፡፡በወቅቱ በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ሙዚቀኞች ድንገት በጠፉበት ወቅት ሀገርና ህዝብን ከውርደት የታደገው ታማኝ በየነ ነበር፡፡ የጠፋውን ከበሮ ተጫዋች ቦታ በመሸፈን፡፡ በኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ወቅት ‹ኢትዮጰያ ተወረረች› በተባለበት ወቅት ምንም እንኳ ከመንግስት ጋር የአቋም  ልዩነት ቢኖረውም ህዝብንና ሀገርን አስቀድሞ ሙዚቀኞችን በማስተባበር የእርዳታ እጁን የዘረጋ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን የቆመ ሰው ነው፡፡ ከ100 በላይ አርቲስቶችን አስተባብሮ በሰራው የሙዚቃ ኮንሰርት ከ70 ሺ ዶላር በላይ ገቢ አድርጓል፡፡ በአሜሪካ ሀገር 100 ዶላር ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ ለሚያውቅ ሰው 70 ሺ ዶላር  ማለት ምን ማለት ነው?  ይህንን  የሚያውቅ ሰው ታማኝ ከውጭ ሲገባ ከወንበሩ ይነሳለት ነበር፡፡

በባዶ እግር፤ በተቀደደ ቁምጣ  ሱሪ፤ የጨርቅ ኳስ እየተጫወተ  በገጠር በድህነት ላደገው ታማኝ ለፅናቱና ለታማኝነቱ ክብር መስጠት ራስን ማክበር ነበር፤

ግና ታማኝ ለእርሱ  ይሄ ምኑም አይደለም፤ በዓለም ላይ የታወቁ  ቦታዎችን እንደ ብዙዎቻችን የኢሚግሬሽን ሰልፍ ጠብቆ ሳይሆን በግል አውሮፕላን ጭምር ከሀገር ሀገር በሮ አይቷል፡፡ አሉ የተባሉ መድረኮች ላይ ለሚሊዮኖች ስራዎቹን አቅርቧል፤ በክብር በተጋበዘባቸው ሀገራት ላይ በቀይ ምንጣፍ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ከሀገራችን የሙዚቀ ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ ጀምሮ ከብዙዎቹ  እንቁ አርቲስቶች ጋር መድረክ ላይ ቆሟል፡፡ከሁሉም በላይ  ለዘመናት ሲያቀነቅነው የነበረው ኢትዮጵያዊነት በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት ሲነገር ሰምቶ ፊቱ በእንባ ታጥቧል፡፡ ለአንዳንዶቻችን ብርቅ የሆኑት  ፈረስ ግልቢያም ሆነ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ዘመናዊ መኪና እያሽከረከሩ መጓዝ ታማኝን የሚያጓጓ አይደለም፡፡ ያማልለዋል ተብሎም አይታሰብም፡፡

ታማኝ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለሶስት ጊዜ ያህል ወደ እናት ሀገሩ ተመላልሷል፡፡ ሲመጣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተሰቡን ለመጠየቅና ናፍቆቱን ለመወጣት ቢሆንም እየቆየ በሚያገረሸው ግጭትና ላለፉት 27 ዓመታት የተቀበሩት የዘረኝነት ፈንጂዎች ውዱ የሰው ልጅ ህይወት ሲቀጠፍ ፤ ሲፈናቀልና እህል ውሃ ሲለምን  እፎይ ብሎ እንዲቀመጥ አላስቻለውም፤ በመጣበት ጊዜ ሁሉ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሚፈናቀሉ ወገኖቹን ለመርዳት አይዟችሁ ለማለት ነው፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት ከመተከልና ከትግራይ ግጭት ጋር ተያይዞ የተከሰተውን የወገኖቻችንን መፈናቀልና የረሃብ ችግር ለመጋራት በጣይቱ ሆቴል ስንዴና ዘይት ሲሸከም ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ታማኝ ለጊዜው ካረፈበት ከሸራተን ሆቴል ወደ ጣይቱ ሆቴል ይመላለስ የነበረው በጓደኞቹ መኪናና አልፎ አልፎ በራይድ  ነበር፤ ታማኝ ግን በዚህ ፈፅሞ የሚከፋ ሰው አልነበረም፡፡ እሱን የሚያስከፋው የወገኖቹ እንባና ለቅሶ ለማበስ አለመቻል ነው፡፡ የህፃናት የድረሱለኝ የጣር ድምፅና ኡኡታ ለማስቆም አቅም ማጣት ነው፡፡ የእናቶችን የመፈናቀል ዜናና ማህበራዊ ቀውስ ለመታደግ አለመቻል ነው፡፡ ተሰፋ ሲባል መልሶ የሚተረተረው የዘረኝነት ድር ነው የታማኝ ጭንቀት፡፡

ታማኝ ከረዥም ዓመት ስደት በኋላ ወደ ሀገር ቤት ከገባ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የማግኘት ዕድል ነበረኝ፡፡ በአደባባይ በስሜት ተውጦ ንግግር በሚያደርገው ታማኝና በዚህ ታማኝ መሀከል  ትልቅ ልዩነት  ነው ያለው፡፡  ታማኝ  ሰው አክባሪ ነው፡፡ እንባ የሚቀድመው አልቃሻ ነው፡፡ ለዓላማው ሟች ነው፡፡ ለሚወደው ሰው ባሪያ ነው፡፡ የጽናት ተምሳሌት ነው፤ ሁሉ ሰው ለእርሱ እኩል ነው፤ ዘር ፤ ብሔር ፤ሐይማኖት አይልም የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት የእርዳታ እጁን ሲዘረጋ፡፡ ስለ ሀገሩ ስለ ባንዲራውና ስለጥላሁን ገሠሠ ሲያወራ ውሎ ሲያወራ ቢያድር አይሰለቸውም፡፡ ሰውም ይሰለቸዋል ብሎ አያስብም፡፡  ይህንን ፍቅሩን  ደግሞ  በንድፈ ሀሳብ ሳይሆን  በተግባር አሳይቷል፡፡   ታማኝ  የማይታገሰውና የሚቀየመው አክብሮቱን ሲያጣጥሉበት፤ ፍቅሩን ሲንቁበት ፤ የሀገሩን ክብር ሲነኩበት ነው፤ ታማኝ አደባባይ ላይ አንደበተ ርትዑ ሆኖ ይናገር እንጂ በራሱ ጉዳይ  ይሉኝታ የሚያጠቃው ስስ ሰው  ነው፤ ለዚህም ነው ላለፉት ሶስት ዓመታት ‹ተሸለመ› ስለተባለው የሿ ሿ መኪና ዝምታን የመረጠው፡፡

ታማኝ በስደት አሜሪካ ሀገር ይኑር እንጂ ‹ከሀገሬ ወጥቼ በስደት እኖራለሁ› የሚል እምነት ፈፅሞ አልነበረውም፡፡ተገፍቶ ከሀገሩ  መጥቶ ለ22 ዓመታት በስደት መቆየቱን እስኪያውቅ ድረስ ከኢትዮጵያ ተለይቶ ሀገር ውጭ መኖር ለታማኝ ከባድ ነውር ነበር፡፡ ከሀገር ወጥቶ በስደት ትዳር መያዝ ከዚያም ሲያልፍ ልጆች ወልዶ ልጆቹን የውጭ ሀገር ዜጋ ማድረግ በታማኝ መዝገብ ውስጥ ሊታሰብ የማይችል ውርደት ነው፡፡ ታማኝ የሚያልማት ኢትዮጵያ በነፃነት የኖረች፤ የተከበረች፤ ህዝቦቿ በእኩልነትና በወንድማማችነት የሚያምኑ፤ አንድ ማዕድ የሚጋሩ፤  ፈርሃ እግዚአብሔር ያላቸው የአብሮነት ተምሳሌት ናት፡፡

እንደ ታማኝ አይነት ሙሉ ዕድሜውን ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነት ሲያቀነቅን ለኖረ ሰው መኪና ለዚያውም የመንግስት ባለስልጣናት ባሉበት ‹ሸለምኩ› ብሎ ሿ ሿ መስራት እንደ ሀገር አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ነውርም ነው፡፡ በስራቸው በተግባራቸውና በስብዕናቸው በራሳቸው ‹ሀገር› የሆኑ እንደ ታማኝ ላሉ ሰዎች ሀገር ከዚህ የበለጠ የክብር ካባ ማልበስ ትችል ነበር፡፡

<አሜሪካ ሶስቱም ሀገራት ካልጋበዟት በግድቡ ድርድር መግባት እንደማትችል አስታወቀች>

ለመሆኑ ህዝብ ፊት መኪና ሸለምን ያሉ የአማራ ባለ ሃብቶች ለቃላቸው ታማኝ ለመሆን ለምን አልቻሉም? ለዚያ በባዶ እግሩ እየሄደ ሀገር ስለሚያቀናው ድሃ ህዝብ ክብር ተጨንቀዋል? ታማኝ የህዝቡን ክብር ሞራልና ለመጠበቅ በሚል ለሶስት ዓመታት ያህል የያዘውን እውነት ዛሬ ለመናገር ሲጨናነቅ ማየት አያሳፍርም?  በታማኝ ስም በህዝብ ፊት እቃ እቃ መጫወት ለምን ተፈለገ?

እርግጥ ነው ይህንን ድርጊት ጊዜና ታሪክ ይፈርደዋል፡፡

ቴዲ አፍሮ ግን እንዲህ ይላል፡- ‹“የተማረ እንጂ የተባረከ መሪ ከለመንን ቆይተናል። የተማረ ከተገኘማ ጥሩ ነው የተባረከ ይሁን እንጂ። የተባረከ መሪ ግን ከተገኘ በጣም ጥሩ ነው ባይማርም እንኳን።”›

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe