በዘላለም ጌታቸው (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ ጽሑፍ መምህር
“ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ እና ሌሎች ወጎች“ የተሰኘው የታምራት ኃይሉ መጽሐፍ ሁለት ዋና ዋና ትሩፋቶችን ይዞልን የመጣ ይመስለኛል፡፡
የመጀመሪያው ከህትመትና ስርጭት ሥርዓት አኳያ የተገኘ ትሩፋት ነው፡፡
መጽሐፉ፣ በቅድመ ሽያጭ ከታተሙ ጥቂት መጻህፍት አንዱ ነው፡፡ የቅድመ ሽያጭ ጊዜውም ለአስር ቀናት ብቻ የቆየ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም፣ ለመታተም ከታቀደው ቁጥር በላይ የሚውል የማሳተሚያ ገንዘብ በማሰባሰብ ተጠናቋል፡፡ ይህ ችግር የወለደው አማራጭ የመጽሀፍ ህትመትና ስርጭት መንገድን ፈር አስይዞ፣ የምንወዳቸውን ደራሲያን መጻሐፍትን በቅድሚያ የምንገዛበት ሥርዓት እንደሚፈጥር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የመጽሐፉ የህትመት ሂደት አዲስ ፓራዳይም ሽፍት ይዞ የመጣ ነው፡፡ አዲሱ ለውጥ አዋጭነቱንም ያሳየ ነው፡፡ በነባሩ የህትመት አካሄድ፣ የህትመት ስራ እና ሂደት በደራሲው ላይ የወደቀ እዳ ነበር፡፡ የመጽሐፍ ህትመት ሥራ በጣም አሰልቺ፣ አድካሚ፣ ብሎም ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ብዙ ደራሲያንን ሳያሳጣን አልቀረም፡፡ አንድ መጽሐፍ አሳትመው “ለምን አልደገማችሁም?“ ሲባሉ ብዙ ደራሲያን የሚሰጡት መልስ ይህንኑ የህትመት ወጪ መሸፈን አለመቻልና የስርጭትና ሽያጭ አሰልቺነት ሂደትን መወጣት አለመቻልን ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይህንን ሂደት የሚያግዙ ድርጅቶች አልነበሩንም፣ አሁንም እየተፈጠሩ አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ህትመት እዳው ሁሉ በደራሲው ላይ የወደቀ ነበር፡፡ አሁን ግን ታምራት “ሀምሳ ሎሚ“ የሚለውን መርኅ ተግባራዊ በማድረግ ሂደቱን ያቀለለው ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ እነቴዎድሮስ ተ/አረጋይን የመሰሉ ቅን ሰዎችንም ትጋት አይተናል፡፡
ይህ የህትመቱ ሂደት ያቀለለው ጉዳይና ያስገኘው ጥቅም በሁለት መልኩ ልናው እንችላለን፡፡ አንደኛው ደራሲው ተበድሮ ወይም ንብረት ሸጦ ያሳትም የነበረውን አስቀረለት፤ ከእዳ ነጻ ወጣ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው “ሰው ገንዘቡ ባለበት ልቡ አለ“ ይባላልና የመጽሐፉ ጉዳይ ሲነሳ ከፋይ፣ ቀድሞ ከከፈለው መጽሐፍ ጋር ቁርኝቱ የጠበቀ ይሆናል፡፡ ይህ ሂደትም ማህበራዊነትን ያሰፋል፣ ቅርርብን ያመጣል፣ በአንባቢና ደራሲ መካከል የአለኝታና የዷደኛነትን መንፈስ ይፈጥራል፤ ባጠቃላይ ከፍ ያደርጋል፤ ያጠነክራል፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንደሚለው፣ ብርቱ ይኖራል (survival of the fittest) የሚለውን ሳይሆን (survival of the friendliest) ማህበራዊነት/ጓደኝነት ለህልውና የበለጠ ዋጋ አለው የሚለው የእዚህ ዘመን ገዥ መርህ እውን ያደርጋል፡፡ እንደዚህ ያለው ሥራ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ስሪት የሆነበትን የመተጋገዝ፣ የመተባበር መርህን ከፍ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪ የታምራት መንገድ በህትመትና ስርጭት ጣጣ ምክንያት ጸሐይ ያልሞቃቸው ስራዎችን ወደአደባባይ የሚያወጣ ይመስለኛል፡፡ የመጽሐፍ መብዛት የዕውቀት መብዛትን፣ የዕውቀት መብዛት ደግሞ ማህበራዊ እርምደትን ከፍ ያደርጋልና የእዚህን መጽሐፍ ህትመት ንቅናቄ ማህበረሰብን የሚያሳድግ ዕውቀትን የማስፋት ውለታ አድርገን ልንወሰደው እንችላለን፡፡ ታምራት እና መሰሎቹ እየፈጠሩልን ላለው አዲስ ባህል አክብሮቴ ከፍ ያለ ነው፡፡ መንገዱንም ብዙዎች እንደሚከተሉት አልጠራጠርም፡፡
ሁለተኛው ትሩፋት – በመጽሀፉ የቀረቡት አወያይና ኮርኳሪ ጭብጦች ናቸው፡፡
“ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድና ሌሎች ወጎች“ 19 ወጎችን እና 1 የግርጌ ማስታወሻን የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ኢ–ልቦለዳዊ እና ልቦለዳዊ ፈጠራዎችን አደባልቆ የያዘ መጽሀፍ ነው፡፡ የግርጌ ማስታወሻው ደግሞ የተለየ መልክ ያለው ነው፡፡ ወጎቹም ይሁኑ የግርጌ ማስታወሻው ከጋዜጠኝነት ህይወት የተቀዱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ወጎች የተወሰኑትን ምን አሳዩን የሚለውን በማንሳት፣ ከፊሉን ደግሞ ዋና ሀሳባቸውን በማካፈል ሀሳቦችን ልሰንዝር፡፡
መጽሐፉ “ሽልማት“ በሚል ወግ ይጀምራል፡፡ ይህ ወግ፣ “…ጋዜጠኛ የመባል ልዩ ፍላጎት ስለነበረኝ በልጅነቴ ከሬዲዮ የሰማሁትን ነገር በቃሌ አነበንብ ነበር፡፡..“ በሚል ዓረፍተ ነገር የሚጀምር፣ የአንድ ጀማሪ ጋዜጠኛን በስህተት የተሞላ ሥራን የሚያስነብበን፣ ስህተትን በፍጥነት እያረሙ የመሄድን የልምድ እጦት ላይ መሰረት አድርጎ የቀረበ ወግ ነው፡፡ ከጀማሪነት ጣጣ ባሻገር፣ ከጠየቁት ሰው መልስ ይልቅ የራሳቸውን ጥያቄ ብቻ የሚያዳምጡ ጋዜጠኞች ተሞክሮ የእዚህ ወግ መነሻ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ከእዚህም ባሻገር የጋዜጠኝነት ህይወት ተስፋ ሳይቆርጡ ዘወትር እየሞከሩ፣ ጥረት እያደረጉ መሻሻልም የሚቻልበት መስክ እንደሆነ በእዚህ ወግ መጨረሻ በሰፈረው ማጠቃለያ ለመጠቆም ተሞክሮበታል፡፡ ሞክሮ መሳት እና ወድቆ መነሳት የሰው ልጅ የተፈጥሮ መታገያ መርህ መሆኑን ይህ ወግ ያሳያል፡፡ ከ“ራይት“ ይልቅ “ኤክስ“ ማጠንከሪያ፣ ማነጫ መንገድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ለዚህ ትልቅ የመማሪያ መርህ ማሳያ ሆኖ የቀረበም ነው፡፡ ይህ የታምራት ወግ፣ ጀማሪ ጋዜጠኛ ወደመስኩ ሲገባ ምን ሊጠብቀው እንደሚችል ሊማርበትም ይችላል፡፡
“ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ“ የሚለው የመጽሐፉን ርእስ የያዘው ወግም፣ መቼቱ የሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ አንድ ጀማሪ ሰራተኛ፣ ‘ልምድ የሌለው‘ ወይስ ‘ዜሮ ዓመት ያህል ልምድ አለው‘ ነው የሚባለው? ዜሮ ዓመት ምን ማለት ነው? የሚል ዋዘኛ ጥያቄ በሚያነሳው በእዚህ ወግ፣ በቢሮ ውስጥ ያለን የእወደድ ባዮች እና በራሳችን እንቆማለን በሚሉ ሰራተኞች መካከል ያለን ትግልንም ያሳያል፡፡ ለመሆኑ “የዜሮ ዓመት የስራ ልምድ አለው“ ማለት እንችል ይሆን?
ታምራት በእዚህ ወጉ፣ ዜሮ ልምድ የሚለውን ዘወትር በማስታወቂያ ላይ የምናየውን የስራ ቅጥር መግለጫ አጥብቆ ይሞግተዋል፡፡ ዜሮ ለሚባለው ሂሳባዊ ጽሰሃሳብ ትዕምርት ያለን አለመሆኑ መነሻ ሆኖት ይሆን? ብዙ ጥያቄ ያጭራል፡፡
“እኔና እኔዎቼ“ የሚለው ሌላው ወግ፣ መጽሐፉ ውስጥ በተለየ መልኩ የቀረበ ወግ ነው፡፡ “…የሃሳቡ መነሻ የጆዋሪ መስኮት /Johari window/ ተብለው የሚታወቁት አራቱ የእኔነት የስነ ልቦና መለኪዎች The open Self, Blind Self, Hidden Self and Unknown Self ናቸው…“ በሚል የግርጌ ማስታወሻ የተገለጸው ወግ በጣም ግሩም በሆነ መልኩ ቀርቧል፡፡ የጋዜጠኝነት ስራ መሰረት የሆነው ጥያቄ እዚህ ወግ ላይ በርከትከት ብሎ ቀርቧል፡፡ ጋዜጠኝነት ውስጥ ላለ ሰው እንዲህ በጥያቄ የሚያንበሸብሽ ርእሰ ጉዳይ ማንሳት ብዙ ምቾት እንደሚሰጥ ተረድቻለሁ፡፡ አራት እኔዎችን (የምታወቀው፣ የማልታወቀው፣ ድብቁ እና ስውሩ እኔ) የተነተነበት ወግ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሲያከራክር የቆየ፣ እያከራከረም ያለ ትልቅ ጽንሰሃሳብ ነው፡፡ ይህንን በማሳየትና በማጥራት ረገድ ታምራት ተሳክቶለት ይሆን? እንደአንባቢው የሚወሰን ይመስለኛል፡፡
እንደ“እኔና እኔዎቼ” ሁሉ፣ “ሲግመን ፍሮይድ“፣ “ጋዜጠኛና ጋዜጠኝነት“፣ “ጋዳፊ በ2003 ዓ.ም ቢሞቱ ኖሮ…..“፣ “የቹ ቻን መጨረሻ“ በሚሉ ወጎቹ፣ በኢ–ልቦለዳዊ የፈጠራ አጻጻፍ ትዝብቱን እና ምሳሌዎችን ለማቅረብ ሞክሯል፡፡
“ንጉሡን ፍለጋ“፣ ከወደድኳቸው ወጎች አንዱ ነው፡፡ ለጋዜጠኝነት ትምህርት ጥሩ ማስተማሪያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የእዚህ ወግም አብይ መቼት የጋዜጣ ቢሮ ነው፡፡ ታምራት በሚያውቀው እና በሚቀርበው ርእሰ ጉዳይ ላይ ወጎቹን መመስረቱ በጣም ወድጄለታለሁ፡፡ የአንድ ሀገር ንጉስ ሞተው ከተቀበሩ 10 ዓመት በኋላ፣ በእርግጥ ንጉሱ ሞተዋል? የሆነ ወገን ስለሞታቸው መግለጫ ማውጣቱና በይፋዊ የቀብር ስነስርአት መቀበራቸው ብቻ የሞታቸውን እርግጠኝነት ያሳያል? በሚል መነሻ ጥያቄ የያዘች ጋዜጠኛ ይህንን ለማረጋገጥ ለተለያዩ ሰዎች የምታቀርባቸው ጥያቄዎች በጥሩ አመክንዮ የተደራጀ ነው፡፡ ጋዜጠኛ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዶ እስከምን ድረስ ማረጋገጥ እንዳለበት ያሳያል፡፡ በእዚህ ውስጥ ሰዎች ለዝና፣ ለመታወቅና ለመታየት ብቻ ጋዜጠኞችን የመፈለግ፣ ጋዜጠኝነት ውዳሴ ማቅረቢያ መድረክ ብቻ አድርጎ ማሰብን በስሱ እያሳየ፣ እያረመም የሚሄድ ወግ ነው፡፡ አቀራረቡ ማራኪ ነው፡፡
ይህንን ወግ ሳነበው ሞትን አምኖ ስለመቀበልም ተጨማሪ ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ በወጉ ውስጥ እንደተጠቀሰው ንጉሱ ስለመሞታቸው የሀገሬው ሰው አያምንም፡፡ ለአንድ ሰው መሞት ማረጋገጫው ማነው? አላምንም የሚሉትስ ዘላለማዊነት ለንጉሱ ለመስጠት ነው ወይስ በሌላ ምክንያት? የሚነግረን የሰው ልጅ ስለሞት ያለውን እይታ ነው፡፡ ይህንን ለማሳየት አንድ ወዳጄ የነገረኝን ገጠመኝ ላንሳ፡፡
ሴትየዋ ልጃቸው ዘመቻ ሄዶ አልተመለሰም፡፡ እናም በአንድ ወቅት በጦርነት የተሰው ዘማቾችን መርዶ ለመንገር መታሰቡን እኝህ እናት ሲሰሙ ዘመድ አዝማዶቻቸውን ሰብስበው፣ “ልጄ ሞቷል ካሏችሁ አታርዱኝ፡፡ ልጄ አይሞትም፡፡ ሞቷል ካላችሁ እንኳን እኔ ስሞት ታለቅሳላችሁ እንጂ አትንገሩኝ፡፡ ከነገራችሁኝ ካለልጄ መኖር አልችልምና ራሴን አጠፋለሁ“ አሉ፡፡ በእዚህም የሞተው ልጃቸው ሞት ሳይረዱ፣ ልጃቸውን ዘላለማዊ አድርገውት ለመኖር ታገሉ፡፡
እኝህ እናት የልጃቸውን ሞት እየሸሹ ነው? ሰው የሚወደውን ዘላለማዊ የማድረግ መብት አለው ማለት ነው? ዘላለማዊነትን እያሰቡ ነው? እያሸነፉ ነው ወይስ እየተሸነፉ? በእዚህ እሳቤ ሞት ዘላለማዊነትን አይገድብ ይሆን? ብዙ ጥያቄ አለው፡፡ ታምራት በእዚህ ወጉ ብዙ ጥያቄ እንዳነሳ አድርጎኛል፡፡
“አጀንዳው” የተሰኘው ሌላ ወደድኩት ወግ፣ መነሻው በ2002ዓ.ም. የአህያ ስጋን ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ ለአንድ የቻይና ኩባንያ ከቀረጥ ነፃ መብት መፈቀዱ ነው፡፡ ይህ ያሳሰባቸው አህዮች ስብሰባ አደረጉ በተባለበት በእዚህ ወግ በስብሰባው አጀንዳ ለመቅረጽ የተደረገውን ውዝግብ ያሳያል፡፡ በየስብሰባዎቻችን የጋራ አጀንዳ ለመቅረጽ እንኳን የሚበቃ አቅም እንደሌለን ጥሩ አድርጎ ለማሳየት ተሞክሮበታል፡፡ በየስብሰባዎቻችን የሚታየውን የቅርጽና ስልት እጦት፣ የዲስፕሊን ጉድለትና አቋም አልባነትንና መዋለልን በግልጽ ያሳየ ወግ ብቻ ሳይሆን የቱ ነው የጋራ አጀንዳችን የሚለውን ቁልፍ ጥያቄም ግሩም በሆነ መልኩ ለመመለስ የተሞከረበት ወግ ነው፡፡
የሰውን ልጅ የጋራ የሚያደርገው አጀንዳ ምን ይሆን? ታማራት ኃይሉ በእዚህ ወግ የነገረን የሰውን ልጅ በአንድ ላይ የሚያቆመው አጀንዳ ህልውናን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው የሚለን ይመስለኛል፡፡ የወጉን የመጨረሻ አንቀጽ ላቅርብ…
“…ጉባኤውን በትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት እንቅፋት መፍጠሩን የተገነዘበው ሰብሳቢው ‹‹ከመሀከላችን መታረድ የሚፈልግ ካለ እጁን ያውጣ›› በማለት ጠየቀ፡፡ አንድም ተሳታፊ መታረድ እና ስጋው ተብልቶ በየሰው ገበታ ላይ እንዲቀርብ ፍላጎት እንደሌለው እጁን ባለማውጣት ገለፀ፡፡ ይህን ጊዜ ሰብሳቢው ‹‹መታረድ አንፈልግም አይደል?›› ሲል ሁሉም በአንድ ድምፅ ‹‹አዎ አንፈልግም!› አሉ፡፡ይህን ጊዜ ‹‹የስብሰባው አጀንዳ ‹‹መታረድ አንፈልግም፤ ሆኗል›› በማለት ሌላ አስተያየት ሳይጠብቅ ጉባኤው አስጀመረ…“
ይህ ሁሌም ህልውናን ማስጠበቅ የጋራ አጀንዳ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ እኔ የተረዳሁት በእዚህ መንገድ ነው፡፡
ኩላሊቱ ታምራት ኃይሉ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ህመም እና እርሱን ተከትሎ ስላለው እርዳታ ማሰባሰብ ሂደት ትዝብትን ተዝናኖት ባለው መልኩ ያካፈለበት ወግ ነው፡፡ በእዚህ ወግ ውስጥ ሊያሳየን የፈለገው ያለብንን የሞራል ውድቀት፣ የሥነምግባር ክሽፈት፣ ያልጠግብ ባይነት ስስት መዘፈቅን ነው፡፡ ይህንን ዝንባሌ አደገኛ የሚያደርገው ማህበረሰቡ አይኑን ገልጾ በሚያያቸው ጋዜጠኞች እና የጥበብ ሰዎች ላይ መሆኑ ነው፡፡ የእነዚህ የአደባባይ ሰዎች ውድቀት፣ የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብን ውድቀት ይዞ የሚመጣ አደገኛ ልምምድ ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በቀጥታ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው የሚታየውን ወለፈንዴ አካሄድ “አርሂቡ“ በተሰኘው ወጉ ላይ ምጸት አዘል በሆነ መልኩ አቅርቦታል፡፡ “አሻንጉሊቴ“ በሚለው ወጉ ደግሞ በቃል ያልተገለጸ ፍቅርን የሚያሳይ፣ ተግባር ከቋንቋ ይልቅ ሲናገር ለማድመጥ መቸገር የሚያመጣውን ጣጣ የሚያሳይ ትረካ አቅርቦልናል፡፡ “እግር ኳስን በመፅሔት ስሙ”፣ “ዲያስፖራው“፣ የሚሉ ማህበራዊ ህጸጾችን የሚያሳዩ ወጎችንም መጽሐፉ ይዟል፡፡
“ይግባኝ” የሞት ፍርድ አስፈጻሚ ሰው በሞት እንዲቀጣ የተወሰነበትን ታሪክ የሚያሳይ በመጽሐፉ የተካተተ ሌላ ወግ ነው፡፡ ህግና ሥርዓትን ለማስፈጸም የሚደረግ ጥረትን የሚያሳየው ይህ ወግ፣ የሰው ልጅ ከተቀመጠ ህግና ዲስፕሊን ውጭ መስራት የሚገደደው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ የሚያጭር– ለካ ህግና ሥርዓት እስካወጣንለት ድረስ እንቢ ባይነት የለም የሚል ተጠየቅም የሚያስነሳ ውብ ወግ ነው፡፡
ታምራት፣ “የሁኔታዎች ሀገር” በሚለው ወጉ፣ የሚዲያ ተጽዕኖ እስከቤታችን እንዴት ሰርጎ እንደሚገባ እያዋዛ አውግቶናል፡፡ “የድሃ ‹ ፎርብስ›“ በሚለው ወጉም የድህነታችን ጥግ ከድሃ ድሃ በታችም ወርዶ፣ መኖሪያ ፍራንካ ሳይሆን “ራሳችንስ አለን ወይ?“ እስከሚያስብል ደረጃ መድረሱን ያሳየናል፡፡ “የመጨረሻው ሐሙስ“ የሚለው ወጉም በሚዲያ መስክ “እንደንጉሱ አጎንብሱ“ በሚል መርህ አለቆች የሚያዘጋጇቸው ደካማ ዝግጅቶች ማንም የማይተቻቸው እና ፋይዳ ቢስም ቢሆኑ እየተሸሞነሞኑ የሚቆዩ መሆናቸውን አሳይቶናል፡፡ “መጥሪያ“ በሚለው ወጉም ከታላላቅ የአዳራሽ ስብሰባዎች በፊት በየግሮሰሪው የሚደረጉ ስብሰባዎች የቃለጉባኤዎችን ግልጽና ስውር ውሳኔዎች እንዴት እንደሚፈጥሩ ያሳየበት የተቋሟዊ ሥነምግባር ልሽቀት ማሳያ ወግ ነው፡፡
በታምራት መጽሐፍ መጨረሻ የምናገኘው፣ ከሶስቱም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትሮች ጋር ታምራት ኃይሉ ያደረጋቸውን ቃለመጠይቆች ነው፡፡ “የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ውሎ“ ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ እስከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ድረስ ያደረጋቸውን ቃለመጠይቆች በግርጌ ማስታወሻው አንስቷል፡፡ የግርጌ ማስታወሻው ታሪክን በጽሑፍ የማቆየት አንድ መልካም መንገድ ነው፡፡ ይህንን ልማዱን ቀጥሎ፣ ከዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ከፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጎርጊስን ጋር በቁምነገር መጽሔት ያደረጋቸውን ቃለመጠይቆች በቀጣይ መጽሐፉ እንደሚያካትት አምናለሁ፡፡ ታምራት፣ ለጋዜጣዊ መግለጫ በተጠራባቸው መድረኮች የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ከፖለቲካ ተጽእኖ ወጣ ያሉና ለሌሎች ስልጣን ላይ ለሌሉ ሰዎች በሚጠይቃቸው ቅርጽ የተቃኙ ናቸው፡፡ ይህም ጥያቄዎቹን ለየት ያደርጋቸዋል፡፡
በመጨረሻም፣ ታምራት በዚህ የወግ መድበሉ ሊያሳየን የፈለገው ማህበረሰባዊ ዝቅታዎችን ነው፡፡ ታምራት ጥሩ ታዛቢ ነው፤ አትኩሮ ተመልካችም ነው፡፡ ባዳበረው የጋዜጠኝነት ልምዱ ልንፈወስ የግድ የሚያስብሉን በሽታዎችን ጥበባዊ በሆነ መልኩ አቅርቦልናል፡፡ እኛም እንደጋዜጠኛው አይናችን ይከፈትልን ዘንድ ትልቅ ምኞትም መሻትም አለኝ፡፡ መጽሐፉን ማንበብ ለዚህ ይረዳናል፡፡ እንደታምራት ሁሉ ሌሎችም ነባር የሙያው ባለቤቶች ማህበራዊ ተሀዝቦቱን ኪናዊ በመሆን መልክ ያቀርቡልናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

